ይህ ወቅት የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዓይንና ልብ ወደ አንድ ስፍራ የሚያተኩርበት ነው።ሃገራቸውን ማስጠራትና ብቃታቸውን ማስመስከር የሚፈልጉ አትሌቶች ህልማቸው የሚፈታበት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሊካሄድ 10ቀናት ብቻ ይቀሩታል።ቻምፒዮናው በአሜሪካዋ ኦሪገን አዘጋጅነት ለ18ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከተማዋም ሆነች የውድድሩ ተሳታፊዎች ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ።
በተለያዩ ርቀቶች አትሌቶቿን በውድድሩ ላይ የምታካፍለው ኢትዮጵያም ሶስት ሳምንታትን አስቀድማ የጀመረችውን ዝግጅት ወደማጠቃለሉ እየገባች ትገኛለች።ከ800 ሜትር ጀምሮ በ1ሺ500 ሜትር፣ በ3ሺ ሜትር መሰናክል፣ በ5ሺ ሜትር፣ በ10ሺ ሜትር እንዲሁም በማራቶን በሁለቱም ጾታ የዓለም አትሌቲክስን መምረጫ መስፈርት የሚያሟሉ ከ43 ያላነሱ አትሌቶች ዝግጅት ላይ ይገኛሉ።13 አሰልጣኞች እንዲሁም 5 የህክምናና የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችም በቡድኑ ተካተው ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ዝግጅቱም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መም፣ በጂምናዚየም፣ በጫካ እንዲሁም ሌሎች ስፍራዎች ላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል።የቡድኑ አባላትም በቻምፒዮናው ስኬትን አስመዝግበው የሃገራቸውን ስም ለማስጠራት ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።የ800 ሜትር አትሌቷና በዚህ ውድድር ሃገሯን የምትወክለው ሃብታም ዓለሙ፤ ዝግጅቱ በክረምት እየተደረገ ቢሆንም ያን ያህል አስቸጋሪ አለመሆኑን ትጠቁማለች።ዝግጅቱ በመልካም ሁኔታ የቀጠለ ቢሆንም በውድድሩ ላይ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል በሚል ከወዲሁ እንደ ስጋት የሚነሳው ውድድሩ የሚካሄድበት አሜሪካ ለጉዞ ረጅም ርቀት መሆኑ ነው።
አትሌት አብርሃም ስሜ በ3ሺ ሜትር መሰናክል ቡድን ውስጥ በተጠባባቂነት የተያዘ ሲሆን፤ ዝግጅቱ እንደ ሌላው ጊዜ ረጅም ባይሆንም በመልካም ሁኔታ እንደቀጠለ ይገልጻል።ይህም በውድደሩ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚረዳቸው ነው።በዚህ ርቀት ኬንያዊያን አትሌቶች በተሻለ ስኬት የሚታወቁ ቢሆንም በቡድኑ ውስጥ ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች በመካተታቸው የውድድሩ የበላይነት በኢትዮጵያዊያን እጅ ይገባል የሚል ተስፋ እንዳለውም አትሌቱ ጠቁሟል።
የቡድኑ አባላት በቀረው ጥቂት ጊዜ ለዓለም ቻምፒዮናው ስኬታማ ሊያደርግ የሚችል ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ነው የሚገልጹት።ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ውድድሮች በተለይ ዝናን ያተረፈችበት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀት ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት እየመሩ ያሉት ኮማንደር ሁሴን ሽቦም ይንኑ ሃሳብ ይጋራሉ።ለዚህ ውድድር በሃገር ውስጥ የተለያዩ ውድድሮችን ከማድረግ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃም በዳይመንድ ሊጎች እና የማጣሪያ ውድድሮች ተሳታፊ በማድረግ በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያመላክታሉ።ብሄራዊ ቡድኑ ተሰባስቦ ሰኔ 13/2014ዓም ሆቴል ከገባበት አንስቶ መልካም የሚባል ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል።በስነልቦናም ሆነ በአካል ወቅታዊና ሳይንሳዊ ስልጠና ለአትሌቶች በመስጠት ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን እየተሰራ ነው።
በኢትዮጵያ አሁን የክረምት ወቅት በመሆኑ ቡድኑ ዝግጅቱን የሚያደርገው ዝናብን ጠብቆ ነው።ውድድሩ በሚካሄድበት አሜሪካ ደግሞ አሁን ሞቃታማ ወቅት ነው።በመሆኑም ይህ የአየር ሁኔታ መለያየት እንዲሁም በኢትዮጵያ ቀን በአሜሪካ ደግሞ ማታ መሆኑ እንደ ስጋት ሊነሳ ቢችልም፤ ዝግጅቱ ግን ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ነው።ሌላው አትሌቶች በዳመንድ ሊግ እንዲሁም በሰዓት ማሟያ ውድድሩ ምክንያት በአጭር ጊዜ ውስጥ በተከታታይ በመሮጣቸው ኃይላቸውን በከፍተኛ ሁኔታ አውጥተው ተጠቅመዋል።የማገገሚያ ጊዜም አለማግኘታቸውም እንደ ተጽእኖ ሊነሳ የሚችል ነው።በመሆኑም ወደነበሩበት በመመለስ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ውድድር ተኮር ስልጠና ላይ ማተኮራቸውንም አሰልጣኙ ያስረዳሉ።
የአንድ አሰልጣኝ ብቃት አትሌቶችን ለውጤት ማብቃት ብቻም ሳይሆን ጤንነታቸውን ጠብቆ መቆየትም ነው።በመሆኑም እርሳቸው በሚያሰለጥኑት ርቀት የሚገኙ አትሌቶች በሙሉ ጤንነት ትኩረታቸውን በዝግጅታቸው ላይ አድርገዋል።በመሆኑም እንደተለመደው ጥሩ ውጤት ይመዘገባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ነው አሰልጣኙ የሚገልጹት።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014