
አዲስ አበባ፡- ሕወሓት ከዚህ በፊት በተደረገው ጦርነት ከተከሰተው ውድመት ትምህርት በመውሰድ ለሰላም ውይይቱ ዝግጁ መሆን እንዳለበት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ አሳሰበ።
ሻለቃ ኃይሌ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጠው አስተያየት እንደገለጸው፤ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያደረጉት ጥረት በተለይ በሕወሓት በኩል አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ በተደረገው ጦርነት አስከፊ ውድመት ተከስቷል።
በአገር ደረጃ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረው ቀውስ ከፍተኛ ቢሆንም በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰው ግን እጅግ አስከፊ ነው ያለው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ፤ ከጦርነት ጥፋት እንጂ አንዳችም መልካም ነገር ስለማይገኝ ለሁሉም የሚበጀው አሁን የተጀመረውን የሰላም ጥረት በአግባቡ መጠቀም ብቻ ነው ብሏል።
ከጦርነቱ በፊት ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ወደ መቀሌ በመሄድ ከዶክተር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ጋር አለመግባባቶቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ብዙ ጥረት ማድረጋቸውን ያነሳው ሻለቃ ኃይሌ፣ ዳሩ ግን በሕወሓት በኩል ቁርጠኝነት ባለመኖሩ ጥረቱ ፍሬያማ ሳይሆን ቀርቶ የብዙዎችን ሕይወት ያረገፈና የዘመናት ጥረት ውጤቶች የሆኑትን የአገሪቱ ሀብቶች ወደ ዶግ አመድ የቀየረው ጦርነት መከሰቱ በቁጭት ገልጿል።
በወቅቱ የሕወሓት ባለሥልጣናት ትግራይን እንደ አንድ የኢትዮጵያ ክልል ሳይሆን እንደ አንድ አገር አድርገው ከማቅረባቸው በተጨማሪ ለውይይት የሚያቀርቡት ነጥቦች እንደ የአንድ የክልል ባለሥልጣናት የሥልጣን ገደብ ባለመሆኑ ድርድሩ እንዲመክን ትልቅ እንቅፋት እንደነበር የጠቆመው ሻለቃ ኃይሌ፣ አሁንም «ቀይ መስመር፣ ሰጥቶ መቀበል» የሚሉ የቅድመ ድርድር ቃላቶች የድርድሩ ሂደት እንዳያደናቅፉ ያለውን ስጋት ገልጿል።
እንደ ሻለቃ ኃይሌ ማብራሪያ፣ የሰላም ውይይት ክርክር ስላልሆነ ቀይ መስመር የሚባል ነገር ባይነሳ ጥሩ ነው። አገር ማዳን ከተፈለገ ሁሉም ወገን ሰጥቶ ለመቀበል ብቻ ሳይሆን የመተውም ኃላፊነት አለበት። ያም ሆኖ ሕወሓት እንደ ከዚህ በፊቱ «እኩል ነን፣ ትግራይ አገር ናት ወዘተ» የሚሉ አፍራሽ ነጥቦችን ይዞ ለሰላም ውይይት ባይቀርብ ጥሩ ነው ብሏል።
በጦርነት ያለቁ በርካታ ዜጎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደሰላማዊ ውይይት ከመግባት የበለጠ ነገር የለም። በኢትዮጵያ መንግሥትም በኩል ቢሆን አሁን ያሉ የኑሮ ውድነትና የሰላም እጦት ችግርና የውጭ አገሮች ጣልቃ ገብነት ግርግር በቂ በመሆናቸው ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ላይ መጽናት ይጠበቅበታል።
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ሕወሓት ለፌዴራሉ መንግሥት አንገዛም በማለት ሕዝቡን ለሌላ ችግር ማጋለጡ ተገቢ ባለመሆኑ ለሰላማዊ ውይይቱ ዝግጁ እንዲሆንም በአጽንኦት አሳስቧል።
መጀመሪያውኑ የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ዋዝቦች በክልሉ ታጥሮ የሚኖር ሕዝብ ሳይሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖርና በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሕዝብ መሆኑን የመሰከረው ሻለቃ አትሌት ኃይሌ፣ ድርድሩም ቢሆን የሚካሄደው በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል እንጂ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ሌላው አካል ከትግራይ ሕዝብ ጋር ጸብ እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል ብሏል።
ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ኢላማ በመሆን ሕዝቡ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ተጋላጭ በሆነበት ጊዜ ውስጥ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የጦርነት ወሬ እንዳይሰማ አደራዳሪ አካላት፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሰላም ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ጠይቋል።
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014