በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ታሪክ ኢትዮጵያ 85 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ትቀመጣለች:: ከእነዚህ ሜዳሊያዎች መካከል 36 የሚሆኑት የተገኙት ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የረጅም ርቀት ሩጫዎች ነው:: ከእነዚህ ርቀቶች 10ሺ ሜትር በርካታ ሜዳሊያዎች የተመዘገቡበት ሲሆን፤ 10 የወርቅ፣ 5 የብር እና 4 የነሃስ በጥቅሉ 19 ሜዳሊያዎች ተገኝተውበታል:: በዚህ ርቀት ስኬት የጀግናውን አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ያህል የገዘፈ ታሪክ ያለው ኢትዮጵያዊ አትሌትም የለም::
ቀነኒሳ በአራት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሳትፎው (ፓሪስ፣ ሄልሲንኪ፣ ኦሳካ እና በርሊን) ቻምፒዮናዎች በ10ሺ ሜትር 4የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሲያጠልቅ፣ በ5ሺ ሜትር ደግሞ አንድ የወርቅ እና የነሃስ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል:: በአንድ ውድድር በሁለት ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያዎችን የግሉ በማድረግም ብቃቱን ያስመሰከረ አትሌት ነው:: ይኸውም እአአ በ2009 የበርሊን ዓለም ቻምፒዮና በቀናት ልዩነት በሁለቱም ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ አስደማሚ ብቃቱን ያሳየበት ሆኖ ይታወሳል:: ይህም ስኬት በአትሌቲክስ የታሪክ ማህደሮች ስሙን በደማቅ እንዲፃፍ አድርጓል::
ከቀነኒሳ ወርቃማ የውድድር ዘመን በኋላ ባሉት ቻምፒዮናዎች ግን ኢትዮጵያ በሁለቱም ርቀቶች ያገኘቻቸው ሜዳሊያዎች ቁጥር ቀንሷል:: እንደ ቀነኒሳ ሁሉ በሁለቱንም ርቀቶች የሚደፍር አትሌት ባለመገኘቱ የተነሳም በእንግሊዛዊው አትሌት ሞሃመድ ፋራህ የበላይነት ተይዞ ቆይቷል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በወጣቶቹ አትሌቶች ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ውጤት የመመለስ ተስፋ እያሳየች ትገኛለች:: ከተጀመረ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን በያዘው 18ኛው የኦሪጎን ዓለም ቻምፒዮናም ምናልባትም ሁለቱን ርቀቶች በማሸነፍ የጀግናውን አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ታሪክ የሚጋራ አትሌት እንደሚፈጠር በርካቶች ተስፋ አላቸው::
ታሪክ ለመስራት በኦሪጎን የተገኘው ሰለሞን ዛሬ ምሽት በ10ሺ ሜትር ከቀናት በኋላ ደግሞ በ5ሺ ሜትር ይሮጣል:: አገሩን ከመወከል ባለፈም የቀነኒሳን ታሪክ መድገም የምንጊዜም ምኞትና ፍላጎቱ እንደሆነ የሚናገረው ሰለሞን፣ ታሪክ ሰሪ ለመሆን በዚህ ውድድር ላይ በቂ ዝግጅት አድርጓል:: ሰለሞን ወደ ኦሪገን ከማቅናቱ በፊት ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ‹‹እኔ ባላሳካውም ጓደኞቼ ያሳኩታል፤ እንደ ቡድንም ጥሩ ውጤት እናመጣለን›› ሲል በርቀቶቹ የሚጠበቁት ድሎች ከእሱ እጅ ቢወጡም ከኢትዮጵያ እንደማያመልጡ ይናገራል::
በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ይሆናል የሚል ተስፋ የተጣለበት ይህ ድንቅ ወጣት አትሌት፤ ባለፈው የዶሃ የዓለም ቻምፒዮና ሙክታር እድሪስን ተከትሎ በመግባት በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ ማጥለቁ የሚታወስ ነው:: ይኸውም አትሌቱ በርቀቱ ያለውን ብቃትና ውጤታማነት ያሳየ ሆኗል:: በኦሪገኑ ቻምፒዮና ላይም ካለው አስደናቂ ወቅታዊ አቋም አንጻር በሁለቱም ርቀቶች ወርቆችን ያጠልቃል ተብሎ ይጠበቃል::
የ10ሺ ሜትርን ድል ከሁለት ኦሊምፒኮች በኋላ ቶኪዮ ላይ ማሳካት የቻለው ይህ ወጣት የረጅም ርቀት ተወርዋሪ ኮከብ አስደናቂ አጨራረስ ብቃቱና የማይደክሙ እግሮቹ ዛሬ ተዓምራቸውን ለዓለም ማሳየት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል:: ሰለሞን በዘንድሮ ዓመት በቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በ3ሺ ሜትር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያውን ያጠለቀበት ሂደትም ለዚህ ማረጋገጫ ነው:: ባለፈው ወር በዳይመንድ ሊግ ውድድር በፓሪስ 5ሺ ሜትርን በከባድ የአየር ንብረት ተፎካካሪዎቹ እስከማቋረጥ ሲደርሱ እሱ ያሸነፈበት ውድድርም የዛሬው የ10ሺ ሜትር ወርቅ የግሉ እንደሚሆን ፍንጭ የሰጠ ነው:: ‹‹ለዚህ ቻምፒዮና ጥሩ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል›› የሚለው ሰለሞን፤ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል የብሄራዊ ቡድን ጥሪ እስከሚደረግ ጊዜው ቢዘገይም ይህንን ውድድር ያማከለ ዝግጅት በግሉ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግሯል:: ከጥሪው በኋላም ከቡድኑ አባላት ጋር መልካም የሚባል ዝግጅት አከናውኗል:: ዓመቱ በርካታ የግልና የአገር ውድድሮች የነበሩበት ሲሆን፤ የሄንግሎው የሰዓት ማሟያም በመዘግየቱ ከውድድሮች ጋር እጅግ የተቀራረበ ጊዜ ላይ በመከናወኑ አትሌቶች ላይ ጫና ነበረው:: ከሄንግሎው ማጣሪያ በኋላ ግን ከውድድሮች በመታቀብ እሱና የቡድን አጋሮቹ ወደ ዝግጅት መግባታቸውን ያስረዳል::
በዚህ ዓመት በ10ሺ ሜትር በርካታ ውድድሮች ያልተደረጉበት እንደመሆኑ ተፎካካሪዎቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው:: ከኬንያ በቀር ሌሎች ቡድኖች የሰዓት ማሟያ ሲያደርጉም ባለማሳወቃቸው ምክንያት የትኛው አትሌት ምን አይነት ብቃት ላይ እንደሚገኝ ለመገመት አስቸጋሪ ነው:: እንደ ኢትዮጵያ ግን መልካም አቋም ላይ በሚገኙ አትሌቶች የተገነባ ቡድን ወደ ኦሪገን እንደተጓዘ ይታመናል:: ከዚህ ቀደም ሰለሞንና ሌሎች ወጣት አትሌቶች ከልምድ አንጻር ያለባቸው ክፍተት ካለፈው ጊዜ ትምህርት በማግኘት የተሻለ ውጤት ለማምጣት በሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ብርቅየው አትሌት አስተያየቱን ሰጥቷል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2014