ክፍል አራት እና የመጨረሻው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ወቅታዊ አገራዊ ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል። ይህንኑ ምላሽና ማብራሪያ በተከታታይ ማስነበባችን ይታወሳል። በዛሬው አራተኛና የመጨረሻው ክፍል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለግንዛቤ ያክል በሚል ለምክር ቤቱ የሰጡትን ተጨማሪ ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤
ይቅርታ ! የተከበሩ አፈጉባኤ በቀጥታ ኢንተርፊር ማድረግ ያለብኝ ጉዳይ ባይሆንም አንዳንድ ነገሮችን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ትንሽ ጊዜ ልወስድባችሁ ነው።
አንደኛው ይሄ ምክር ቤት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የመገምገም ስልጣን የለውም፣ ቀመር እንዲህ ለምን አላወጣም እንደዚህ አልገመገመም ኢ- ሕገመንግስታዊ ነው፣ ይሄ ምክር ቤት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የመገምገም ስልጣን የለውም፤ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የራሱ አሰራር አለው። እናንተ ሕግ ስታወጡ ሕግ የሚታይበት አሰራር አለ፤ እናንተ የምትገመግሙት አስፈፃሚውን፣ ሕግ አውጪውን ሲሆን እነሱን በጋራ ስብሰባዎቻችሁ እነዚህ ጉዳዮች ቢታዩ መጠየቅ ካልቻላችሁ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሰብስቦ ስለእናንተ ሕግ አወጣጥ የሚገመግም ከሆነ እኛም እዚህ ተቀምጠን ስለእነሱ የምንገመግም ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ማን መልስ ይስጥበት? ፌዴሬሽን ምክር ቤት እዚህ ካለው የሕዝብ ውክልና በላይ በተለየ መንገድ ውክልና ያለው ስብስብ ነው።
እያንዳንዱ ብሔር የተወከለበት ስብስብ ነው። ጥያቄ ካለን በሁለቱ አፈ ጉባዔዎች አማካኝነት የጋራ ስብሰባ አድርገን ባሉበት ይሄን ጉዳይ እንዴት አደረጋችሁት፣ እንዴት አያችሁት ብለን አብራሩ ማለት ነው ያለብን እንጂ እነሱ በሌሉበት የእነሱን አሰራር ትክክል አይደለም ብለን የምንገመግም ከሆነ ቅድም እንዳነሳሁት አይነት ጉዳይ ይፈጠራል። ምክር ቤት ማለት የሁሉ ጠቅላይ ማለት አይደለም፣ የተገለፀ ስልጣን ያለው ሃይል ነው፤ እሱ ታሳቢ ቢደረግ ጥሩ ነው።
ሁለተኛ ከቀመር ጋር ተያይዞ ምክር ቤት ቀመር አላየም የሚለው ስህተት ነው፣ ሕዝብ ቆጠራ ተደርጎ በዚያ መሰረት ሕጉ አልተሻሻለም እንጂ በጣም በርካታ ሪፎርሞች ሰርቷል። ለምሳሌ የጋራ ገቢ፣ የጋራ ገቢ ዛሬና ትናንት አራምባና ቆቦ ነው። ቢሊየን ብሮችን ክልሎች ይወስዳሉ። አሁን ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጥንቶ አሻሽሎ የጋራ ገቢ ትክክል አይደለም ብሎ ድሮ ምንም የማያገኙ ክልሎች በሺህ ፐርሰንት፣ በመቶ ፐርሰንት እድገት አግኝተዋል።
ሁለተኛ ቅድም እንዳነሳሁት ክልሎች በቀመሩ ሂሳብ ከፍ ያለ በጀት የሚያገኙ ሁሉም ክልሎች ስላሉበት ተነጋግረው አንዳንድ ክልሎች ከራሳቸው ቀንሰው አነስተኛ ገቢ ላላቸው ተጨማሪ ድጎማ እያደረጉ ነው። እና ምንም አይነት ስራ ሳይሰራ ዝም ብሎ ጅምላ እንደሄደ አድርጎ መውሰድ ትክክል አይደለም። የሕዝብ ቆጠራ ቅድም እንዳነሳሁት አስፈላጊ ነገር ነው።
እንደምታስታውሱት የዛሬ ሁለትና ሦስት ዓመት ገደማ ቆጠራ እንዲካሄድ ወስነን ነበር፣ ቆጠራው እንዳይካሄድ የተቃወማችሁት እናንተ ነበራችሁ፤ አብኖች። በተረጋጋው ጊዜ ማለት ነው።
ጠርተንም አወያይተናችኋል፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ፣ ቆጠራው እንዲካሄድ ፍላጎት ነበረ፣ ያላችሁት አይነት መዛባቶች እዚያም እዚያም እንዲስተካከሉ ማለት ነው፣ ቆጠራው ሳይካሄድ ግን ሰው ተነስቶ እንደዚህ ጎደለ፤ እንደዚያ ጎደለ ቢል ንግግር ነው የሚሆነው። ቆጠራውን አካሂደን የጎደለ ነገር ካለ መጠየቅ ግን ያስፈልጋል።
ሁለት ነገር ይነሳል የተከበረው ምክር ቤት በደንብ እንዲያሰምርበት፣ አንደኛው ፍልሰት ነው። ይሄ የክልል ቁጥር ትክክል አይደለም በርካታ ሚሊየን ሰዎች እየፈለሱብኝ ነው የሚሉ ክልሎች አሉ፣ ሰውየው የተቆጠረው እዚያ ነው፤ የሚኖረው ግን እዚህ ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ በሚሊየን የሚቆጠር ፍልሰት አጋጥሞኛል፣ እኔ በጀት የማልሻማው በራሴ ገቢ የማስተዳድረው ለሕዝቤ ነው ግን ከየክልሉ ሰዎች እየፈለሱ ለእነሱ ቤትና ውሃ ማቅረብ ፈተና ሆኖብኛል ክልሎች እየረዱኝ አይደለም ይላል።
ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ፍልሰት አለብኝ ከደቡብ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ይፈልስብኛል። ከተለያየ ክልል እንደዚሁ፣ እና ይሄ አልተቆጠረም ለነዚህ ግን አገልግሎት ስጥ እንባላለን ይላሉ። ይሄ ሁሉ የሚፈታው ሲቆጠር ነው፣ ቁጥር ያስፈልጋል፤ ጊዜው ሲስተካከል ተቆጥሮ መስተካከል አለበት ትክክል ነው። ግን በተለየ መንገድ አንዱን ጠቅሞ አንዱን የሚጎዳ አድርጎ ማሰብ አያስፈልግም። ሁሉም በራሱ መንገድ አንዱ በጥቅሙ ተጎድቻለሁ፤ ሌላው በቁጥር ተጎድቻለሁ ይላል ብዙ ሃሳብ ስላለ ማለት ነው።
ከአፋር ጋር ተያይዞ የተነሳው አንደኛ አፋር ያለው ቁስለኛ እኛ ነን መድሃኒት የምንሰጠው፣ አፋር የራሱ ደሴት የለውም፤ እኛ ነን የምናክመው ይሄ አደገኛ ልምድ ነው፣ ወለጋ ላይ ውጊያ ስላለብኝ ጦርነት ሁሉ ያለው ወለጋ ነው፣ አፋር ውጊያ ስላለብኝ ጦርነት ሁሉ ያለው አፋር ነው አይነት ዝንባሌ ተው፣ ኢትዮጵያ ሁሉ የታመሰ ነው፣ በቁስለኛ የተሞላ ነው። የፌዴራል መንግስት ለእያንዳንዱ ክልል መድሃኒት ያቀርባል፣ እያንዳንዱን ሆስፒታል በሚችለው ድጋፍ ያደርጋል፣ የአፋርን የተለየ የሚያደርገው ነገር የለም።
ኦሮሚያም እንደዚያ አይነት ስላለ። በዚህ ጉዳይ በየፖሊስ ጣቢያው በየእንትኑ ቁስለኛ አለ፤ እኛ ነን የምናግዘው ባለ አቅም። ክልሎች ግን ለማኝ ሆነዋል፣ ገቢ ማሳደግ ልማት ማምጣት ሳይሆን በቃ የሆነ የሚፈስ ነገር፣ ቅድም እንዳነሳሁላችሁ ገቢያችን ሶስት መቶ ምናምን ቢሊየን ነው፣ 309 ቢሊየን አካባቢ፣ ይሄ አብዛኛውን የሚሄደው ክልል ነው። 379 መንገድ ግንባታ አለ ያልኳችሁ እኮ አንድም አዲስ አበባ ውስጥ የለም፣ ሁሉም መንገድ የሚገነባው ክልል ነው። ሆስፒታል ይገነባል፣ ት/ቤት ይገነባል አብዛኛው ክልል ላይ ነው የሚውለው፣ ግማሹ በእኛ ይሰራል። ግማሹ ደግሞ በእነሱ ማለት ነው።
ኢትዮጵያ መቶ ሁለት መቶ ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋታል፣ ከዚህ መቀሌ፣ ከዚህ ባህርዳር፣ ከዚህ አሶሳ፣ ከዚህ ጋምቤላ፣ ከዚህ ሰመራ ሃይዌይ ያስፈልገናል። ባቡር ያስፈልገናል። ሃብቱ ውስን ስለሆነ ነው እንጂ ፍላጎት ስለሌለ አይደለም። ከስር ከስር እየሰራን መሄድ፣ ከስርስር ልማቱ እያደገ ሲሄድ ችግሮች እየተፈቱ እንደሚሄዱ ማሰብ ነው። የኢንፍራስትራክቸር መዛባትን በሚመለከትም እንደተባለው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥናት አጥንቶ በድርጅትና በካቢኔ ሃሳቡ ቀርቧል፣ ያን ታሳቢ አድርገን ከፍተኛ የመንገድ ችግር ያለባቸውን ክልሎች ምላሽ መቶ በመቶ ሰጥተናል።
አንዱ ክስ ያለው አማራ ክልል ነው፤ ሰፊ የመንገድ ስራ ሰርቷል፣ በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ ነው፣ በደቡብ ደግሞ አሉ ኮሪደሮች እንደዚሁ ያልተሰሩ፣ ያለፈውን ለመመለስ ተሞክሯል። አሁንም ግን ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማት ያስፈልጋል። ወደ ደቡብ ምዕራብ አዲሱ ክልል ብትሄዱ እኮ ምን አለ መንገድ እኮ የለም፣ ብዙ ስራ ያስፈልጋል። ዞኖች አንዳንዱ ጋር ወረዳ ላይ አስፋልት የለውም፤ የዞን ከተማም አስፋልት የሌላቸው አሉ። እነዚህን ደረጃ በደረጃ እየመለስን ለመሄድ ውስጥ ውስጡን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ታሳቢ ማድረግ ጥሩ ነው።
ዘንድሮ ድርቅ በሚመለከት የውጪ እርዳታ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ውስን ነው። እንኳን የፌዴራል መንግስት እያንዳንዱ ክልል ረድቷል። ሁሉም ክልሎች ረድተዋል ሱማሌም ቦረናንም፣ አፋርንም። አማራ ክልል ይሄ ሁሉ ጣጣ እያለበት ረድቷል ኦሮሚያ ሄዶ። በእርነሱ እርዳታ ጭምር ነው ድርቁን በተወሰነ ደረጃ ለመቋቋም የሞከርነው።
ታክስ ሊሰበስብ ነው መንግስት የሚያስበው ለተባለው እንኳን ከሞተው ካለውም አልተሰበሰበም። የእኛን አካባቢ ችግር አንስተን እንደ አጠቃላይ አገር የምንመራ ሰዎች የምንናገር ካለን ችግር ነው። በአገር ደረጃ ያለውን ነገር ማየት ጥሩ ነው። እንደዚያ አይነት ግንዛቤ ቢወሰድ መልካም ነው።
አፋር ክልል ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገንብተናል ባለፈው አንድ አመት ተኩል። ያ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለአፋር ክልል የተመደበ አልነበረም። ለሌላ ክልል የተመደበ ነው። ከባንክ ጋር ተነጋግረን አፋር ክልል የማይሰራ ከሆነ ይቅርብን ብለን ነው፤ ወደዚያ የወሰድነው። ለምንድነው አፋር ክልል ለፖርት ቅርብ ነው እዚያ ብናመርት ኤክስፖርት ለማድረግ ይመቻል። ምንም አስቻይ ሁኔታ በሌለበት ፕሮጀክቱን በተለመደው አካባቢ መደርደር ትክክልና አዋጭ አይደለም ተብሎ ከሌላ ክልል ተወስዶ ነው አፋር የተመደበው።
አፋር በመንገድ ስርጭት ጥያቄ ሊያነሳ አይችልም። ከሁሉም ክልሎች ከትግራይ ቀጥሎ ሻል ያለ መንገድ ያለው አፋር ነው። ወደ ኤርታሌ የሚሄደው የአስፓልት መንገድ ላይ የፈጀው ሲሚንቶ ሌላ ሶስት እጥፍ አስፓልት ይሰራል። ይሄን ታውቃላችሁ። እኛ የምንፈልገው ፍትሀዊ ልማት እንዲሰራጭ ነው።
የተወሰነ ሀብት ተጠቅሞ ሌላው እንዳይጎዳ በተለይ እንደ አማራና ኦሮሚያ ያሉ ክልሎች በየአመቱ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲሰበሰብ ከሚያገኙት ገቢ በህጉ ቢገባቸውም እየቀነሱ ለአነስተኛ ክልሎች ይደጉማሉ። ይህን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በመጠየቅ ልታረጋግጡ ትችላላችሁ። ፍፁም ነው አይደለም የሚለው አይደለም። ፍጹምነት የለም ስህተት ሊኖር ይችላል ያንን እያስተካከልን እያረቅን እንሄዳለን።
ህገመንግስቱ በአካታች አገራዊ ውይይት ይታይ ያልነው እኮ ችግር ስላለበት ነው። ህገመንግስቱ ግን መንግስቱ የኃይለስላሴ እንደቀደደው፤ መለስ የመንግስቱን እንደቀደደው አንቀድም። ህጋዊ በሆነ መንገድ ግን እናሻሽለዋለን። የመጣው ሁሉ ቢቀድ ስርዓት አይገነባም። ለዚያ ነው አካታች አገራዊ ውይይት ይደረግና በዚያ ላይ ያላችሁን ሀሳብ አንሱ ተወያዩ ሲባል አንወያይም የሚል አካል ህገመንግስት ይላል። ፌዴሬሽን ላይ ባንዲራ እንዲህ መሆን የለበትም የሚል ኢሹ ያነሳል።
ሁሉም ያገባኛል የሚል ሁሉ ተወያይቶ ከተስማማን በኋላ ህዝብ የሚወስንበት ዘላቂ ነገር መሰነድ ያስፈልጋል። ያ ሲሆን ነው አገር የሚቀጥለው። ለምንፈልገው ነገር ሲሆን ህገመንግስቱ ሪፈር እናደርጋለን፤ ለማንፈልገው ነገር ሲሆን ደግሞ ህገመንግስቱን አንፈልግም ካልን ያስቸግራል፤ አይሆንም።
ለምሳሌ ወልቃይት፤ ወልቃይት በተመለከተ ባለፈው ፓርላማ ላይ በነበረን ዝግ ውይይት አንድ ባንድ አንስቼላችኋለሁ። አሁን እዚህ አላነሳውም። ወልቃይትን በሚመለከት በተደጋጋሚ አቅጣጫ አስቀምጠናል ለክልሉ። ህግ በተከተለ መንገድ ሶልቭ እንዲደረግ። ለምን መወሰን ቀላል ነው።
ከዚያ በኋላ ልጆቻችን እየተባሉ የሚኖሩበትን መንገድ አናድርግ። የፍትህ ጥያቄ ነው የቆየ ጥያቄ ነው። ሁሉም ሰው ህግን ተከትሎ የሚፈታው ጉዳይ ካልሆነ አሁን በደፈናው እንዲህ ነው ብሎ ቢወስን ሁልጊዜ ግጭት ሁልጊዜ መባላት ይፈጠራል። እንደተባለው የተጎዳ ህዝብ የተሰደደ ህዝብ ነው።
ፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው የሚወስነው። ክልሎቹ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባሉ፤ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ይወያያሉ፤ እዚያ ሲወሰን እኛ እናስፈፅማለን። ወልቃይትን በሚመለከት እስካሁን በትግራይ ክልል ስለነበር በጀት ተመድቧል።
አላያችሁም በጀቱን። ህገመንግስታዊ ስለሆነ አምናም ካቻምናም ተመድቦ ነበር። ህገመንግስቱ ለክልሎች መድቡ ይላል። ከተመደበ በኋላ እንዴት እንሰራበታለን ለሚለው በጀት አስተዳደር የሚያየው ጉዳይ ነው።
እኔና እናንተ ግን ትግራይ ችግር ስላለ በጀት አይወሰንም ማለት ግን አንችልም። ቀመሩም አይፈቅድም ህገመንግስቱም አይፈቅድም። አምናም ፀድቆ ነበር ነገር ግን ሊጠቀሙበት አልቻሉም ፈሰስ ተደርጓል። ዘንድሮም ተበጅቷል ችግሩ ከተፈታ የሚጠቀሙበት ይሆናል ካልተፈታ ደግሞ በበጀት አስተዳደር የሚታይ ይሆናል።
እንጂ እኛ እዚህ ሆነን የማንፈልገውን ጉዳይ እያፋለስን ከሄድን ትክክል አይደለም። በጀት በሚመለከት ወልቃይት ላይ ችግር አለ። መደገፍ አለበት ወልቃይት። ግን ትግራይ የባሰ ችግር አለ። የትግራይ በጀት ጉዳይ እንዴት ነው የሚሆነው ለምን አትሉም እናንተ። የትግራይ በጀት ጉዳይ የምናነሳው ከቲፒ ኤል ኤፍ መነፅር አንፃር አይደለም።
የትግራይ በጀት የምናነሳው በሕወሓት መነጽር አይደለም፤ ከትግራይ ሕዝብ አንፃር ነው። ቅድም ለትግራዮች እንዴት ትረዳላችሁ የሚል ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ግን ያው ትቸዋለሁ፤ የተውኩበት ምክንያት፤ እነዚያ በትግራይ ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚፍጨረጨሩ ኃይሎች ካሉ ያው ውጤታቸው እየታየ የሚሄድና ሁሉም ዜጋ ሕዝብ በየአካባቢያቸው የሚያግዛቸው ይሆናል በሚል ነው።
ለምሳሌ የአማራ ክልል ከትግራይ ጋር በነበረው ግጭት ጉዳት ደርሶበታል፤ ግን የአማራ ክልል ከትግራይ ተሰደው የመጡ ሰዎች አቅፎ፣ እያበላ ነው ያለው። ትናንት ተዋግታችሁኛልና አትመጡብኝም አላለም። ኑ ወንድሞቼ፤ ፀቤ ከሕወሓት ጋር ነው፤ ከቸገራችሁ ብሎ በአማራ ክልል ጫፍ ጫፍ የሚያበላቸው ሕዝብና መንግሥት ነው። ሕዝቡ እንደሱ ነው።
እና ወልቃይትን በሚመለከት፤ በበጀት አስተዳደር የሚታይ ነገር ካለ፤ ገንዘብ ሚኒስቴር አምናም አይቷል፤ ዘንድሮም ያያል። በተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ይደረጋል፤ ግን ለማን ተብሎ ይመደባል ለሚለው ነገር የሚጠፋችሁ አይመስለኝምና በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ክልሎች ሥራቸውን ሰርተው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበው፤ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ብንፈጽመው በዘላቂነት ሰላም ሊፈጥር ይችላል በሚል እንጂ የወልቃይት በጀት አንድ ሚሊዮን ሁለት ሚሊዮን እዚህ ቀርቶ እዚያ ቀርቶ ምንም ለውጥ ስለሚያመጣ አይደለም።
ያም ሆኖ ግን በመከላከያ የሚደረግ ድጋፍ እንዳለ የተከበረው ምክር ቤት እንዲገነዘብ ነው። እና በተለየ መንገድ እዚህ አይተን ለመወሰን እንቸገራለን፤ ፌዴሬሽን ተወያይቶ ሕጋዊ መንገድ ሲያስፈጽም ደግሞ እኛ እናስፈጽማለን በሚለው መገንዘብ።
ወልቃይት አካባቢ ኮንሰርን ያደረጋችሁ ሰዎች ሄዳችሁ ምን አቅጣጫ እንደተሰጠ፣ ምን እንደተሰራ፣ ምን እንዳልተሰራ በአካል ብትገመግሙ ጥሩ ነው። እዚህ የሚጠየቅ ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ በርካታ ችግሮች ስላሉ። መሬት ላይ ያለውን ችግር አይተን መፍትሔ ብናደርግ አብዛኛው ነገር መስመር የሚይዝ ይመስለኛል።
በዘላቂነት ግን መፍትሔ ማግኘት አለበት፣ ሕዝቡ የተጎዳ ሕዝብ ነው፤ የተሰበረው መመለስ አለበት ያለአግባብ የተበደለው ቢያንስ በሥርዓት እንዲከበር መደረግ አለበት፤ በልማት የደረሰበት ጉዳት ደግሞ ታሳቢ ተደርጎ እንዲሰራ መደረግ አለበት።
ያም ሆኖ ግን ብዙ ቢፈናቀልም፤ ወልቃይት ውስጥ ብዙ የዴሞክራሲ ጥያቄ ቢኖርም ከመሰረተ ልማት አንፃር ደግሞ ብታዩ አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ተጠቃሚ ምዕራብ ትግራይ ነው። ከ320 ኪሎ ሜትር በላይ ኮንክሪት አስፋልት፣ በቀን ሁለት ሦስት መኪና የማይሄድበት አስፋልት አለ አሁን። ጉዳትም አለ፤ የተሰራም ሥራ አለ። ጉዳቱን ጠግነን፣ የተሰራውን ተጠቅመን እንዴት እናለማዋለን የሚለውን እያዩ መሄድ ጠቃሚ ይሆናል ለማለት ነው አመሰግናለሁ !
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2014