ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ናቸው። ቋሚ ስራቸው የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስተማርና ማማከር ነው። ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ ለ28 ዓመታት የነቃ የፖለቲካ ተሳታፊ ነበሩ። አሁንም የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲን በሊቀመንበርነት ይመራሉ። ፓርቲያቸው የመድረክ ስብስብ አባል ሲሆን፤ እርሳቸውም የስብስቡ ምክትል ሊቀመንበር ናቸው።
ፕሮፌሰር በየነ፤ ለ28 ዓመታት በፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ ስላደረጋቸው ምክንያት ሲናገሩ “የኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት አለመቃናት ዕልህ አሲዞኝ ነው፤” ይላሉ። እንደርሳቸው እምነት የሰው ልጅ የፖለቲካ ፍጡር ነው። ይህ እንዲቃና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሚሰራው ሙያ በተጨማሪ በአገሪቱ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ በነፃ ማገልግል መልመድ አለበት። ፖለቲካን ለጥቅምና ለስልጣን ብቻ ሳይሆን ለአገርና ለህዝብ ሲባልም ዜጎች መሳተፍ እንዳለባቸው በጽኑ እምነት ይገልፃሉ። ከአንጋፈው ምሁርና ፖለቲካኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጋር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳቶችና መፍትሄያቸው ዙሪያ ቆይታ አድርገናል። እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያልተቃናው ለምንድን ነው?
ፕሮፌሰር በየነ፡– የኢትዮጵያ ፖለቲካ መቼም ተቃንቶ አያውቅም። ምክንያቱም መተማመን የለም። አንዱ ሌላኛውን በበላይነት መግዛት ነው የሚፈልገው፤ ሌላው ይህንን መቀበል የለብኝም በማለት ይንፈራገጣል። በመሆኑም ፖለቲካችን ሁሉም የበላይነት ለመያዝ የሚደረግ ግብግብ ነው።
በፊውዳሉም ሆነ በወታደራዊው አገዛዝ ተመሳሳይ ነው። አሁንም የጎበዝ አለቆች በአገሪቱ ዴሞክራሲ እናመጣለን ብለው ከዲሞክራሲ ጋር የማይገናኝ ፍጹማዊ አምባገነን አስተዳደር ጫኑብን። ሁሉም በዙር ይህንን ነው የሚያደርጉት፤ ከዚህ ወጥተን ዘመናዊ አስተዳደር መስርተን ዜጎች ማን ማስተዳደር እንዳለበት ይወስኑ፤ ካልተስማማቸው ያወርዱታል።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተቃንቶ ቢያዩት ፖለቲካን እርግፍ አርገው ይተውታል?
ፕሮፌሰር በየነ፡– አንተ የምትለው ስልጣን ነው። ስልጣን ብፈልግ እስካሁን ከማን ጋር መመሳጠር እንዳለብኝ አውቃለሁ። እስካሁን ባለስልጣን እሆን ነበር። ይህን ግን ህሊናዬ አይፈቅደውም።
አዲስ ዘመን፡– ስልጣን ሳይሆን ፤ የአገሪቱ ፖለቲካ እርስዎ እንደሚሉት የተቃና ቢሆን ኖሮ ከፖለቲካ ጡረታ ሊወጡ ይችላሉ ወይ? ነው፤
ፕሮፌሰር በየነ፡– ይህ በኢትዮጵያ ሊመጣ እንደማይችል እያየሁ ነው። ሁሉም ጽንፈኛ ነው። የበላይነቱን ለመጫን ይፈልጋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ወስጥ ያለው ፖለቲከኛ፤ ጠባብና የተደበቀ አጀንዳ ያለው ነው። አንዳንዱም የቀን ጅቦች ይላል። ለዚህ ተትቶ የሚኬድበት ደረጃ ላይ አይደለም። ገና ብዙ ዓመት ያለፋናል።
ዕድሜያችንና ጤናችን የፈቀደውን ያህል የሚያስለፋ ነው። አንተ እንደምትለው በቀላሉ ሁሉንም የሚያግባባ አስተዳደር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይመጣል የሚል ትንበያ የለኝም። የኢትዮጵያን ህዝብ አስማምቶ ያለአድሎና ስጋት በህዝብ ፈቃድ ስር ሆኖ የሚያስተዳድር የፖለቲካ አደረጃጀትና እንቅስቃሴ ለመፍጠር እንናፍቃለን። ስለዚህ በትግሉ መድረክ እስከተቻለኝ እቀጥላለሁ። ህይወቴ እስካለ ይህን ለውጥ ለማምጣት እታገላለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ባለፉት 28 ዓመታት ምን ያህል ፓርቲዎችን መሰሩቱ? ፓርቲዎቹስ ምን ያህል ውጤታማ ነበሩ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ተቧድኖና በደንብ ተዘጋጅቶ የመጣ ነው። ጉልበት፣ ሀብትና ብልጠት ያለው ቡድን ነው። በፈለገው አቅጣጫ የሚወስድና ወጣ ያለውን እየመታና የፈለገውን እያደረገ ከጨዋታ ውጭ አድርጎ የሚሄድ ነው። በ28 ዓመታት ፋታ የማይሰጥ ፖለቲካ ውስጥ ነው የቆየሁት፤ በአብዛኛው ስሰራ የነበረው የፖለቲካ ሀይሎችን ማሰባሰብ ነው። በእነዚህ ዓመታት በዚህ አካል ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል ሀይል ለመፍጠር ስሰራ ነበር። በተናጠል ይህን ሊቋቋም የሚችል ሀይል የለም። ሊፈጠርም አይችልም። ምክንያቱም ስርዓቱ እንዲዳብር አይፈቅድለትም።
በኩርፊያና በብስጭት የተቋቋሙ ድርጅቶችን አሰባስቦ፤ አቅም ገንብቶ ያለውን ስርዓት ምርጫ አካሂዳለሁ፤ ዴሞክራት ነኝ ስለሚል በዚህ እንኳን ተጽዕኖ ለማሳደር የተሟላ ጉልበት ለማምጣት ስታገል ነው የቆየሁት። በዚህ ሂደት ብዙ ስብስቦችን መምራት ችያለሁ።
በሽግግር መንግስቱ 15 የደቡብ ፓርቲዎች ስብስብ አንድ ላይ በማምጣት “የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት” በሚል ወደ ሽግግሩ ገባን። ስብስቡ ከተጠበቀው ውጭ ተፅዕኖ ማድረግ ችሎ ነበር። በሽግግሩ ምክር ቤትም 17 መቀመጫ ነበረው። ቁጥሩም ከኦነግ ይበልጥ ነበር። ኢህአዴግም ከእኛ ጋር መደራደር ነበረበት። በውሳኔ ሂደት ተሳትፎው ቀላል አልነበረም። የወቅቱ መሪም በግልና በቡድን እየጠሩ ያናግሩን ነበር። ከሌላ ጋር አብረን ሚዛን እንዳንደፋ ይሰጉ ነበር።
በ1984 የአካባቢ ምርጫ ሲካሄድ ኦነግ ተገፍቶ ወጣ። እኛ ቀረን። እኛም በሽግግሩ ቻርተር ላይ የተስማማነው በዚህ መልኩ ስላልሆነ የእስካሁኑን ሽግግር እንገምግም የሚል ጥያቄ አነሳን። ኢህአዴግ ይህን አልወደደውም። በሌላ በኩል፤ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የሰላምና የእርቅ ጉባዔ ፓሪስ ላይ ተጠራ። የደቡብ ህብረትም ተወካዮች ልከን በዚያ ተሳተፍን። ጉባዔውም ኢህአዴግ ባለበት በአዲስ አበባ መካሄድ አለበት የሚል ውሳኔ አሳለፈ። ኢህአዴግ ግን “ይቺ በቄላ ካደረች አትቆረጠምም” በማለት ከሽግግሩ መንግስት አፍራሽ ሀይሎች ጋር አብራችሁ አሲራችኋል፤ በሚል ይቅርታ እንድንጠይቅ በምክር ቤቱ ክስ አቀረበብን። ይቅርታ የሚያስጠይቅ የሰራነው ወንጀል የለም ጉባዔው ሰላማዊ ነው። የሽግግር መንግስቱን የሚያፈርስ ነገር የለም። እኛ እናንተን የት ተሰበሰባችሁ ብለን እንደማንጠይቅ ሁሉ እኛም መሰብሰብ መብታችን ነው። ከዚያ ጥቂት ተመሳጥረው አብዛኞቻችንን ከምክር ቤቱ አባላትና
ከነበረን የመንግስት ሀላፊነት አባረሩን።
ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ አማራጭ ሀይሎችን በማቋቋም ምርጫ ውስጥ ገባን። በሃድያ ዞን ከአንድ ኢህአዴግ የምርጫ ተወካይ ውጭ ሌሎቹን በፌዴራልም በክልልም አሸነፍን። ለ1997 ዓ.ም ምርጫ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ህብረት የሚል ትልቅ ስብሰብ ፈጠርን። በዚያም ተወዳደርን። ከዚያ ውስጥ አንጃ ሆኖ የወጣውና በኋላ ቅንጅት የተባለው ቡድንም ከህብረቱ የወጣ ነው። በዚያ ወቅት ሁለት ትላላቅ ሀይሎች ናቸው ኢህአዴግን የተገዳደሩት፤ ከምርጫ በኋላ በተፈጠረው ሁኔታ ሲፍረከረኩ እንደገና አሰባስበን መድረክን ፈጠርን። አሁን ላይ በዚህ እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ የመሯቸው ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተፈረካክሳችኋል፤ ለምንድን ነው?
ፕሮፌሰር በየነ፡-አንድ ልጅ ቤተሰቦቹ በደንብ ተንከባክበው ካላሳደጉት ማደግ ይችላል? እዚያው ቀጭጮ ነው የሚቀረው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታና ሰፊ ምህዳር ያስፈልጋቸዋል። ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ህዝብን አደራጅቶ፤ ምርጫ ገብቶ ድምጽ ማግኘት ነው ዓላማው፤ በየአደባባዩ ወጥቶ የሚጮህ አይደለም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማደግ ሰፊ ምህዳር ተፈጥሮ፤ ተዘጋጀቶና ደጋፊ አሰባስበው መስራት አለባቸው። የፖለቲካ ፓርቲ የጥቂት ሰዎች ሳይሆን የህዝብ ነው። የመሪዎች ሥራ የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው ርዕዮተ ዓለም ቀርጸው ወደ ህዝብ መውሰድ ነው። ከዚያ ህዝቡ የራሱ አድርጎ መደግፍ አለበት። ለዚህ ግን ምቹ ሁኔታ የለም።
አዲስ ዘመን፡– ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ፖሊሲ ቀርፆ የማቅረብ ችግር የለባቸውም?
ፕሮፌሰር በየነ፡– ፖሊሲ ቀርጸህ የምትገባው እንዴት ነው? ሽፍታ ሆነህ ነው። ኦነግ፣ ግንቦት ሰባትና ሌሎችም የሚከበሩትና የሚፈሩት መሳሪያ ይዘው ጫካ ስለገቡ ነው። ወደጫካ የገቡት በሩ ስለተዘጋ ነው። እንደኛ ዓይነቱ ከነገ ዛሬ ይሻላል በሚል ተስፋ ሳይቆርጥ ጥረት ያደርጋል። እነርሱ ቶሎ ወደ ስልጣን መድረስ ይፈልጋሉ። እንደ ቡልዶዘር ደፍጥጠህ ካልገባህ በስተቀር በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ በሀሳብ ክርክር ለመግባት የሚፈቅድ አካሄድ አልነበረም። በዚህ ሁኔታ ፓርቲ እንዴት ይጠናከራል? ፖሊሲስ እንዴት ቀርጾ ይገባል፤ ይቀጭጫል እንጂ፤
አማራ፣ ኦሮሞ፤ እንዲህ በሚል የሚደራጁ ፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም ስብሰብ ሳይሆኑ ብሶት፤ ቂም በቀልና ምሬት የወለዳቸው ፓርቲዎች ናቸው። ፓርቲ መመስረት ያለበት በርዕዮተ ዓለም ነው። በዓለም ያሉትን ርዕዮቶች መሰረት አድርጎ መደራጀት ነው። ማንነቴ ስላልታወቀ ማንነቴ ይታወቅ በሚል የሚቋቋም ፓርቲ አለ። አሁን 107 ፓርቲ የሚባለው በርዕዮት ሳይሆን በተለያዩ ምሬቶች የሚቋቋሙ ናቸው። ይህ የፖለቲካ ፓርቲ ሊሆን አይችልም። የፖለቲካ ፓርቲዎችን መቁጠር ብቻ ሳይሆን፤ የተቋቋሙበትን ዓላማ ጠለቅ ብሎ አይቶ በርዕዮተ ዓለምና በሌሎች መመዘኛዎች ቢመረመር ከ107 ተራግፎ 15 ይቀራል።
አዲስ ዘመን፡– በዶክተር አብይ የሚመራ ውን ለውጥ እንዴት ይገመግሙታል?
ፕሮፌሰር በየነ፡– ለውጡን የጠበቅነው አልነበረም። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመተንበይ አይቻልም። ብዙ ጊዜ ትንበያችንም አልሳካ እያለን ተቸግረናል። ኢህአዴጎች በቢሯቸው ቆልፈው፤ ሲፈልጉም ለአንድ ወር ሰብስባ ገብተው ልዩነታቸውን ያፍኑታል፤ አይታወቅም። ካድሬዎቻቸውም “ደርግ 17 ዓመት የገዛውን እኛ 50 ዓመት መቆየት ያቅተናል ወይ?” ሲሉ ይደመጣሉ። ይህን የሚሉት በዋዛ ሳይሆን በደህንነት መዋቅርና በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ወጥረው በመያዝ ነው። ህውሓትም በቀላሉ ወደኋላ ይመለሳል የሚል ግምትም አልነበረንም። ከዚህ ተነስተን አሁን የመጣው ለውጥ ይመጣል የሚል ግምት አልነበረኝም። ዶክተር አብይና ሌሎች በዚህ መልኩ መውጣታቸው ደንቆናል።
አሁን ያለው ለውጥ ብዙ ተስፋ የሚጭር ነው። ቋንቋው ሳይቀር በፊት ከነበረው ኢህአዴጋዊ አነጋገር የተለየ በመሆኑ ህዝብ መስማት የሚፈልገው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይዘው የመጡት ጉዳይ፤ ትንታኔ ለየት ያለ አቀራረብ ነው። ህብረተሰቡ ተስፋ እንዲያድርበት አድርጓል። ንግግሮችን በተግባር በማስደገፍ መሬት የረገጠ እንዲሆን ማድረግ ግን ይገባል።
በእርሳቸውም “የምናደርገው ጥረት ምን ይመስልሃል?” ተብዬ አውቃለሁ። ከበፊቱ ብዙ የተሻለ ነገር እንዳለ በማንሳት እያንዳንዱ ቃል በህግ በፖሊሲ እየተደገፈ እታች ህዝብ ዘንድ መውረድ አለበት እላለሁ። ብዙ ጥረትም አድርገዋል። ችግሩ አሁንም የፖሊሲ ለውጥ የለም የአፈጻጸም እንጂ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ነክተዋት አያውቁም። ሰው ከሰው ይለያል የዶክተር አብይ የተለየ ነው። ህዝብን የማያስቆጣ፤ ተስፋ የሚሰጥም ነው። ከሃይማኖቱም ከተለያየ አንፃር በማድረግ እየሰሩ ነው። እኛም በገንቢነቱ ደግፈነዋል። ኢህአዴግ ሲፍረከረክ አንድ ብሄራዊ መንግስት ይቋቋም ነው ያልነው። ኢህአዴጎች ይህን መስመር አልፈለጉትም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም እኛ እየሰራን ነው በዚያ ይፈታል ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሻግሩናል ብለው ያምናሉ? መስተካከል አለባቸው የሚሏቸው ነገሮች አሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች አሉ። በመጀመሪያው የህግ የበላይነት ማስከበር አለባቸው። ማንም የጎበዝ አለቃ እየተነሳ በመገናኛ ብዙሃንም፤ በምንም እየተነሳ ከህዝብ ፍላጎትና ርዕይ ውጭ አገሪቱን የሚያናጋ ነፃነት መስጠት ትክክል አይደለም። በክፍለ አገር ህዝብ ሲዘረፍ ፖሊስ ቆሞ ነው የሚያየው፤ ከመታሀራ ተደውሎ እንደተነገረን ፖሊስ እያየ ሆ ብሎ መጥቶ ከሱቅ እቃ እየጫኑ ነው የሚሄዱት፤ ፖሊስ የህዝቡን መብት ማስከበር አለበት። ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ጋር ስንገናኝ አንስተናል። እርሳቸው ከዚህ በፊት ታፍኖ የነበረው ህዝብ ትንሽ ይተንፍስ ነው የሚሉት፤ መተንፈሱ ግን ወደ ጋጠ-ወጥነት ተሻገረ። ማንም ተነስቶ “እዚህ በእኛ አካባቢ ምን ትሰራለህ?” ይላል። ዜጎች በአገሪቱ ላይ ያላቸውን እምነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። ከመንግስት ጋር ጦርነት ሁሉ የሚገጥም እየተፈጠረ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከአቅማቸው በላይ ነው እንዳንል የብዙ ዜጎችን ህይወት ከቀጠፈ በኋላ እያረጋጉ ነው። ይህ ትክክል አይደለም፤ አገሪቱን ዋጋ የሚያስከፍል ነው።
አዲስ ዘመን፡– ኢህአዴግ አንድ ፓርቲ ሆኜ እዋሀዳለሁ እያለ ነው። እንዴት አዩት?
ፕሮፌሰር በየነ፡– ኢህአዴግ ቀደም ብሎ መሰባሰብ ነበረበት። ከዚህ ቀደምም አርዓያ መሆን ነበረብህ ስንል ወቅሰነዋል። እናንተ ምሳሌ ሳትሆኑ ሌሎቹን ተበታትናችኋል ትላላችሁ። እናንተ ለ28 ዓመታት በግንባር ተቧድናችሁ ነው የቆያችሁት እናም አርዓያ አይደላችሁም ብለናቸዋል። የሚወክሏቸውን ክልሎችም በሙሉ እንኳን አሳታፊ አይደሉም። ቀደም ብለው ቢዋሀዱ ኖሮ ህውሓት አኩርፎ ጠርዝ ላይ አይሆንም ነበር። እነገሌ አይታመኑም የሚለው አይመጣምም ነበር። አንድ ፓርቲ ነዋ! አሁን ግን ራሳቸውን የቻሉ ፓርቲዎች ናቸው። 28 ዓመት የኢትዮጵያና የራሳቸው ፖለቲካ እንዳያድግ አድርግው ነው የቆዩት፤ ዛሬ ላይ መዋህዳቸው ጊዜ ያለፈበት ቢሆንም ተገቢነት ያለው ነው።
አዲስ ዘመን፡– በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የዜጎች መፈናቀል አለ። ይህን ጉዳይ እንዴት ይገመግሙታል? እንዴትስ መታረም አለበት?
ፕሮፌሰር በየነ፡– ይህ የምናፍርበት ነው። የህግ የበላይነት፤ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ቢኖር አይከሰትም ነበር። ኢህአዴጎች ፍቱን መድሃኒት ብለው ያዘዙት መርዝ አሁን ላይ ለመሰብሰብ አስቸጋሪ ሆኗል። ይህ አፈና ያመጣው ነው። ብቃት የሌላቸውና በየቦታው ዓላማ አራማጆች በሚል በህዝብ ላይ የተሾሙ ካድሬዎች የፈጠሩት የአላዋቂነት ስራ ነው። ድንገት እየተነሱ ህዝብን እኛን አትመስልም ከዚህ ለቅቀህ ሂድ ማለት ያለዋቂዎች ሥራና አገር እንዴት እንደሚተዳደር ያለመገንዘብ ነው።
ተደባልቆ መኖር የዓለም ህዝብ ጠባይ ነው። የትም ዓለም “ንጹህ” እና የአንድ ብሄር ብሎ ነገር የለም። ኢትዮጵያ በዚህ የተለየች አትሆንም። ኢህአዴጎች ግን፤ በተለይም የህውሓት ትርክት ይህን ነው እንዳለ የሚያስቀምጠው፤ እያንዳንዱ እየተነሳ የእኛ መሬት ነው። የአባቶቻችን የሚለው ነገር ውስጥ ገብቶ የመሀይም ስራ ተሰራ። ለአላዋቂ ካድሬ ሲፈልግ ተኩሶ እንዲገድል፤ ሲፈልግ ከአገር እንዲያባርርና እንደፈለገው እንዲያደርግ ፈቃድ ተሰጠ። ዲሞክራሲ፤ የህግ የበላይነት መልካም አስተዳደር ጠፋ። ዛሬ ላይ ለዜጎች ስቃይ ሆነ።
በየቦታው ያለውን መፈናቀልና ሰቆቆ ለማስቀረት ዴሞክራሲን፣ የህግ የበላይነትና መልካም አስተዳደርን ማስፈን ይገባል። የዓለምን፤ የሰዎችንም ስብጥር እንዴት በአንድ አገር ሊኖር እንደሚችል ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማሳወቅ አለብን። አሁን ቀርቶ አያቶቻችን እንዴት ተቻችለው ይኖሩ እንደነበር ማስተማርና ወደ ዜሮ መውረድ እንዳሌለብን ማስረዳት ይገባናል። ከአንድ ዘር መፈጠር፤ ራስን ቅዱስ አድርጎ ማየትና ንጹህ አድርጎ ማሰብ ትክክል አለመሆኑን ማስረጽ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡–የአዲስ አበባ ምርጫ ተራዝሟል ተብሏል፤ ምርጫው ስላለመካሄዱ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– አዲስ አበባ ደሴት አይደለም። በአገር ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ ነው። በምርጫው ህግና አፈጻፀም ላይ እምነት በሌለበት አገር ምርጫ ማካሄድ ውጤት የለውም። የአዲስ አበባ ቀርቶ የጉለሌ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም። በጥቅሉ ነው መታየት ያለበት፤ በአገር ደረጃ የፖለቲካ ምህዳሩ ሳይሰፋ አዲስ አበባን ነጥሎ መውሰድ አይቻልም። አለበለዚያ የይሰሙላ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– ከአዲስ አበባ ጉዳይ ሳንወጣ በአዲስ አበባ ይገባኛልና በወሰን ጉዳይ ላይ የርስዎ አቋም ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር በየነ፡– ከፈለግህ በማንኛውም ነገር ላይ መጨቃጨቅ ትችላለህ። ጭቅጭቁ አያስገርምም። በቤት ውስጥም እናትና አባትም ይጨቃጨቃሉ። አዲስ አበባ በሽግግሩ ወቅት ክልል 14 ተብሎ ራሱን የቻለ አስተዳደር እንዲሆን ተወስኖ ተቀባይነት አግኝቷል። በህገ መንግስቱም ወደ ማዘጋጃ ተቀይሮ ራሱን የቻለ አስተዳደር እንዲሆን ተደርጎ ተወስኗል። ስለሆነም በሽግግርም ወቅትም ሆነ በህገ መንግስቱ አስተዳደራዊ ሁኔታው ይታወቃል። የአዲስ አበባ ክልልም ከየት እስከየት እንደሆነ እልህ አስጨራሽ ክርክር ተደርጎ ስለተወሰነ የሚታወቅ ነው። ይህን ሄዶ ማየትም ይቻላል። ከዚያ በኋላ ይህን የሚከልስ አዋጅም አልወጣም። ስለሚታወቅም ነው አንድ ኮንዲሚኒየም ወሰን አልፎ ተሰራ የተባለው፤ የአዲስ አበባን ወሰን አልፈው፤ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የገነቡ የአዲስ አበባ ባለስልጣናት እብዶች ናቸው። እንደሚያጣላና እንደማያግባባ ይታወቃል፤ በጓደኝነት “ተው እባክህ ዝም ብለህ ስራ” ተባብለው ከሆነ አሁን ዋጋ ይከፍላሉ። አዲስ አበባ በዚያ ንብረት ላይ ያወጣውን ወጪ መክሰር አለበት በእኔ እምነት፤ በህገ አግባብም መሄድ አለበት።
የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም የተባለውን ተደራድሮ ስምምነት ማድረግ ነው። አገልግሎቱን በተመለከተ ውሃ፤ መብራት፤ የቆሻሻ አወጋገድና ሌሎች ነገሮች ላይ መደራደር ነው። ይህን ምንም ሳያደርጉ ቆይተው አሁን ያጨቃጭቁናል። ይህን ሀላፊነት መውሰድ ያለበት ኢህአዴግ ነው። ከዚያ ውጭ በአዲስ የፖለቲካ ፍላጎት አዲስ አበባ ፊንፊኔ ነው፤ በረሮ ነው እያሉ ወዲያና ወዲህ የሚላገው ነገር ቅንነት የሌለው ክርክር ነው። ለምን ብትለኝ፤ አሁን የተሰባሰበው የፖለቲካ ቡድን ሁሉ ህገ መንግስቱ እስከሚሻሻል ድረስ ባለው ህገ መንግስት እንቀሳቀሳለሁ ብሎ ነው የገባው፤ ጦረኛ ነኝ ያለውም፤ እድሜ ይፍታህ የተፈረደበትም፤ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ይዞ አክቲቪስት ነኝ ባይም በህገ መንግስቱ መሠረት ነው የተለቀቀውም፤ የመጣውም፤ ህገ መንግስቱ ሳይሻሻል ምናምን እያሉ የሚያውኩን የቅንነት ችግር ነው። ይህ በጣም ያናድደኛል። ይህን አክብረው ለመስራት ፈቃደኛ ካልሆኑ ለምን መጡ? እንደዚያ ከሆነ በህገ መንግስቱ አግባብ መምጣት የለባቸውም። ይህ የሚያነሱት ጥያቄ የጦርነት ጥያቄ ነው። በሰላማዊ መንገድ እንንቀሳቀሳለን ብለው መጥተው እኔ አልደመጥም እያሉ ነው ጦርነት የሚያውጁት፤ ትክክል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡– ለብዙ የአገሪቱ ችግር ምክንያት የትምህርት ፖሊሲው እንደሆነ ይነሳል። ፖሊሲውን በማርቀቅ ረገድ እርስዎ እንዳሉበት ይታወቃል። ስለዚህ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– በሽግግር መንግስቱ ወቅት የአጠቃላይ ትምህርት ምክትል ትምህርት ሚኒስትር ነበርኩ። ዋናው ስራ በጦርነቱ የወደሙትን ትምህርት ቤቶች በማቋቋም ሚና ተጫውቻለሁ። አሁን ላይ ባሉት የትምህርት ተቋማት ላይ የራሴ ግብዓት አለኝ። የትምህርት ፖሊሲውን በወቅቱ አለቃችን በነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገምገም ጀመሩ ተብሎ የቤት ስራ ተሰጥቶኛል። ስድስት ወር ያህል የትምህርት ባለሙያዎችን ይዤ ቅዳሜ ቅዳሜ ከጠዋት እስከ ምሳ ሰዓት እየተሰበሰብን የፖሊሲ አቅጣጫ ሰርተናል። ባለን የፖለቲካ ልዩነት ከትምህርት ሚኒስቴር አንስተው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ወሰዱኝ። ያኔ ከእኛ ከባለሙያዎች ወጥቶ የተሰራ የትምህርት ፖሊሲ ነው አገርን ለችግር የዳረገው፤ በእኛ አልተሰራም። በግምገማው ሂደትም “ለምንድን ነው?” ብዬ ስጠይቅ ዶክተር በየነ አንተ የራስህን መንግስት ስታቋቁም በባለሙያ ታሰራዋለህ አሉኝ። የዚያን ጊዜ በሽታ አሁን የትምህርት ስርዓቱን አያወከ ነው። አሁንም እንኳን የተዘጋጀው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነሱ መኖር አለባቸው ብለው ሰብሰባው ጠዋት ሊካሄድ ሲል ማታ ነው የተነገረን፤ ዩኒቨርሲቲዎችም ከፍተኛ ባለሙያ አልላኩም። አሁንም በተሰራው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ ምሁራንን ለማሳተፍ በሩን የመክፈት አዝማሚያ የለም።
አዲስ ዘመን፡– የህዝብና ቤት ቆጠራ መራዘም ተገቢ ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር በየነ፡– መሬት ላይ ያለው ሁኔታ መስራት የሚፈለገውን ነገር ችግር ላይ ሊጥል ይችላል። የህዝብና ቤት ቆጠራ ጠባያቸው አንድ ነው። ቤት ለቤት ሄዶ ነው የሚቆጠረው። ይህን ለማከናወን በአገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ መኖር አለበት። በተለያየ ቦታ ግጭት አለ። “እኔም አለሁ፣ እኔ አልተደመጥሁም” እያለ በቁምህ የሚገድል ባለበት ሁኔታ በሁሉም ቦታ አጀብ ተልኮ አይቻልም። ይህን ዋስትና ለመስጠት ይቸግራል ብሎ የማራዘም ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢ ነው። ባይወሰን ነው የሚገርመኝ፤ ተገቢ መረጃ ለማግኘት ነው የሚቆጠረው፤ 99 ከመቶ ፈጸምሁ ለማለት ቆጠራው መካሄድ የለበትም። የተፈናቀለ ህዝብ አለ። ውሳኔያቸውን አከብራለሁ። ስላልተቆጠረም የዓለም መጨረሻ አይደለም። የሚያነታርኩንን ነገሮች መፍታት ነው።
አዲስ ዘመን፡–ፕሮፊሰር፤ ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር በየነ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2011
በአጎናፍር ገዛኽኝ ��