ለአገራችን ኪነጥበብ ዕድገት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። እጅግ ስሙ የናኘ በሥራዎቹም አንቱ የተባለ አርቲስት ‹‹ከወደየት ነህ›› ቢባል ከእነዚህ የጥበብ ቤቶች አንዱን መጥራቱ አይቀርም። ‹‹እዚያ ነው የጥበብ ሀሁን የጀመርኩትና ያደግኩት›› ማለት አይቀሬ ነው። በዜማው የተወደደ በግጥምና እንጉርጉሮው የተደነቀም ድምፃዊ መነሻው ቢጠየቅ እነዚሁ የጥበበኞች ምንጭ ወደነበሩት ቤቶች መጠቆሙ የተለመደ ነው።
ለረጅም አመታት በእነዚህ የጥበብ ቤቶች ብዙዎች ኪነጥበባዊ ጥማታቸውን ቆርጠዋል። ኪናዊ አምሮታቸውን ተወጥተዋል። አንቱ መሰኘት፤ በዘርፉ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠርና ዝናን ማትረፍም ችለዋል። የኪነጥበብ አፍቃሪውም ተጋፍቶ ከጥበብ ማዕዳቸው ተቋድሷል። ተሰልፎ የተደገሰውን ኪነ ጥበባዊ ድግስ ተካፍሏል። በጥበብ ቤቶቹ አገር ፍቅር ቴአትር፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፤ ራስ ቴአትር እና ሌሎችም ቴአትር ቤቶች ለዘመናት ኪናዊ ሁነት ሲበጅ፣ ኪነት ሲገን፣ ጥበብ ሲንቆረቆር ኖሯል።
የጥበብ ቤቶቹ በአገር ደረጃ ስመጥር የሆኑ የኪነጥበብ ባለሙያዎች አፍርተዋል። በሙዚቃ ቲያትርና መሰል የሥነፅሑፍ ዘርፎች ውስጥ የሚሳተፉ አያሌ ከያኒያን “ቤቴ” እያሉ ይጠርዋቸዋል። ቀደም ባሉት አመታት በተመልካች ተጨናንቀው እንዳልነበር ዛሬ ላይ ከነበሩበት ፍፁም በተለየ መልኩ ይገኛሉ። ይህንን ገፅታቸው ለመቀየርና በፊት የተላበሱትን ግርማ ሞገስ ለማላበስ ብሎም አገልግሎት አሰጣጣቸውና ገፅታቸው እጅግ ባማረ መልኩ ለማነፅ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር ቤት ግንባታ ያጠናቀቀ ሲሆን እንዲሁም ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ሕፃናትና ወጣቶችን ቴአትር ቤትን ግንባታ እያጠናቀቀ እንደሆነ ገልጿል። ከእነዚህ መሀል የአፍሪካ የመጀመሪያው ቴአትር ቤት አገር ፍቅር ታድሶና በተሻለ መልክ ተደራጅቶ ሥራውን ለመጀመር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ሥራውን ሳያቆም ጎን ለጎን የቴአትር ቤቱን ሁለንተናዊ ገፅታ በመታደስ ላይ ይገኛል።
ለዚህም ሥራው በመፋጠን ላይ ይገኛል። ሌላኛውና በመዲናችን ከሚገኙ አንጋፋ ቴአትር ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው በኢትዮጵያ የጥበብ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ቴአትር ቤት ራስ ቴአትር ለበርካታ አመታት ፈርሶ አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቷል። ስመ ጥርና በሙያቸው አንቱታን ያተረፉ በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለአገር ያበረከተው የራስ ቴአትር በቅርቡ ቀን ሊወጣለት መቃረቡ ታውጇል።
ይህ ለዘመናት የኪነጥበብ ሥራዎችን ለሕዝብ እያቀረበ ቆይቶ በእርጅና ምክንያት የፈራረሰው የጥበብ ቤት በፊት ከነበረው ገፅታው በተሻለ ሁናቴ ለማስገኘትና የጥበብ ቤትነቱን በሚመጥን ዲዛይን ለማዋቀር በአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ሰኔ 25/2014 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት ሥራውን ጀምሯል። በግንባታ መሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ላይ ታዋቂዎቹ አንጋፋ የኪነጥበብ ሰዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ አገር ግንባታ ውጣ ውረድ ውስጥ ትልቅ ዋጋ የከፈሉ አርቲስቶች ተገኝተዋል።
በክብር እንግድነት ተገኝተው የግንባታ መሠረተ ድንጋዩን ያኖሩት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስተዳደሩ ለኪነጥበብ ሥራዎች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥና ለዚህም እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ትልቅ ምስክር መሆናቸውን ጠቁመዋል። ‹‹ለኪነጥበቡ ልዩ ትኩረት በመስጠት በመስራት ላይ እንገኛለን›› ያሉት ከንቲባዋ በከተማዋ 10 አምፊ ቴአትሮችን በማስገንባት ላይ መሆኑንና አንዳንዶቹ መጠናቀቃቸውን፣ በሌላ በኩልም የማዘጋጃ ቤቱ የባህል አዳራሽ ባማረ መልኩ የተገነባ መሆኑን አንስተዋል።
ራስ ቴአትር ብዙ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ያፈራ ቤት እንደመሆኑ ደረጃውን የሚመጥ ግንባታ ለማካሄድ እንደታሰበና በዚህም የመጀመሪያውን አዲስ ቴአትር ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ እንዳስቀመጡ ጠቁመዋል። ‹‹ቴአትር ቤቱ ባማረ መልኩ ተገንብቶ ለኪነጥበብ ባለሙያውና ለሕዝቡ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ይደረጋል›› ብለዋል። ጥበብ ትውልድን በመቅረፅና በመገንባት ትልቅ ሚና ስላላት አሁንም ትኩረት ሰጥተን መሥራታችንን እንቀጥላለን በማለት የከተማ አስተዳደሩ ለኪነጥበብ እየሰጠ ያለውን ዋጋ አንስተዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ለኪነጥበብ ባለሙያው መልዕክታቸው ያስተላለፉት ከንቲባዋ ‹‹እናንተ ጥበባችሁን ተጠቅማችሁ አገር ግንባታ፣ ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ላይ በርትታችሁ ስሩ›› ብለዋል። በዚህ ለዘመናት የኪነጥበብ ባለሙያዎች እያፈራ ቆይቶ በፈረሰ ቴአትር ቤት ላይ በተሻለ ዲዛይንና ምቹ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖረው ተደርጎ በሚታነፀው ሕንፃ መሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የቀድሞ የቴአትር ቤቱ ባልደረቦች ባዩት መደሰታቸውን ገልፀዋል።
ቴአትር ቤቱ አገልግሎት ከመስጠት ተቋርጦና ለብዙ አመታት ፈርሶ በማየታቸው እጅጉን ያዝጉ እንደነበረም አስተያየት ሰጥተዋል። ቴአትር ቤቱ በፊት በነበሩት ሥራዎች የሌሎች ቴአትር ቤቶች ሥራ በሙሉ በተሻለ መልኩ የሚያቀርብና ሌሎች በከተማዋ ውስጥ የነበሩ ቴአትር ቤቶችን ወጪን በመደጎምና በመሸፈን ጭምር ለቴአትር እድገቱ ትልቅ አስተዋፅዖ የነበረው ቴአትር ቤት እንደነበር የገለፀው ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሐንስ ነው።
‹‹ታላቅ የሙዚቃና የቴአትር ባለሙያዎች ያፈራ እጅጉን ትልቅ አስተዋፅዖ የነበረው ቴአትር ቤት ነው፤ በመሆኑም ቤቱ የተሻለ ሆኖ ሊሠራ ይገባል፣ ቤቱ ያሳደገኝ እንደመሆኑ ብዙ ትዝታዎች አሉኝ›› ያለው ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሐንስ ከፈረሰ በኋላ በአካባቢው ማለፍ እንደማይወድና አሁን ለመሥራት መታቀዱ ጥሩ መሆኑንና መንግሥት ቃሉን ጠብቆ ግንባታውን ጀምሮ እንዲጨርሰው አደራውን አስተላልፏል። ‹‹ራስ ቴአትር ለብዙዎች የጥበብ ትምህርት ቤት ነው›› ያለው ፀሐዬ፤ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ታላላቅ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ያፈራ ቤት ወደፊት በተሻለ ገፅታው ማግኘት እንደሚፈልግ ተስፋውን ገልጿል።
የራስ ቴአትር ባልደረቦች ለኪነጥበብ ያላቸው ፍቅርና አንድነት እጅግ የሚያስቀና እንደነበር የገለፀው ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሐንስ ይህ አንድነትና ፍቅር ዛሬ ድረስ እንደቀጠለና ባለሙያዎቹ በተለያየ መንገድ እየተገናኙ ሥራዎችን እንደሚሠሩና ማህበራዊ ግንኙነታቸውም እንዳስቀጠሉ ይገልፃል። አርቲስት ሙሉ ገበየሁ በበኩሉ ራስ ቴአትር ሲመሠረት ጀምሮ ቤቱን በማስተካከልና ለቴአትር ምቹ በማድረግ እንደተሳተፈ ገልጾ ቤቱ በኪነጥበብ ባለሙያ እጅጉን የገነኑና ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ትልቅ አበርክቶ ያላቸው ባለሙያዎች ያፈራ እንደነበር ያስታውሳል።
ቤቱ ከመፍረሱ በፊት በተለያየ የኪነጥበብ ሥራዎቹ አገራዊ ጉዳይ በማንሳት ኅብረተሰቡ አንድነቱ እንዲጠነክርና አገራዊ ፍቅሩን ያዳብር ዘንድ ትልልቅ ሥራዎችን ሠርቷል። ባለሙያዎቹም በመከባበር መንፈስ ለኪነጥበቡ እድገት በጋራ በመስራት የሚታወቁ እንደነበሩ የገለፀው አርቲስት ሙሉ ገበየሁ፤የቴአትር ቤቱ ባልደረቦች ለሥራቸው የነበራቸው ፍቅርና በጋራ የመሥራት ወኔና ሙያዊ ፍቅራቸው ለሌሎች ቴአትር ቤቶችም ጭምር አርዓያ ተደርጎ ይታይ እንደነበር ያስታውሳል።
ለአመታት ፈርሶ ያለምንም ሥራ መቆየቱ የሚያስቆጭ እንደነበረና አሁን ላይ መሠረት ተጥሎ የግንባታ ሥራው መጀመሩ በማየቱ እጅግ መደሰቱን ይገልፃል። አርቲስት ሙሉ ወደፊት እንደከዚህ በፊቱ ጉምቱ ሞያተኞች በማፍራት ለአገሪቱ ኪነጥበብ የራሱ የሆነ ጉልህ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳለው ያስረዳል። የቀድሞ የራስ ቴአትር ባልደረባ የነበረው አርቲስት ኤልያስ ተባባል በበኩሉ ራስ ቴአትር ለብዙዎች የጥበብ ቤት መሆኑና በሕይወት ዘመኑ በሙዚቃ ሥራው ካሳለፋቸው ውብ ቆይታዎች የራስ ቴአትር ቤት የተለየ እንደነበርና እዚያ ብዙ ተምሮ እንደነበር ከባልደረቦቹም ጋር የነበረው ትስስር አስደናቂ መሆኑን ያነሳል።
አርቲስት እንቁስላሴ ወርቃገኘሁ በበኩሉ ቴአትር ቤቱ እጅግ በጣም ብዙ የጥበብ ባለሙያዎችን ያፈራና ለኢትዮጵያ ኪነጥበብ እድገት ውለታ የዋለ እንደነበር ጠቅሶ እሱና ባልደረቦቹ በቴአትር ቤቱ ውስጥ ለኪነጥበብ እድገት የላቀ ሥራ እንደሠሩና ቤቱ ለኪነጥበብ እድገት ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ያስታውሳል። አሁን ላይ በኪነጥበብ ዘርፍ የሚሳተፉ ወጣቶች ቀድሞ በራስ ቴአትር ቤት ይሳተፉ የነበሩ አርቲስቶች ሥራ ዲስፕሊን ቢከተሉና አብሮነታቸው ከዚያ ቴአትር ቤት ባለሙያዎች ቢማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልፆ፤ በራስ ቴአትር ቤት ውስጥ በሥራ በቆየባቸው አመታት ስለጥበብ ብዙ ተምሮ ያንን ኪነጥበባዊ እውቀትና ችሎታ ለሌሎች ለማውረስ ዕድል ገጥሞት እንደነበረ ያስታውሳል።
አርቲስት ደበሽ ተመስገን በራስ ቴአትር ባልደረባነት ለአመታት ተሳትፏል። በጥበብ ቤቱ ውስጥ ኪነጥበብን ተምሮና እራሱን ለሕዝብ እንዳስተዋወቀ በዚህም ቤቱን እጅግ እንደሚወደውና ትዝታው ሁሌም አብሮት እንደሆነ ገልፆ አሁን ላይ በአዲስ መልክ ሊታነፅ መታቀዱ መስማቱ አንዳች ተስፋ በውስጡ እንደፈነጠቀና የተሻለ ተደርጎ ተሠርቶ ማየት እንደሚመኝ ገልጿል።
በራስ ቴአትር ቆይታው አብሮነትን፣ ሙያዊ ፍቅርና የአገራዊ ስሜት እንደተጋባበትና ወደፊት ቤቱ ተሠርቶ በተሻለ ገጽታና በተሻሉ የጥበብ ሥራዎች እንደሚያየው ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጿል። በአገር ደረጃ እድገቱ የጅማሮው ያህል እንዳልሆነ የሚነገርለት የቴአትር ዘርፍ ብዙ መሰናክሎችን እያለፈ መቆየቱና ለቴአትር ምቹ አውድ መታጣቱ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ደጋግመው ይገልፃሉ። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ በአዲስ አበባ መስተዳድር ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተሠሩ ያሉ ለቴአትር ጥበብ ብሎም ለአጠቃላይ ኪነጥበባዊ ጉዳይ ማደግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባ መሆኑን መጠቆም እንወዳለን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2014