ያለንበት ወቅት ከባዱ የክረምት ወር መጀመሪያ ሐምሌ እንደመሆኑ ማልዶ ከሚጥለው ዝናብ በተጨማሪ ጭፍጋጋ ቀናትን እያሳለፍን እንገኛለን።በዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችንም ከክረምት ጋር ጥምረት ያላቸውን አደጋ ነክ ዜናዎች ባለፉት ዘመናት በአገራችን እንዴት እንደነበሩ ለማየት ሞክረናል።
ሌሎች ዘገባዎችን ጨምሮ ከሕገወጥ እርድ ጋር በተያያዘም በመዲናችን ይታዩ የነበሩ ችግሮች የተዘገቡባቸውን ጋዜጦች ይዘናል፡፡
በዝናም ምክንያት ተራራ ተንዶ ስለሞቱት ሰዎችና ከብቶች
በአርሲ ጠቅላይ ግዛት በከንባታ አውራጃ በዴንሳ ጥምባሮ ምክትል ወረዳ ግዛት በአቶ ፀደቀ ጋረዴ ባላባትነት ውስጥ በነሐሴ 24 ቀን 1946 ዓም ለ25 አጥቢያ ሌሊቱን በዘነበው ኃይለኛ ዝናም በሣና የተባለው ተራራ ተንዶ፤ ከዚሁ ጋራ ሥር የሚኖሩ የቤቱ ጌታ አንቃሞ፣ 2ኛ ሚስቱ በቦሬ በዶሬን፣ 3ኛ ልጁን ሸክሜ አንቃሞ የሚባሉትን ሰዎችና ከበረት የነበሩት ፲፩ የቀንድ ከብቶች፤ ሁለት ባዝራ ፈረሶች፣ ፭ በጎች በናዳው የጋራ አደጋ ሲሞቱ፤ አንደ ዶሮና አንድ ባዝራ ፈረስ ከዚሁ አደጋ ድነው ታይተዋል።ከተናደው ጋራ ሥር አንድ ምንጭ ፈንድቶ መታየቱን ያውቁት ዘንድ እገልፅሎታለሁ፡፡
ማህተም የአርሲ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ ዋና ጽ/ቤት ፡፡
ፊርማ ሻለቃ አበበ ወልደ ሥላሴ የአሩሲ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ ምክትል ዋና አዛዥ
(ነሐሴ 27 ቀን 1946 የወጣው አዲስ ዘመን)
የነፋስ አደጋ
ጎንደር፤ (ኢ-ዜ-አ) በጎንደር አውራጃ ግዛት በታች አርማጭሆ ወረዳ በአፍደራፊ ከፍተኛና አካባቢው ባለፈው ረቡዕ ዝናም ቀላቅሎ የነፈሰው ኃይለኛ ነፋስ በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተገለጠ፡፡
በዚሁ የነፋስ አደጋ የ፳፬ መኖሪያ ቤቶች የቆርቆሮ ክዳን ተገነጣጥሎ ከጥቅም ውጪ ሆኗል።እንዲሁም የእመት ታደለች ገብረሕይወት አንድ ክፍል የመኖሪያ ቤት በቤት ውስጥ ካለው ምድጃ ላይ በነፋስ ኃይል በተነሳው እሳት ተቃጥሏል፡፡
ይኸው የነፋስ አደጋ በንብረት ላይ ካደረሰው ጉዳት ሌላ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ አለማድረሱን፤ ምክትል የመቶ አለቃ ግርማ ዘውገ የበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ የማስታወቂያና ሕግ ክፍል ሹም ገልጠዋል፡፡
(ሰኔ 14 ቀን 1964 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
የተማሪዎች ልብስ በሽያጭ ታደለ
ከጅማ፤ የትምህርትና ሥነጥበብ ሚኒስቴር በትምህርት ገበታ ላይ የሚውሉት ሕፃናትና ጎልማሶች እንደየ ትምህርት ደረጃቸው የመለያ ልብስ እንዲለብሱ ባደረገው ውሳኔ መሠረት ለከፋ ጠቅላይ ግዛት ትምህርት ቤቶች ማለት ለአንደኛ ለ፪ኛ ደረጃ ተማሪዎች ፩ሺህ ፭፻፹፬፤ ፪ኛ ለአንደኛና ፪ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፭፻፲፮ በድምሩ ፪ ሺህ ፩፻ ተማሪዎች በሽያጭ የሚታደል ልብስ ሰኔ ፲፭ ቀን ፶፯ ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተልኮ ሲታደል የዋለ መሆኑን የጠቅላይ ግዛቱ ትምህርት ቤቶች ጠቅላይ ሥራ አስኪጅ አቶ ስዩም ወ/መስቀል ገልጠዋል፡፡
በዚህ ዓመት በጠቅላይ ግዛት በሚገኙት ፲፰ ትምህርት ቤቶች እስከ ፮ኛ ክፍል ድረስ የሚሰጠውን ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩት ፬፻፵ ወንዶችና ፳፩ ልጃገረዶች ተማሪዎች ከሰኔ ፲፮ ቀን ጀምሮ ወደ ፱ ክፍል ማለፊያ ፈተና እንደሚቀበሉ ታውቋል፡፡
(ሰኔ 18 ቀን 19 57 የወጣው አዲስ ዘመን)
የሕዝባዊት ቻይና ኤክስፐርቶች አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ፤ (ኢ-ዜ-አ-) ሰባት የኮሚኒስት ቻይና መንግሥት የጠቅላይ ግዛት ከተማዎች፤ የኤሌክትሪክ ጥናት አዋቂዎች፤ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ከተማዎች የሚቋቋሙትን የኤሌክትሪክ መብራቶችን ጥናት ለመመልከት ጧት በአይሮፕላን ከፔኪንግ አዲስ አበባ ገቡ፡፡
በሚስተር ማ-ሚንግ-ቲ- የሚመሩት ሰባቱ አዋቂዎች የዲዘልና በወሀ ጉልበት የሚሠራ የኤሌክትሪክ ኃይል መስጫ መሣሪያዎች ኢንጂነሮች ናቸው፡፡
እንግዶቹ በኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ ጠቅላይ ግዛቶች የኤሌክትሪክ መብራት የሚቋቋምባቸውን ሥፍራዎች እየተዘዋወሩ እንዲመለከቱ የላካቸው የቻይና የውጪ አገር የኤኮኖሚ ኅብረት ሚኒስቴር ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የቻይና የመንገድ ቅየሳና የወሀ ልማት ኤክስፐርቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አሁን በጥናት ላይ እንደሚገኙ መገለጡ የሚታወስ ነው፡፡
(ሐምሌ 1 ቀን 1964 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ያለፈቃድ የታረዱ ፩፻፴፮ በጎች ለእግዚቢት ተይዘዋል
በአዲስ አበባ በልዩ ልዩ ሠፈሮች ያለፈቃድ የታረዱ ፳፭ በጎች፣ አንድ ጥጃና ፩፻፴፮ የበግ ጭንቅላቶች ትናንት መያዛቸውን ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ጽዳት ክፍል የተገኘው ወሬ ያስረዳል፡፡
ሕገወጥ ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙት ሰባት ሰዎች ከነኤግዚቪቱ የያዙ የጽዳት ክፍሉ ያሠማራቸው ፵ የሚሆኑ የጽዳት ዘበኞችና ሠራተኞች ናቸው።ያለ ፈቃድ ታርደው ከተገኙት ውስጥ ጥጃው ከሞተ በኋላ ለበላተኛ ለሆቴል ምግብ ሆኖ እንዲያገለግል የተደረገ መሆኑ ታውቋል።ይህንን ተግባር የፈጸመው ሰው አብሮ ተይዟል።
የፅዳቱ ክፍል ዋና ዲሬክተር የተያዙት ሥጋዎች ከፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ቄራ ተወስደው እንዲቃጠሉና አራጆቹ እንዲቀጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።ባለፈው ጊዜ ፩፻፹፯ የበግ ጭንቅላት ሥጋና ቆዳ ተይዘው መቃጠላቸው የሚታወስ ነው፡፡
የፅዳት ክፍሉ ሠራተኞች የሚያደርጉትን ጥብቅ ቁጥጥር እየተቃወሙ አምባጓሮ የሚያበቅሉ ብዙ ሰዎች መኖራቸው ተገልጧል።ይህንን አድራጎት የሚከታተሉ ሕገወጦች የወገኖቻቸው ጤና እንዳይጠበቅ የሚጥሩ ናቸው፡፡
አድራጎታቸው ሁሉ ከሕግ የወጣ ስለሆነ፤ በግሣፄ ብቻ መታለፍ የለባቸውም።ዐጥፊዎቹ በሕግ ፊት ቀርበው ቅጣት እስኪፈጸምባቸው ድረስ የጽዳት ዘበኞቹ ከርኅራኄ የወጣ ተግባር ባይፈጽሙ መልካም ነው፡፡
(ሰኔ 11 ቀን 1957 የወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2014