የጋዜጠኛ ዘላለም መሉ የመጀመሪያ ስራ የሆነውን “ብር አዳዩ መሪ” መጽሐፍን በድጋሚ እያነበብኩ ነበር። መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ አዕምሮዬ አንድ ሃሳብ ማውጣት ማውረድ ጀመረ። ሐምሌ 27 ቀን 2010ዓ.ም ጂግጂጋ ከተማ ላይ የነበረውን ጭንቅ ተመልሼ እንዳስብ አድርጎኛል። የክልሉ አመራሮች አቅደው ‘ሄጎ’ የተባለ ገዳይ ቡድን አደራጅተው ሃይማኖትና ብሔራቸው ተለይቶ የተጨፈጨፉት ንጹሃን ሁናቴን አስታወሰኝ።
በወቅቱ በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂግጂጋን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የነበረው እንቅስቃሴ ክልሉ ዳግም ወደ ሰላም ይመለሳል ለማለት የሚያስደፍር አልነበረም። ነገር ግን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ በወሰደው አፋጣኝ እርምጃ ትኩሳቱ ሊበርድ ችሏል። አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ደግሞ ነገሮች ሙሉ መልካቸውን ቀይረዋል።
ነሐሴ 2010 ዓ.ም ሶማሌ ክልልን ለበርካታ ዓመታት በርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የነበሩትን አብዲ ሙሐመድ ኡመርን የተኩት አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ፤ ጂግጂጋ ዳግም የሰላም አየር ይነፍስባት ይሆን? የተባለላትን ከተማ ታሪክ ቀየሩ። በአጭር ጊዜ ክልሉ ከስጋት ቀታናነት ወደ ሰላም እንዲሸጋገር አደረጉ።
ለዚህ ደግሞ የክልሉ መንግስት ከምንም በፊት ሰላም ይቅደም በሚል ተጨባጭ ሥራዎችን ማከናወን ችለዋል። ለሰላም ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ህዝብም በተግባር ተክሷል። በአሁኑ ወቅት በሱማሌ ክልል ዜጎች በሃይማኖታቸውም ሆነ በብሄራቸው ሳይሸማቀቁ በነጻነት የእለት ተለት እንቅስቃሴያቸውን ከመተግበርም በላይ በነጻነት ሃሳባቸውን መግለጽ እንዲችሉ ተደርጓል። በውጤት ደረጃ ሲለካም ተጨባጭ ለውጥ ተገኝቷል።
እዚህ ጋር የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትና አስተዳደራቸው በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የሰሩት አኩሪ ሥራን የመንግስት ቀዳሚ ተግባራት ምን መሆን ይገባቸዋል ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን፣ የፖለቲካ ሳይንስና የህግ ሊቃውንት ከሚያቀርቧቸው ሃሳቦች ጋር የሚጣጣም ነው። ከዚህ ውስጥ ቶማስ ሆብስ የተባለው ሊቅ ሌዋታን (Leviathan) በሚል ርእስ ባሰናዳው የፖለቲካ ፍልስፍና ጽሑፉ፤ “ያለ መንግስት – የማያቋርጥ ሰላም፣ ያለ መንግስት – ህግ እና ስርዓትን ማስጠበቅ፣ ያለ መንግስት – ዜጎችን ከእርስ በርስ እና ከውጭ ጠላቶች መጠበቅ” እንደማይቻል ያስቀምጣል።
ክሌር አንደርሰን የተባለ ሌላ ጸሐፊ ደግሞ “ማንኛውም መንግስት የህዝቡን ደህንነት መጠበቅ፣ መሰረተ ልማት መዘርጋት እና የህዝቡን ገጽታ በመገንባት ዙሪያ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይጠበቅበታል” ሲል የቶማስን ሃሳብ ያጠናክራል። በዚህ ጸሐፊ እይታ የአንድ መንግስት ዋነኝ ኃላፊነት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከጥቃት መጠበቅ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቶ ይናገራል።
ከሊቃውንቱ እሳቤ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ከተገነዘብን፤ የሶማሌ ክልልን ከስጋት ቀጣናነት ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ያሻገሩትን ሰው አለማድነቅ እንዴት ይቻላል?!
በሶማሌ ክልል ውስጥ የሚፈጠረው ሰላምና መረጋጋት እንደ ሀገር ካለው ጥቅም ባለፈ ለቀጣናው መሰረታዊ መፍትሄን በማምጣት የአፍሪካ ቀንድ አገራትም እንዲቀራረቡና እንዲረጋጉ የሚያደርግ ጭምር መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ደረጃ ወሳኝ የሆነውን ክልል ከስጋት ወደ ሰላም ቀጣና ለመቀየር እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የነበሩ ቢሆንም፤ በክልሉ ጠንካራ የመንግስት መዋቅር በመዘርጋት አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ተችሏል። ይህም ክልሉን ሁሉም ዜጎች በአንድ መነጽር የሚታይበት አድርጎታል።
በሶማሌ ክልል ከለውጡ በኋላ አስተማማኝ ሰላም በመፍጠር የተገኘውን ድል በሁሉም ክልሎች ቢደገም ስል አስባለሁ። በእርግጥ በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግስቶች በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ አይካድም። ይሄንን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ ባለሁበት ቅጽበት እራሱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በኦሮሚያ ክልል በንጹሃን ላይ ጭፍጨፋ የፈጸሙ የሽብር ቡድኖች ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን እያብራሩ ነበር።
የመንግስት ጥረትና ድካም የማይካድ ቢሆንም፤ የክልል መስተዳድሮች ከሶማሌ ክልል መንግስት እና ከክልሉ ፕሬዚዳንት ብዙ ሊማሩ ይገባል። ክልሎች ወደ ምስራቅ መመልከት ልምድ መቅሰም እንደሚጠበቅባታ አስባለሁ፤ አምናለሁም። በቀናነት በመማማር ፈተና የሆኑብንን ችግሮች በመፍታት ወደ አሰብንበት መድረስ እንችላለን።
በቤኒሻንጉል፣ በአማራ ሆነ በሌሎች ክልሎች ዜጎች ከስጋት በጸዳ መልኩ መንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን ሁኔታ ለመፍጠር ከሶማሌ ክልል ተሞክሮ ብዙ መማር እንደሚችል እገምታለሁ። በእርግጥም በእነዚህ ክልሎች የሚወሰዱ የህግ ማስከበር ስራዎች በዘላቂነት የመፍትሄ ምንጭ እንዲሆን የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው።
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ በአሸባሪዎች ጥምረት እየተፈጸሙ የሚገኙ አሰቃቂ የሰላማዊ ሰዎች ግድያዎች በቀጣይ ሊደገሙ አይገባም። በተለይ ኦሮሚያ፣ አማራና ቤኒሻንጉል ክልሎች ህግና ሥርዓትን በማስከበር የዜጎች በሰላም የመኖር ተቀዳሚውን የመንግስትነት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል። አሁን በክልሎቹ ዘላቂ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርአት መፍጠር ውዴታ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነ አምኖ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ የግድ ይላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተናገሩት አንድ ንግግር ነበር። “የአማራ ክልል እናቶች ማታ ማታ በሚሰማው የጥይት ድምጽ መተኛት አይችሉም ነበር። በክልሉ በተወሰደው የህግ ማስከበር ስራዎች የአማራ እናቶች የጥይት ድምጽ እንዳይሰሙ አድርጓል”። ይህ አይነቱ ውጤት በኦሮሚያ ክልል እንዲመጣ እሻለሁ።
የኦሮሞ እናቶች የጥይት ድምጽ እንዳይሰሙ ማድረግ ያስፈልጋል። ባለፉት አራት ዓመታት በወለጋ የሚገኙ እናቶች እንባን ሰላምን በማስፈን ማበስ፤ በቤኒሻንጉል በግፍ የሚፈሰውን የዜጎችን ደም ማስቆም ያስፈልጋል። መንግስት የግድ ይህን ማድረግ ያለበት በሁለት ምክንያቶች ነው።
የመጀመሪያው መንግስት ህግና ሥርዓትን የማስከበር ሥራው ወቅታዊ ጉዳይ ሳይሆን የሁልጊዜ ሥራው በመሆኑ ነው፤ በሁለተኛው ደግሞ በክልሎች ሰላምን በማስፈን የህግ የበላይነት ማስከበር አለመቻል በህዝቦች መካከል እርስበርስ መከፋፈል ከዛም አልፎ ግጭት ሊፈጥር ስለሚችል ነው። ይህ ደግሞ በዙሪያችን ለከበቡን ጠላቶቻችን “ሠርግና ምላሽ” እንደሚሆን ይታመናል።
አሁን አሁን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች በሽብር ቡድኖች የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ዝርፊያዎች ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ባለመቻሉ እንደ አቅመ ቢስ እያስቆጠረው ይገኛል። አስተሳሰቡ በራሱ የተሳሳተ ቢሆንም መንግስት ግን አስተሳሰቡ የተጨማሪ ችግር ምንጭ ሳይሆን በተግባር ሊያርመው ይገባል።
የክልል መንግስታትም እንደ መንግስት ካለባቸው ህገመንግስታዊ ኃላፊነት አንጻር የየክልሎቻቸውን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ፊታቸውን ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ በማዞር ተገቢውን ተሞክሮ መቅሰም ይጠበቅባቸዋል እላለሁ።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014