በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስመጥር የሆነው ሕዝባዊ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና እንደ ገናና ስሙ የሊጉን ዋንጫ ደጋግሞ በማንሳት ስኬታማ መሆን አልቻለም። በርካታ አሰልጣኞችን ቢቀያይርም ውብ እግር ኳስን እንጂ የሊጉን ዋንጫ ለውብ ደጋፊዎቹ ከአንድ ጊዜ የበለጠ ማበርከት አልቻለም።
ከሶስት ዓመት በፊት የክለቡን ባህልና አጨዋወት ጠንቅቆ የሚያውቀው የቀድሞ ተጫዋቹ ካሳዬ አራጌ ከሚኖርበት አሜሪካን አገር መጥቶ በዋና አሰልጣኝነት ክለቡን መምራት ሲጀምር ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ይሁን እንጂ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከክለቡ ጋር ከሶስት ዓመታት የበለጠ አብሮ እንደማይዘልቅ ተረጋግጧል።
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከመጣ በኋላ ባለፉት 3 ዓመታት በቆየበት ጊዜ አምና በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። ኮከብ ተጫዋችና ኮከብ ግል አግቢ የነበረው አቡበከር ናስርን አስመርጧል። በየጨዋታው ያገኛቸውን ተጋጣሚዎቹን ሁሉ እግር ኳሳዊ በሆኑ ቁጥሮች በልጦ ማሳየት ቢችልም ደጋፊው የተራበውን ዋንጫ ግን ማሳካት አልቻለም። ለረጅም ጊዜ ተይዞ የነበረው የሊጉ የግብ ክብረወሰንም በእሱ ዘመንና ተጫዋች መሰበሩ ከሚጠቀሱለት ስኬቶች ቀዳሚ ናቸው። ሆኖም ለክለቡ ኃላፊዎች ይሄ በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ሊያሰናብቱት ወስነዋል።
በርካታ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን እንደዘገቡትም ኢትዮጵያ ቡና ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር ያለውን ውል ሐምሌ 30/2014 እንደሚያቋርጥ አሰልጣኙም በኃላፊነቱ የተረከባቸውን ንብረቶች እንዲመልስና የሐምሌ ወር ደመወዙም እንደሚከፈለው በመግለጽ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ ካስገባ ቀናቶች አልፈውታል።
ኢትዮጵያ ቡና የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ የነበረውን አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩን ዛሬ ይፋ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም መረጃዎች ወጥተዋል። ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀሉትና የሚቀላቀሉት ተጫዋቾችም በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ምርጫ መሆኑ ተጠቁሟል። የአሰልጣኝ ካሳዬ ተተኪ የሚሆነው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና የመሆኑ መረጃ ከወጣ በኋላ የክለቡ ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ሲሆን ለክለቡ የፈረሙትና ይፈርማሉ የተባሉ ተጫዋቾች ክለቡን ያጠናክራሉ ብለው እንደሚያምኑ ነገር ግን አሰልጣኙ ላይ እምነት እንደሌላቸው በመግለጽ ጠንካራ የሆነ ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
የአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመራ ከተመረጠበት 2010 ጀምሮ በፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ተፈላጊ መሆን ችሏል። አሰልጣኝ ተመስገን በ2011 የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ምክትል ሆኖ ሀዋሳ ከተማን አሰልጥኗል። በ2012 የደቡብ ፖሊስ ዋና አሰልጣኝ ቢሆንም በኮቪድ ምክንያት ውድድሩ እስኪቋረጥ ሰርቶ 2013 ላይ እንደገና ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን ተረክቦ አንድ አመት ተኩል አሰልጥኗል።
አሰልጣኙ በሴካፋ ከ20 አመት ቻምፒዮና ሁለተኛ የወጣበት ታሪኩ ትልቁ ሆኖ ተመዝግቦለታል። ከብሔራዊ ቡድኑ መልስ ወልቂጤ ከተማ የክለቡ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት 12 ጨዋታ ከመራ በኋላ በመለያየታቸው አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን በመቅጠር የ2014 18 ጨዋታን እንዲመራላቸው በማድረግ የዘንድሮውን የውድድር አመት አጠናቋል።
አሰልጣኙ ለተመልካች በሚስበው ምርጥ አጨዋወት የሚታወቅ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ሲሆን የቡናን ማራኪ አጨዋወት ያስቀጥላል ተብሎ በአመራሮቹ ታምኖበታል። ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር ህጋዊ ውል ያላሰሩት የቡናማዎቹ አመራሮች ግን የደጋፊዎቹን ጫና ፈርተው ሀሳባቸውን ይቀይራሉ ? ወይስ ? በጀመሩት አዲሱ ፕሮጀክት ይቀጥላሉ የሚለው ጉዳይ ዛሬ ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል።
የወልቂጤ ከተማን በ2014 የውድድር ዓመት ከሁለተኛው አጋማሽ በኋላ የተረከቡት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና አሁን አዲሱ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ እንደሚሆኑ ግን ባለፉት ጥቂት ቀናት የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።
በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ42 ነጥብና 8 የግብ ዕዳ 6ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ከያዛቸው ተጫዋቾች መካከል በእስካሁኑ አምበሉ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ተከላካዩ አስራት ቱንጆ፣ ሁለቱ ግብ ጠባቂዎች በረከት አማረና እስራኤል መስፍን.፣ ታዳጊዎቹ ገዛኸኝና ሱራፌል ጨምሮ ከ10 የማይበልጡ ተጨዋቾች ብቻ ሲቀሩ ቀሪዎቹ ውል ያላቸው በስምምነት ውላቸው ያለቀ ደግሞ ውላቸው ሳይታደስ ቡድኑን እንዲለቁ የሚደረግ መሆኑ ከክለቡ ተጫዋቾች የተገኘ መረጃ ጠቁሟል። ክለቡ ውል ያላቸውን ተጫዋቾች በስምምነት እንዲለያዩ መጠየቅ መጀመሩም ታውቋል።
እስካሁን ባለው መረጃ በዲሲፕሊን ደመወዙን ከተቀጣው ዊሊያም ሰለሞን፣ ከሶስት ወር የደመወዝ ቅጣት በኋላ የመጀመሪያ ደመወዙን የወሰደው ታፈሰ ሰለሞንና ሚኪያስ መኮንን ጨምሮ አብዛኞቹ ቡድኑን እንደሚለቁ እየተገለጸ ነው። ኢትዮጵያ ቡና ከአቡበከር ናስር ዝውውር የተገኘውን ገንዘብ ለዘንድሮ ዝውውር እንዲውል መወሰኑም እየተነገረ ነው።
የክለቡ ፕሬዘዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ “ዘንድሮ ከመቼውም ጊዜ ደካማ የሆነ ውጤት እንዳይመዘገብ የምትችሉትን ጣሩ በቀጣይ የውድድር አመት ግን ውጤታማ አሰልጣኝና ለዋንጫ የሚፋለም ስብስብ ይኖረናል” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን የመቶ አለቃ ፈቃደ ንግግር በቀጣዩ አመት ሊመጣ የሚችለውን አሰልጣኝ በይፋ ባያሳውቅም ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር ግን እንደማይቀጥሉ ያመላከተ ሆኗል።
እስከ ትናንት ድረስ ቡናማዎቹ መስፍን ታፈሰን ከሀዋሳ ከተማ፣ መሀመድ ኑርን ከጅማ አባጅፋር እንዲሁም አብዱልከሪም ወርቁን ከወልቂጤ ከተማ፣ ሃይለሚካኤል አደፍርስና ዱሬሳ ዱቢሳን ከሰበታ ከተማ ለማስፈረም መስማማታቸው በስፋት ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ዓርብ ሐምሌ 1/2014 በይፋ ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6/2014