
አዲስ አበባ፡- በሕዝቦች መካከል ከወዳጅነት ጠላትነትን መስበክ፣ ከልማት ጥፋት ላይ ማተኮር የሚዲያ ተግባር ሳይሆን የግል አመለካከት በመሆኑ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የባህልና ሚዲያ ጉዳዮች አማካሪ አቶ መሐመድ አህመድ አመለከቱ፡፡
አቶ መሐመድ አህመድ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፣ የተለያየ ባህልና ታሪካዊ ዳራ ያላቸው ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች በሰላም አብረው ለሚኖሩባት ኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነት፣ ከጥፋት ይልቅ ልማትን የሚያጎላ የሰላም ሚዲያ ነው፡፡ ለከፋ ችግር ተጋልጠው የነበሩ እንደነሩዋንዳ እንዲሁም ከብተና አፋፍ ላይ ያሉ እንደነ ኢራቅ፣ የመንና ሶሪያ ያሉ የዓለም አገሮች ጀርባ የሚዲያ ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር መሆኗ አንድ ነገር ሆኖ በውስጥና በውጭ ሃይሎች ጫና ተወጥራ ባለችበት በአሁኑ ጊዜ ሚዲያዎች አፍራሽነት ከታከለበት ፈተናው ቀላል እንደማይሆን ያሳሰቡት አቶ መሐመድ፣ ከዚህ አንጻር ሕዝቡ ትንፋሹን በመሰብሰብ በዙሪያችን ያንዣበቡ ጠላቶችን በአንድነት እንዲመክት ለአገሪቱ የሚያስፈገው ሚዲያ ሚዛናዊ የሆነ የሰላም ጆርናሊዝም መርሆን የተከተለ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በሩዋንዳ እንደቀላሉ ተጀምሮ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ወደ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕይወት የቀጠፈው ዘግናኝ የዘር ፍጅት በውሸት መረጃ ያቀጣጠሉና ሕይወታቸውን ለማትረፍ የሸሹ ሰዎች እንዳያመልጡ የት እንዳሉ አቅጣጫን በማሳየት ገዳዮቹን የመሩ በተለይ በወቅቱ የኤፍ.ኤም ሬዲዮኖች እንደነበሩ በታሪክ የተመዘገበ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መሐመድ፣ በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሱ ያሉና የመበተን አፋፍ ላይ የሚገኙ እንደ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ የመንና ሶሪያ ያሉ አገራት በውጭ ፈንድ የሚደረጉ ሚዲያዎች ጭምር ጦርነቱ እየተፋፋመ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
ዳሩ ግን በአገራችንም አገረ መንግሥቱን በሃይል ለመናድ ብሎም አገራዊ ለውጡን ለመቀልበስ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ያሉ ሃይሎች በዋናነት የሚዲያ ጉልበት በመጠቀም መሆኑን የገለጹት አማካሪው፣ አንዳንድ የአገራችን ሚዲያዎች በስማቸው መደበኛ ይሁኑ እንጂ በሥራቸው ከሚዲያ መርሆ ባፈገጠ መልኩ ሁለት ቦታ በመቆም ጠላትንም ወዳጅንም እኩል ሲያገለግሉ ማየት እየተለመደ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡
ከሁሉም በላይ በሕጋዊ መንገድ ተቋቁመው ሕገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ሚዲያዎች ካልተፈተሹ እስካሁን ካስከተሉት ጥፋት የከፋ ጥፋት ለመፈጸም ወደ ኋላ እንደማይሉ ያሳሰቡት አማካሪው፣ በማህበራዊ ሚዲያ ረገድም በሃላፊነት የሚሰሩ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ ጭር ሲል የማይወዱ አካላት የጎማ ፍንዳታ የቦምብ ፍንዳታ፣ የሁለት ሰዎች ጠብ ብሔር ወይም አገራዊ መልክ በማስያዝ አገር እንዳይረጋጋ እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
እንደ አማካሪው ማብራሪያ፣ ሚዲያ እውነትን፣ ፍትሃዊነትን፣ እኩልነትንና ወንድማማችነትን ይሰብካል፡፡ ማንም ሰው እውነትን በመወገን ሃሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት አለው፡፡ ሆኖም ግን ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አንዱ የሚዲያ መርሆ ነወ፡፡ በፈረሰች አገር ውስጥ ይቅር ነጻነት በሕይወት ለመኖር ራሱ ከባድ መሆኑን ማመዛዘን ያስፈልጋል፡፡ ለሚዲያ የመረጃ ምንጭ የሚሆኑ ሰዎች በተለይ በአሁኑ ጊዜ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2014