በሩጫ፣ ዝላይ እና ውርወራ ስፖርቶች ምርጥ አትሌቶች ብቃታቸውን ለማሳየት የሚፋለሙበት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በተያዘው ሳምንት መጨረሻ ይጀመራል። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ተራዝሞ የቆየው ይህ ውድድር፤ የ192 አገራት ብሄራዊ ቡድኖች ውስጥ የተካተቱ 1ሺ900 የሚሆኑ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆኑበታል። ለአስር ቀናት በሚቆየው ውድድር የሚካፈሉ አገራትም ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን ወደስፍራው በማጓጓዝ ላይ ይገኛሉ።
ከእነዚህ መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን የመጀመሪያ የአትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድኗ አባላት ትናንት ከምሽቱ 4ሰዓት ከ30 ላይ ወደ ስፍራው አቅንተዋል። በአምስት ዙር ተከፋፍሎ ወደ አሜሪካዋ ኦሪጎን የሚጓዘው ቡድን ዛሬ ምሽትን ጨምሮ በቀጣዮቹ ቀናት ወደ ስፍራው እንደሚያመራም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ከመጀመሪያው ጀምሮ በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ በመሆን በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ላይም ስሟን ማስፈር የቻለችው ኢትዮጵያ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ አዳዲስና ነባር አትሌቶችን ያሰባጠረ 47 አባላቱን ጨምሮ ሌሎች ልኡካንን ወደ ስፍራው ትልካለች።
ላለፈው አንድ ወር በዝግጅት ላይ የቆየው የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ውድድሩ ስፍራ ከማምራቱ አስቀድሞም ባለፈው ቅዳሜ በስካይ ላይት ሆቴል የሽኝትና የሰንደቅ አላማ ርክክብ መርሃ ግብር አካሂዷል። የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአትሌቲክስ ስፖርት ሙያ ማህበራት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም በመርሃግብሩ ተገኝተዋል። ለአትሌቶቹ፣ ለአሰልጣኞችና ለቡድኑ አመራሮችም የአገር አደራ ምልክት የሚሆን የሰንደቅ አላማ ርክክብ ተደርጓል። በወቅቱም የቡድኑ አባላት የአገራቸውን ስም ለማስጠራት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በብሄራዊ ቡድኑ የረጅም ርቀት አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሽቦ፤ አሰልጣኞችን በመወከል ለውድድሩ በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። አትሌቶችን በአካልም ሆነ በአእምሮ የተዘጋጁ በመሆኑ በዚያው ልክ አገራቸውን ለማስጠራት የሚችል ውጤት ያስመዘግባሉ የሚል ተስፋቸውንም አንጸባርቀዋል። የ3ሺ ሜትር መሰናክል ተወዳዳሪዋ አትሌት የወርቅውሃ ጌታቸው እንዲሁም የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ተሳታፊው አትሌት ሰለሞን ባረጋም በተመሳሳይ ንግግር አድርገዋል። አትሌቶች ለዚህ ውድድር የሚመጥን ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቁመውም የአገራቸውን ባንዲራና ስም በድል ለማስጠራት በውድድሩ እንደሚካፈሉም ገልጸዋል።
በውድድሩ ላይ ቡድኑን በምክትልነት የሚመራው ኮማንደር አትሌት ማርቆስ ገነቲ፤ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሲነሳ የሚታወሰው የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል መሆኑን ጠቁሟል። በዚህ ውድድርም በተመሳሳይ ቡድኑ የአገሩን ስም ለማስጠራት የሚካፈል መሆኑን ገልጻል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ፣ ይህ የውድድር መድረክ እርስ በእርስ በመረዳዳት በቡድን ስራና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በታሪክ መዝገብ ላይ የአገርን ስም ለማጻፍ የሚቻልበት ወርቃማ እድል መሆኑን ገልጻለች። በቻምፒዮናው ላይ የኢትዮጵያን ስም ለማስጠራት በትጋት ሲዘጋጁ የቆዩ አትሌቶችን፣ አሰልጣኞችና መላው ልኡካን ቡድን የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ታላቅነት በማንሳትም ቡድኑን አበረታታለች።
የሰንደቅ አላማ ርክክቡን ያደረጉት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ፤ ልኡካኑ የሄዱበትን ዓላማ ለማሳካት መንፈሰ ጠንካራ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ስፖርታዊ ውድድር ከአካላዊ ብቃት ባለፈ በአእምሮም ዝግጁ መሆንን ስለሚፈልግ መጠንከር ያስፈለጋል። በተለይ በቡድን መስራት እና ስፖርታዊ ስነምግባርን ማክበር ለአትሌቶች አስፈላጊ ነው። የቡድን መሪዎችም በአግባቡ ቡድኑን እንዲመሩና ለስኬት እንዲያበቁም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአትሌቲክስ ስፖርት ስኬቷ የምትታወቀው ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ለ17ኛ ጊዜ የምትሳተፍ ሲሆን፤ ከአንድ ጊዜ ውጪ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ መልካም የሚባል ውጤት አላት። በዚህም 29የወርቅ፣ 30የብር እና 26የነሃስ በድምሩ 85 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በዓለም የደረጃ ሰንጠረዡ ሰባተኛ ላይ ልትቀመጥ ችላለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2014