አጓጊ ፉክክር ያስተናገደው የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ አጀማመሩ ፍጻሜው አላማረም። በ30ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ሶስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ሲካሄዱ የተመዘገቡ ውጤቶች ክለቦች ‹‹ከአቅም በታች ተጫውተዋል›› በሚል እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ።
ከሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተፋልሞ 4ለ0 የተሸነፈው አዲስ አበባ ከተማ ከሊጉ መውረዱን ተከትሎ በተመሳሳይ ሰዓት በተካሄደው የፋሲል ከነማና ድሬዳዋ ከተማ የጨዋታ ውጤት ላይ ቅሬታውን እያቀረበ ይገኛል። በሌላ ወገንም አዲስ አበባ ከተማ ከአቅም በታች ተጫውቷል በሚል ቅሬታዎች ይቀርባሉ።
ይህንን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ ሆቴል መግለጫ የሰጠው አዲስ አበባ ከተማ ከሊጉ የወረደው ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ መሆኑን በመግለጽ ጨዋታው እንዲመረመርለት ቅሬታውን አቅርቧል። አዲስ አበባ ከተማ ራሱ ከአቅም በታች ተጫውቷል በሚል ለሚቀርብበት ወቀሳም ማስተባበያ ሰጥቷል።
‹‹በኛ ግምገማ በመጨረሻ ጨዋታ ላይ በርካታ ክለቦች በጨዋታ ማጭበርበሩ ላይ ተሳትፈዋል፣ የሐዋሳ ከተማና የአዳማ ከተማ ጨዋታም የዚሁ የጨዋታ ማጭበርበር አካል ነው›› ያሉት የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እንዲሁም የክለቡ የቦርድ ጸሐፊ አቶ ዳዊት ትርፉ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፍትሐዊ ውሳኔ ካልተሰጠው ምን አልባት በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚኖረው ተሳትፎ ሊያበቃ እንደሚችል አሳስበዋል።
አዲስ አበባ ከተማ እግርኳሳዊ ባልሆነ መንገድ ከሊጉ በመውረዱና ይህን አቅጣጫ ለማስቀየስ ሲባልም አዲስ አበባ ለጊዮርጊስ ለቋል በሚል የሚደርስበት ወቀሳ እንዳሳዘናቸውም አቶ ዳዊት ተናግረዋል። ‹‹የመጨረሻ ጨዋታ ከመካሄዱ ከሁለት ቀን በፊት ጨዋታው በደንብ ይታይልን በሚል ለሊግ ኩባንያውና ለፌዴሬሽኑ አሳውቀናል። ክለባችን እንዲወርድ መታሰቡንም ሰምተናል፣ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረንም ጨዋታ ብናሸንፍ አንድም ሰው በሕይወት አይተርፍም፣ ለአዲስ አበባ ክለቦች ልትለቁ በጠረጴዛ ላይ ተወያይታችሁ ነው የመጣችሁት ተብለን ዛቻ ሲሰጠንም ነበር፣ የባህርዳር የወልቂጤና የፋሲል ከነማ ደጋፊና አመራሮች ዛቻ ሲገርመን ነበር፣ ስም አልጠቅስም አታግባና አታሸንፉና ደቡብ አፍሪካ ይናፍቅሃል የሚሉ ደጋፊና አመራር ማየት ያሳዝናል›› ሲሉ አቶ ዳዊት የሂደቱን ጅማሮ ገልጸዋል።
ከዳኛ ምደባ ጀምሮ ክለቡ ጫና እንደነበረበት ያስታወሱት አቶ ዳዊት ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ መደራደር ቢፈልግ ከክለቦች ጋር መደራደር እንችል ነበር፣ ይህን ለማድረግ ግን አናስብም ለወደፊት አይታሰብም፣ በፌዴሬሽኑ 33 ድምጽ ያላቸው ክለቦች አዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው፣ ይህን ለሀገሩ ስፖርት ትልቅ ድርሻ ያበረከተ ከተማ ለመጣል የተደረገው ሂደት አሳዝኖናል›› ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ዳዊት አክለውም ከፌዴሬሽኑና ከአወዳዳሪው አካል ፍትሕ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ያ የማይሆን ከሆነ በርግጠኝነት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፍትሕ ሲሉ እስከ ዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት እንደሚያቀኑ ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ለጊዮርጊስ ለቋል የሚለውን ወቀሳ በተመለከተም አሰልጣኙ ጳውሎስ ጌታቸው በሰጡት ማብራሪያ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾችና አባላት ክለቡን ከመውረድ ከታደጉት የመሬትና ሌሎች አርኪ የሆኑ ጉርሻዎች ተዘጋጅቶላቸው ነበር፣ ካልወረድን የጋራ መኖሪያ ቤትና ተጨማሪ ደመወዝ ከተማ አስተዳደሩ ቃል ገብቶልን እንዴት ለጊዮርጊስ እንለቃለን›› በማለት አስተባብለዋል፡፡
የክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ታከለ በበኩላቸው፣ ለክለቡ ከፍተኛ በጀት በከተማ አስተዳደሩ መመደቡን ገልፀው፣ ከሁለትና ከሶስት ቀናት በፊት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ አሉባልታዎች ቡድኑን በስነልቦና እንዳይጎዳ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንዲመራ ቢያቀርቡም ወቅታዊ ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ቅሬታውን ካቀረበባቸው ክለቦች አንዱ የሆነው ፋሲል ከነማ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ብርሃኑ ‹‹በድሬዳዋ ከተማ መሸነፋችን እኛም ያልፈለግነው ነው እንጂ ታስቦበት የተደረገ ነገር እንዳልሆነ በንፁህ ልብና በሐቅ የኢትዮጵያን እግርኳስ ለሚደግፍ የስፖርት ቤተሰብ መግለፅ እንፈልጋለን›› በማለት መናገራቸው ከቀናት በፊት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክስዮን ማኅበር የውድድርና ሥነ ሥርዓት ሰብሳቢ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ ‹‹ይህን ድርጊት የፈፀሙና የእግርኳስ ቤተሰቡን ያሳዘኑ ክለቦች ላይ በሚቀርበው ሪፖርት ልክ እርምጃ እንወስዳለን ብለን እናስባለን፣ የተፈጠረው ክስተት በእውነቱ የእግርኳስ ቤተሰቡን ያሳዘነ ነው፤ እኛም እንደ አወዳዳሪ አካል ያዘንበት ነው፣ የጥቂት ክለብ ደጋፊዎች የእግርኳስ ድጋፍ ምን ማለት እንደሆነ እየገባቸው ያለ አይመስለኝም፣ በአንዳንድ ተፅዕኖዎች ለተወሰነ ክለቦች አድቫንቴጅ መስጠትን የሚያሳዩ ነገሮች ተከስተዋል፣ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ እስካልሰረፀ ድረስ አሁን የተከናወነውን ነገር በቅጣትና በማስተማር የሚመለስ መስሎ አይታየንም›› በማለት ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው ጉዳዩ ተጣርቶ ፌዴሬሽኑ እርምጃ የማይወሰድበት ወይንም ህጋዊ ነገር የማይደረግበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድርና ሥነሥርዓት ኮሚቴ በ30ኛ ሳምንት የሀዋሳ ከተማና የአዳማ ከተማ፣ የድሬዳዋ ከተማና የፋሲል ከነማ እንዲሁም የቅዱስጊዮርጊስና የአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ የሚመለከታቸውን አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞችና ኮሚሽነሮችን በዛሬው እለት በተለያየ ሰዓት ለማናገር ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29 /2014