በአሜሪካ ፖርትላንድ ኦሪገን የሚካሄደው የዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከሳምንት ያልበለጠ ጊዜ ይቀረዋል። ኢትዮጵያን በተለያዩ ርቀቶች በመወከል የሚወዳደሩ ስመ ጥር አትሌቶችም ባለፉት በርካታ ሳምንታት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክና በዓለም ቻምፒዮና ስኬታማ በሆነችባቸው የ5 እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች በኦሪገኑ ቻምፒዮናም ውጤት ታስመዘግብባቸዋለች ተብሎ ከሚጠበቁ ውድድሮች ዋናዎቹ ናቸው። ለዚህም ኢትዮጵያ በርቀቶቹ የብቃታቸው ጣራ ላይ የሚገኙና የዓለም ኮከብ የሆኑ በርካታ አትሌቶች በሁለቱም ጾታ እንዳላት በውድድር አመቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች መታዘብ ተችሏል። እነዚህ ከዋክብት አትሌቶች በኦሪገኑ ቻምፒዮና ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ተመርጠው እየተዘጋጁም ይገኛሉ። የ5 እና 10ሺ ሜትር በተለይም ወንድ አትሌቶች አመራረጥን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ መጀመሪያ የመለመላቸው አትሌቶች ላይ ጥርጣሬዎች የነበሩ ቢሆንም ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው የመጨረሻ ዝርዝር ላይ በርካቶችን ያሳመነ ለውጥ አድርጓል። ይህም እንዳለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ወርቅ የማስመዝገብ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው አትሌቶች ይዛ እነሱን በአግባቡ ባለመጠቀም እንደገጠመው ዓይነት የውጤት ቀውስ እንዳይደገም የነበረውን ስጋት ማስቀረት ችሏል።
በአትሌቲክስ ታሪክ የ10ሺ እና 5ሺ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያ ስኬታማ የምትሆንባቸው ፉክክሮች ብቻ ሳይሆኑ በአትሌቲክስ ባለፉት በርካታ አመታት ገናና ስም እንዲኖራት የአንበሳውን ድርሻ የተወጡ ናቸው። ያ ስኬቷ እንዲቀጥል ለኦሪገኑ ዓለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ ይፋ
በተደረጉ በተለይም የወንዶች 10 እና 5ሺ ሜትር ተሳታፊዎች አትሌቶችን ጉዳይም አሰልጣኞች በጥንቃቄ ተመልክተውት ማሻሻያዎችን እንዳደረጉ ይታመናል።
በርቀቶቹ እየዳበረ የመጣውን የሌሎች አገራት አስፈሪ ተፎካካሪነት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለመግታት አቅሙም ብቃቱም አላቸው። ነገር ግን ይህን አቅም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በነዚህ ርቀቶች እንደሚሳተፉ ይፋ ያደረጋቸው አትሌቶች አስደናቂ ብቃት ያላቸው ቢሆንም ማን በትክክለኛው ርቀት እንዲሮጥ ታስቧል የሚለው ላይ በርካታ ምክኒያታዊ ሙግቶች ይነሳሉ። የትኛው አትሌት በየትኛው ርቀት መሮጥ አለበት የሚለውን የሚወስነው አሰልጣኙ ነው። ለአሰልጣኞች ሙያዊ ነፃነት መስጠት እንደሚገባም አያከራክርም። ነገር ግን እንዳለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ አሰልጣኞች አገርን ዋጋ በሚያስከፍል ደረቅ ሕግና ደንብ ታጥረው ውጤት ሲበላሽ በዝምታ ማለፍ ተገቢ ሊሆን አይችልም። አሰልጣኞች ይህን ስጋት ተመልክተው ተገቢውን ማሻሻያ ሲያደርጉም ማመስገን ባህል ሊሆን ይገባል።
በ5ሺ ሜትር ከተመረጡ አትሌቶች መካከል ወጣቱ በሪሁ አረጋዊ አንዱ ነው። ይህ ድንቅ አትሌት እኤአ በ2018 የታዳጊዎች የዓለም ቻምፒዮና ገና በለጋ ዕድሜው ፈጣን ሰዓት አስመዝግቦ ለአገሩ ሜዳሊያ ካጠለቀበት ጊዜ ጀምሮ በ10ሺ ሜትር ምን ያህል ልዩ ተሰጥኦ እንዳለው አስመስክሯል። በቶኪዮው ኦሊምፒክም በርካታ ጠንካራ አትሌቶች በተሳተፉበት ውድድር በሚደንቅ ብቃትና የቡድን ሥራ ብቸኛ ወርቅ እንዲመዘገብ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። ዘንድሮ ግን በመጀመሪያው ዝርዝር ውስጥ በ5ሺ ሜትር ከሁሉም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሻለ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገቡ በኦሪገኑ ቻምፒዮና በዚሁ ርቀት ብቻ እንዲወዳደር ተመርጦ ነበር። ይህ አትሌት በመጀመሪያው ዝርዝር ውስጥ በ10ሺ ሜትር እንዲወዳደሩ ከተመረጡ አትሌቶች መካከል አንዱ አለመሆኑ ምርጫው ላይ ስጋት አሳድሮ ነበር። በመጨረሻው ምርጫ ግን ይህ አትሌት በ5 እና 10ሺ ሜትር እንደ ኢትዮጵያ ከ1 እስከ 3 ፈጣን ሰዓት ስላለው በሁለቱም እንዲሳተፍ መደረጉ አሰልጣኞች ከስህተታቸው የተማሩበት አንዱ ማሳያ ነው። የዓለም ቻምፒዮና የ5ሺ ሜትር ውድድሮች ታክቲክ የበዛባቸውና የማጣሪያ ፍልሚያም ያላቸው እንደመሆኑ አንድ አትሌት ለውጤት ለመብቃት የተሻለ ልምድ ሊኖረው እንደሚገባ ይታመናል። አንድ አትሌት ፈጣን ሰዓት መሮጡ ብቻ መታሰብ የለበትም። በዚህ ስሌት መሠረት በቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጤት መበላሸቱ መዘንጋት የለበትም። በወቅቱ አትሌት ጌትነት ዋለ በ5ሺ ሜትር የኢትዮጵያ ፈጣን ሰዓት ስለነበረው ለኦሊምፒክ ተመርጦ ማጣሪያውን እንኳን ማለፍ አለመቻሉ በራሱ በቂ ትምህርት ነው። ይህ የተፈጠረው በርቀቱ የተሻለ ልምድና ብቃት ያለው ሰለሞን ባረጋ 10ሺ ሜትርን አሸንፎ በሙሉ የራስ መተማመን በቂ እረፍት ወስዶ በጥሩ ብቃት ላይ እንደሚገኝ እሱን ትቶ በወቅቱ ልምዱም ብቃቱም ያልነበረውን ጌትነትን ማወዳደር ስለተፈለገ ነበር። ይህ ዘንድሮ አለመደገሙ አሰልጣኞችን የሚያስመሰግን ሲሆን ኢትዮጵያም በርቀቱ አስፈሪ ስብስብ እንዲኖራት አድርጓል።
የኦሊምፒክ ባለድሉ ሰለሞን ቶኪዮ ላይ በዚያ የተሳሳተ ስሌትና ውሳኔ ክፉኛ ተበድሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብም ተቀይሟል፣ ተቆጥቷልም። በቶኪዮ 5ሺ ሰለሞን የቀነኒሳን ታሪክ የመድገም አቅም ነበረው፣ ግን የተሳሳተው ስሌት ታሪክ እንዳይሠራ ኢትዮጵያም በአንድ ወርቅ እንድትመለስ አድርጓል። አሁን ግን አሰልጣኞች ሰለሞንን የመካስ ዕድሉን በአግባቡ ተጠቅመዋል። በ5 እና 10ሺ ሜትሮች እንዲወዳደሩ ከተመረጡ አትሌቶች የመጨረሻ ዝርዝር ውስጥ መካተት ችሏል። ሰለሞን ዘንድሮ በሁለቱም ርቀቶች አስደናቂ ብቃት ላይ እንደሚገኝ ማሳየቱ በዓለም ቻምፒዮናው የኦሊምፒክ ቁጭቱን እንዲወጣና ኢትዮጵያም በርቀቶቹ የወርቅ ተስፋዋ ከፍ እንዲል አድርጓል። በተለይም በቅርቡ በተካሄደው የፓሪስ ዳይመንድሊግ በ5ሺ ሜትር የአየር ሁኔታው በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ የዓለም የርቀቱ የሁለት ጊዜ ቻምፒዮን ሙክታር ኢድሪስ እንኳን በውድድሩ መሃል ውሃ ለመጠጣት በተገደደበትና አንዳንዶችም መቋቋም አቅቷቸው ባቋረጡት ከባድ ፍልሚያ ላይ፣ ሰለሞን ብቻውን ከ13 ደቂቃ በታች 12፡56 ሮጦ ማሸነፉ ትልቅ ተስፋ እንዲጣልበት ያደረገ ነበር።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2014