በዓለምሕዝብ ዘንድ ቁጥር አንድ ተወዳጅ ስፖርት እንደሆነ የሚነገርለት እግር ኳስ ተቀባይነቱ ላይ ጥቁር ጥላ እንዲያጠላ የሚያደርጉ ብዙ ፈተናዎች በዙሪያው አሉ። የጨዋታ ማጭበርበር፣ ከአቅም በታች መጫወት፣ መላቀቅ ወይም የጨዋታን ውጤት ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ እንዲለወጥ ማድረግ የዓለም እግር ኳስ ትልቁ ፈተና የሆነው ጉዳይ መገለጫዎች ናቸው። ይህ ፈተና እግር ኳስ ከተጀመረበት ዘመን ጀምሮ የተፈጠረ፣አሁንም ያለና ወደ ፊትም የሚኖር መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።
ከሳምንት በፊት በተጠናቀቀው የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተለይም የመጨረሻ ሳምንት መርሐግብር ሶስት ጨዋታዎች ይህ የእግር ኳስ ፈተና ጎልቶ መታየቱ አሁንም ድረስ መነጋገሪያ ሆኖ ይገኛል። በፕሪሚየር ሊጉ ይህ ቅሌት ጨዋታዎቹ ከነበራቸው አጓጊነት አንጻር የብዙዎችን ትኩረት ስቦ መነጋገሪያ ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ክስተት አይደለም። በዓለም እግር ኳስም ቢሆን በብዙ አጋጣሚዎች ይህ ቅሌት ተደጋግሞ ታይቷል። በዓለምም ይሁን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕዝብ በይፋ የማያውቃቸውና ማንም ያልደረሰባቸው ወይም ተደባብሰው ያለፉ ተመሳሳይ ቅሌቶች ቁጥር ስፍር የላቸውም ። የጨዋታ ማጭበርበር ቅሌቶች የሚፈጸሙበት መንገድ ይለያይ እንጂ በየትኛውም ዓለም የሚፈጠር የስፖርቱ ፈተና ነው። ይሁን እንጂ በታሪክ አጋጣሚ በገሃድ የወጡና ዓለም በአደባባይ የሚያውቃቸው ትልልቅ የጨዋታ ማጭበርበር ቅሌቶች ስፖርቱ ባደገባቸው የአውሮፓ ሀገራት ጭምር ተፈጥረው ታይተዋል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ይህ ቅሌት ተፈጽሟል ተብሎ መነጋገሪያነቱ ሳይበርድ ሰሞኑን ከወደ ሴራሊዮን የተሰማው ዜና ግን “እንዲህም አለ እንዴ” የሚያስብል ሆኗል። የሴራሊዮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን 95 ለ 0 እና 91 ለ1 የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ውጤት ላይ ምርመራ ላይ እንደሚያደርግ የወጣው መረጃ የወቅቱ ትልቅ መነጋገሪያ ነው።
የሴራሊዮን እግር ኳስ ማኅበር 187 ጎሎችን የተቆጠረበትን ሁለት ጨዋታዎች ውጤት እያጣራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በሀገሪቱ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ደረጃ ባለፈው እሁድ በተደረገ ጨዋታ ካሁንላ ሬንጀርስ እና የኮኖው ገልፍ የከተማ ተቀናቃኞቻቸውን በከፍተኛ ልዩነት አሸንፈዋል። የካሁንላ የተሰኘው ቡድን ሉምቤቡ ዩናይትድን 95-0 ሲያሸንፍ፣ ገልፍ የእግር ኳስ ቡድን ኮኪማ ሊባኖስን 91 ለ 1 በማሸነፍ በሴራሊዮን ብቻም ሳይሆን በዓለም እግር ኳስ ታሪክ የተመዘገቡ ከፍተኛ የጨዋታ ውጤቶች ሆነዋል። ይህም ብዙዎችን ያስገረመና ፈገግ ያደረገም ሆኗል።
በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ተጋጣሚዎቻቸውን የተፋ ለሙት ሁለቱ ክለቦች ተመሳሳይ ሰላሳ ሁለት ነጥብ እና ተመሳሳይ የግብ መጠን ስላላቸው በአፍሪካ መድረክ የሚሳተፈውን ለመለየት ሁለቱም ጨዋታቸውን ማሸነፍና የግብ ልዩነታቸውን ማስፋት ነበረባቸው።
ጋልፍ ከ ኮኩማ ሌበነን እና ሌምባቡ ከ ካኑላ ሬንጄርስ ጋር ጨዋታቸውን ለማድረግ ወደ ሜዳ ገቡ። ጋልፍ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጋጣሚው ላይ ለአንድ ደርዘን ሁለት የጎደለው ግብ በማዝነብ 10 ለ 0 እየመራ እረፍት ወጣ። ሌላኛው ጨዋታ ላይ ተቀናቃኙ ክለብ ካኑላ ሬንጄርስ ደግሞ ተጋጣሚውን 2 ለ 0 እየመራ ነበር ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ያመራው። የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ከእረፍት በፊት በርካታ ግቦች በመቆጠራቸው ብዙዎች ጨዋታው ጤናማ እንዳልሆነ ሊጠረጥሩ ይችላሉ። ሁለተኛው ጨዋታ ላይ በመጀመሪያ አጋማሽ የተቆጠሩ ግቦች ግን ፍጹም የሚያስጠረጥሩ አልነበሩም።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደጀመረ ግን ማንም ያልጠረጠረውና ሕልም የሚመስል ለማመን የሚከብድ የግብ ውርጂብኝ በሁለቱም ጨዋታዎች መውረድ ጀመረ።
ከዕረፍት ተመልሰው ሁለተኛውን አጋማሽ ለመፋለም ሲገቡ ተቀናቃኛቸው 10 ለ 0 እየመራ መሆኑን ያወቁት ካኑላዎች ታዲያ በልጠው ለመገኘት አንድ ነገር ዘየዱ። ተጋጣሚያቸውን አነጋግረውም ከዕረፍት በኋላ 93 ግቦችን በተቃራኒያቸው መረብ ላይ አዥጎደጎዱ። ይህንንም የሰሙት ጋልፎች ተጋጣሚያቸውን በተመሳሳይ በማነጋገር ከዕረፍት መልስ 81 ግቦችን አስቆጥረው ጨዋታውን 91 ለ 1 በሆነ ውጤት ማጠናቀቅ ቻሉ።
ከነዚህ ሁለት ጨዋታዎች በአንደኛው ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ሲመራ የቆየው አልቢትር ግቦችን በመቁጠር ሥራ በዝቶበትና ተሰላችቶ ሁለተኛውን ጨዋታ ጊዜ እየመራ መጨረስ አልቻለም። ደክሞት በአራተኛው ዳኛ መተካቱም ከግቦቹ ብዛት በተጨማሪ የጨዋታው ክስተት እንደነበር ተዘግቧል።
የሴራሊዮን እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ቶማስ ዳዲ ብሪማ “እንዲህ ያለው አሳፋሪ ሁኔታ ሳይቀጣ ሲቀር ማየት አንችልም” ብለዋል። በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶች በጨዋታ ማጭበርበር ተጠርጥረው ተሽረዋል።
እነዚህ ለማመን የሚከብዱ ክስተቶች ግን የውጤት ማጭበርበር በአፍሪካ እግር ኳስ ምን ያህል ደረጃ እንደደረሰ በግልጽ የሚያሳይ ሆኗል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 /2014