በፖርትላንድ ኦሪገን ትናንት በተጀመረው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እየተካፈለች የምትገኘው ኢትዮጵያ ውጤታማ እንደምትሆን ከምትጠበቅባቸው ርቀቶች መካከል የወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል እና የሴቶች 1ሺ500 ሜትር ተጠቃሾች ናቸው።በዚህ ርቀት አገራቸውን የሚወክሉት ወጣት አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ላይ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ሲሆን፤ በዚህ ቻምፒዮናም ከወርቅ ጀምሮ ሌሎች ሜዳሊያዎችን እንደሚያስመዘግቡ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
በቻምፒዮናው የ3ሺ ሜትር መሰናክል የወንዶች ውድድር የሰሜን እና ምስራቅ አፍሪካውያን ትንቅንቅ የሚታይበት እንደሆነ በበርካታ የአትሌቲክስ ቤተሰብ ዘንድ ግምት አግኝቷል።ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሜቻ ግርማ እና ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያውን ለማጥለቅ የሚፋለሙ አትሌቶች ናቸው።ሁለቱ አትሌቶች ባለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ባደረጉት አስደናቂ ፉክክር ኤል ባካሊ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ ለሜቻ ብሩን የግሉ አድርጓል።ባለፈው የዶሃ 2019 የዓለም ቻምፒዮናም ሁለቱ አትሌቶች ተገናኝተው ለሜቻ የብር ሜዳሊያ ሲያጠልቅ ሞሮኳዊው አትሌት የነሐስ ሜዳሊያ ነበር ማሸነፍ የቻለው።ይህም የሁለቱን አትሌቶች ፉክክር በጉጉት እንዲጠበቅ ያደረገ ሲሆን ርቀቱ ባህላቸው እንደሆነ ደጋግመው ያሳዩ ኬንያውያንም የተዳከሙ ቢመስሉም አዲስ ነገር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይታመናል።
ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ብዙም በማትታወቅበት 3ሺ ሜትር መሰናክል ውጤታማ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ወጣቱ አትሌት ለሜቻ በቤልግሬድ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤት መሆኑ ይታወሳል። በዚህም የዓለም አትሌቲክስ በዓመቱ የምርጥ ወጣት አትሌት ምርጫ ውስጥ በእጩነት ያካተተው ተስፈኛው አትሌት ያለፉትን ውድድሮች የሚያስታውሳቸው በቁጭት ነው።በዶሃው የዓለም ቻምፒዮና ለጥቂት በሽርፍራፊ ማይክሮ ሰከንዶች ተቀድሞ የወርቅ ሜዳሊያ ያጣው ለሜቻ፤ የፊታችን ሰኞ በኦሪገን በወርቅ ሜዳሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመድመቅ እድል እንደሚኖረው በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ተስፋ አድርገውበታል።
በውድድር ዓመቱ በግሉ እንዲሁም አገሩን ወክሎ በበርካታ ውድድሮች ላይ በመካፈል አንፀባራቂ ውጤቶችን ማግኘት የቻለው ለሜቻ፣ ያለፈውን ቻምፒዮና ቁጭት ለመወጣት ኦሪገንን በጉ ጉት ሲጠብቅ ነበር። በመሆኑም ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ዓመቱን ለማጠቃለል መልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ነው ወደ ኦሪጎን ከማ ቅናቱ በፊት ለአዲስ ዘመን የተናገረው፡፡
ለሌሎች ውድድሮች የሚያዘጋጀውና የሩጫ እቅድም የሚያወጣለት አሰልጣኙ ተሾመ ከበደ በዓለም ቻምፒዮናው ብሄራዊ ቡድኑን በርቀቱ እንዲያሰለጥን መመ ረጡ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ የዝግጅት ጊዜውን አብረው በማሳ ለፋቸው እንዲሁም አብረውት በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉት አትሌቶች ጋር እንደ ቡድን በጋራ በመዘጋጀታቸው ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል።ይህም ባለፈው ቻምፒዮና በርቀቱ ለጥቂት ያመለጠውን የወርቅ ሜዳሊያ ለማጥለቅ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥርለት አሰልጣኙ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከነገ በስቲያ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ያገኙበት ሌላኛው ርቀት የሴቶች 1ሺ500 ሜትር ውድድር ነው።በዚህ ርቀት በመላው ዓለም በርካታ ተፎካካሪዎች ያሉ ሲሆን፤ በኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋይ የሚመራው ቡድን ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።በዓለም ቻምፒዮና ታሪክ እጅግ ስኬታማዋ አትሌት ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዬጎን ብትሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሌላኛዋ ሆላንዳዊት ጠንካራ አትሌት ሲፋን ሃሰን ተቆጣጥራዋለች።ይሁንና ወጣቶቹ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በዚህ ዓመት በተለያዩ ውድድሮች ባሳዩት አስደናቂ አቅም የአሸናፊነት ግምት እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡
ኬንያዊቷ አትሌት ከጉዳት እያገገመች ያለች በመሆኑ እንዲሁም ሆላንዳዊቷ ሲፈንም በጾምና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ልምምዷን እንደወትሮው አለመቀጠሏ ምናልባትም በውጤታቸው ላይ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።ይህም ለኢትዮጵያውያኑ አንድ መልካ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል።መልካም የውድድር ዓመት እያሳለፈች የምትገኘው ጉዳፍ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በዚሁ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች።ይህም አትሌቷ ሌላኛውን የርቀቱን ስኬት በኦሪጎን ታጣጥማለች በሚል ተስፋ እንዲጣልባት ያደረገ ሲሆን፤ እአአ 2015 ቤጂንግ ላይ በፈጣኗ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የተወሰደውን የበላይነት በድሏ ትደግመዋለች በሚል ቅድመ ግምቱን ልታገኝ ችላለች።
ከአትሌቷ ጋር በመሆን አገራቸውን ወክለው ውድድሩ ላይ የሚሳተፉት ወጣቶቹ አትሌቶች ሂሩት መሸሻ እና ፍሬወይኒ ኃይሉም ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም።ሂሩት ቤልግሬድ ላይ ጉዳፍን ተከትላ በመግባት የነሃስ ሜዳሊያውን ስትወስድ፤ ፍሬወይኒ ደግሞ በዚሁ ውድድር ላይ የ800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ነበረች።በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይም ጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኙ ማስመስከራቸውን ተከትሎም የስፖርት ቤተሰቡ ለተፎካካሪዎቻቸው ፈተና ከመሆን ባለፈ የሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥም የመግባት ተስፋ እንዳላቸው ነው የሚጠብቀው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2014