የኢትዮጵያ ታሪክ በብሄርና በጎሳ ቁርሾ ተጀምሮ ያቆመበት ጊዜ ላይ ነን። የኢትዮጵያ ታሪክ ፖለቲካ ወለድ በሆነ ጦርነትና አለመግባባት ተጀምሮ የቆመ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ ፍቅርና አንድነት በማጣት ያደፈበት ጊዜ ላይ ነን። የኢትዮጵያ ታሪክ የአንድነት ክንድ አጥቶ የሰለለበት ጊዜ ላይ ነን። በዚሕ የተነሳ እራሴን ጨምሮ ዜጎችን—መንግስትን..ፖለቲከኞችን ከትናንት የታሪክ ምእራፍ መረማመጃ ድልድይ መስራት እንዴት አቃተን ብዬ ለመጠየቅ ውስጤ ይነቃቃል ።
የቀደመውን በሰላም በፍቅር ተሳስቦና ተቻችሎ ለመኖር በፍቅርና በይቅርታ፣ በእርቅና በድርድር የተገነባ ትውልድ የሚረማመድበትን ድልድይ መስራት ይኖርብናል። ይሄን ታሪክ ለማደስ በምክክርና በተግባቦት የታነጸ ከዚህ ወደዚያ መራመጃ የብረት ድልድይ ያሻናል። እግሮቻችን በጽናት የሚቆሙበት መረማመጃ ሳይኖረን ሀገር ማሻገር አይቻለንም።
በመካከላችን ያለውን የልዩነት ሽል አምጠን መውለድ አለብን። ወደ ፊት እንዳንሄድ ያደረገንን የጎጠኝነት ሀሳብ ገለን መቅበር አለብን። ችግሮቻችንን በጋራ አምጠን፣ በጋራ በመውለድ የሚያድገውን አሳድገን፣ የሚሞተውን ገለን የአንድነት ድልድይ መገንባጽ ለህልውናችን መሰረት ነው ።
ችግሮቻችንን በጋራ የማሸነፍ ክህሎት እስካላዳበርን ድረስ በቆፈርንው ጉድጓድ ውስጥ ከመውደቅ ሌላ አማራጭ የለንም። ለነገሩ አሁንም እየወደቅን ነው። ትላንትና ሌሎችን ለመጣል ያጠመድናቸው የፖለቲካ ወጥመዶች እኛኑ እያሰቃዩን ነው። የተበተብናቸው የማስመሰል አካሄዶች ዛሬ ላይ በአያሌው እያሰቃዩን ነው።
ከነበርንበት፣ ከኖርንበት የፖለቲካ አስተሳሰብ መውጣት አለብን። ኢትዮጵያን አይታችኋት ከሆነ እየተሰቃየች ያለችው በፖለቲከኞቻችን ነው። ህዝባችንን አይታችሁት ከሆነ መከራ እያየ ያለው በፖለቲከኞቻችን ራስ ወዳድነት ነው። ከከተማ ወጣ ብሎ ያለው ኢትዮጵያዊነት፣ ያለው መተሳሰብ የሚደነቅ ነው ። ኢትዮጵያዊነት የቆሸሸው ከተማ ውስጥ ነው። እያበላሹን ያሉት ፖለቲከኞቻችን ናቸው። ከሁሉ በፊት የፖለቲካውና የፖለቲከኞቻችን እድፍ ሊጠራ ይገባል።
በቀደሙት ዘመናት እልህና አልሸነፍም ባይነት ዋጋ እያስከፈሉን ኖረዋል። አሁን ጊዜው ስለኢትዮጵያ የምንኖርበት ነው። ለዘመናት ስለራሳችን ኖረን አይተነዋል። እስኪ ደግሞ ስለኢትዮጵያዊነት እንኑርና እንየው። እስከመቼ አድሮ ቃሪያ እንሆናለን? ጦርና ጐራዴዎቻችን ጊዜ የሚያልፍባቸው መቼ ይሆን? በኢትዮጵያ ምድር በሀሳብ ማሸነፍ፣ በንግግር መርታት መፈጠሪያቸው መቼ ይሆን? በአንድ አይነት ፖለቲካ፣ በአንድ አይነት ሀሳብ፣ በአንድ ወጥቶ መግባት ሀምሳ አመታትን ደፈንን። መች ይሆን ትንሳኤያችን?
ብዙ እያወቅን፣ ልንማርባቸው የምንችልባቸው ብዙ ትላንትናዎች እያሉን ለምን የተሻለ ሀገርና ህዝብ መፍጠር አቃተን ? በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ቅርሶች ተከበን፣ ሰፋፊና ለም መሬቶችን ታቅፈን፣ የሚሰሩ እጆች፣ የሚያስቡ ጭንቅላቶች ሞልተውን ለምን ግራ ተጋባን ? በታሪክ ልቀን፣ በባህል ደምቀን ለምን ጨለማ ውስጥ ለመኖር ተገደድን ? ብዙ የተማሩ፣ ብዙ ፊደል የቆጠሩ ምሁራን እያሉን ለምን በድንቁርና መንገድ ላይ ቆምን ? ከሁሉም ትልቁ ፍቅር ስለሌለን ነው።
የህግ ሁሉ ፍጻሜ የሆነው ፍቅር ልባችን ውስጥ ስለሌለ ነው። ተነጋግሮ መግባባት ስላቃተን ነው። ሰው ተነጋግሮ መግባባት ካቃተው ለለውጥ የሚሆን ሀይል አያገኝም። ሰው ተነጋግሮ መግባባት ካልቻለ እውቀቱ፣ ጥበቡ ሁሉ ጥቅም መስጠት ያቆማሉ። ሰው ለራሱም ሆነ ለሌሎች አደገኛ መሆን የሚጀምረው በዙሪያው ካሉ ሰዎች ጋር መግባባት ያልቻለ ቀን ነው። ሰው ከሰውነት ወደ አውሬነት የሚቀየረው በውስጡ ተናግሮም ሆነ አድምጦ ከሰዎች ጋር መታረቅ ሳይችል ሲቀር ነው።
ሰው ከእንስሳት የሚለየው ማሰብ በመቻሉ ነው። የማሰብ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተነጋግሮ መግባባት ነው። የማሰብ የመጀመሪያው ገጽ በላሸቀ ሀሳብ የተፈጠሩ ችግሮችን በላቀ ምክረ ሀሳብ መፍታት ነው። ተነጋግረን ካልተግባባን መማራችን፣ ማወቃችን ጥቅሙ ምን ላይ ነው? ሰው የሚማረው እኮ ህይወቱን ቀላል ለማድረግ ነው። ትምህርት ከሌሎች ጋር አግባብቶ ህይወታችንን ካላቀለለልን መማራችን ዋጋ አይኖረውም። የሰው ልጅ በበላጭ ሀሳብ፣ በምክንያታዊነት ከሌሎች ጋር ተነጋግሮ ካልተግባባ ሰው ሊባል አይችልም። ምክንያቱም ሰውነት ከማሰብ ጀምሮ ወደ ላቀ የማንነት እርከን የሚሸጋገር ስለሆነ ነው። እኛ ግን ከዚህ ውጪ በሆነ የኑሮ ዘይቤ መከራችንን እያየን ነው።
ባለመግባባት መግባባት የሚፈጥርልንን መልካም እድል ማየት አልቻልንም። አሁን እኛ ባለመነጋገር መነጋገር የሚፈጥርልንን ሀገራዊ በረከት መቋደስ አልቻልንም። በጸለምተኝነት ብርሀናዊ ጎዳናችንን እያጸለምን ነው። ድልድይ እንስራ..ከዚህ እዚያ መሻገሪያ ድልድይ እንገንባ። በሀሳብ ተላቁጦ በአንድነት የተዋሀደ፣ በብዙ ምክረ ሀሳብ የጠነከረ የብረት መረማመጃ እንገንባ።
‹ሰው ከእንስሳት የሚለየው ማሰብ በመቻሉ ነው› የሚለው ይህ የልጅነት ጥበባችን ወረቀት ላይ ካልሆነ በስተቀር እኛ ላይ ነፍስ ሲዘራ አይታይም። በማሰብ የተራመድንው ጎዳና የለም። ችግሮቻችንን ስናስወግድ የነበረው በሀይልና በመገፋፋት ነበር። ሀይልና መገፋፋት ደግሞ የማሰብ መገለጫዎች አይደሉም። ማሰብ ሁልጊዜም መፍትሄ ነው የሚሰጠን። ማሰብ ሁልጊዜም ምክንያታዊነትን ነው የሚያላብሰን። ራሳችንን በሀሳብ እንገንባ። የሀገራችንን መሰረት በእርቅና በምክክር እናጽና። በማሰብ የተገነባ ሀገርና ትውልድ ለጦርነት የሚሆን ጊዜ የለውም።
በማሰብ የተገነባ ትውልድ ለፖለቲካም ሆነ ለማናቸውም ነውጠኛ ሀይሎች እጅ አይሰጥም። ሀገራችንን ያራቆትናት እኛው ነን። አባቶቻችን ያለበሷትን የክብር ዘውድ የነጠቅናት እኛ ነን። አባቶቻችን ያጎናጸፏትን የአንድነት ካባ ያወለቅነው እኛ ነን። እስኪ ለአፍታ ትላንትን መለስ ብላችሁ ተመልከቱት..ምናችንም እኮ አባቶቻችንን አይመስልም። ሰው እንዴት ከጀግና አብራክ፣ ከኩሩ ጉያ በቅሎ ሌላ ይሆናል? ሰው እንዴት በአንድነት አፍሪካን ፈጥሮ፣ አለምን አነቃንቆ አጠገቡ ካለ ወንድሙ ጋር አይጥና ድመት ይሆናል? እኛ ከአባቶቻችን ጋር ዱባና ቅል ነን። አባቶቻችንን እስካልመሰልን ድረስ የክብር፣ የስልጣኔ፣ የታሪክ ሀይል አናበጅም።
እንደ ሳምሶን አናት ሀይላችን የአባቶቻችን አንድነት ነው። እንደ ሙሴ በትር ክብራችን የአባቶቻችን ስርዐት ነው። ሳምሶን እግዚአብሄር አምላክ በቀባው ጸጉሩ ላይ ምንም ነገር የማድረግ ሀይል ነበረው። ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ሲያወጣ በበትሩ ላይ የእግዚአብሄር ሀይል ነበር። የእኛም ሀይል የአባቶቻችን የአንድነትና የወንድማማችነት መንፈስ ነው። የሳምሶን ሀይል የደከመው፣ ሳምሶን ሀይሉን ያጣው ክብሩን የትም ጥሎ በደሊላ የተረታ ቀን ነበር።
የእኛም ሀይል፣ የእኛም ክብር እያደፈ ያለው የአባቶቻችንን የአንድነት መንፈስ በብሄርና በጎሳ የመነዘርን ሰሞን ነው። ሳምሶን ወደ ክብሩ ይመለስ ዘንድ እግዚአብሄርን ማወቅና ወደ እሱ መመለስ ግድ ይለዋል። እኛም ወደ ቀደመ ክብራችን እንመለስ ዘንድ የአባቶቻችንን የፍቅር ልብሰ ተክህኖ መልበስ አለብን። ያለዛ በባዶ ሜዳ እዬዬ ከማለት በስተቀር የምንቀይረው አንዳች ነገር አይኖርም።
ለውጥ ፍቅር ይፈልጋል። ፖለቲካ መነጋገር፣ ተነጋግሮም መግባባት ግድ ይለዋል። አብዛኞቹ የፖለቲካ ጽንሰ ሀሳቦች ሀገርና ህዝብን መሰረት ያደረጉ ናቸው። በዚህ ጽንሰ ሀሳብ ውስጥ እውቅና ያገኙት ሀገርና ህዝብ ደግሞ ተግባቦትን መርህ ያደረገ፣ ንግግርን እንደ ፖሊሲ የቀረጸ መንግስታዊ ስርዐት ይፈልጋሉ። ይሄ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ ውስጥ የምንፈጥረው የጋራ ታሪክ አይኖረንም።
ባለማሰብ ውስጥ መቆም ባለመግባባት ውስጥ መፈጠር ነው። አለማሰብ ሁልጊዜም መድረሻው ጦርነት ነው። እስካሁንም እንደ ሀገር የፈጠርናቸው ችግሮቻችን ባለማሰብ የቃኘናቸው ስለሆኑ ነው። ለምንም ነገር የሰከነና አርቆ የሚያይ ልቦና ያስፈልገናል። ችግሮቻችንን ችግር በሚፈጥር ሀሳብ ሳይሆን ሰላም በሚያመጣ ሀሳብ ማሸነፍ መልመድ አለብን። ይሄን ሳናደርግ ፊተኝነት የማይታሰብ ነው። ነጋችን እንዲያብብ ዛሬ ላይ ምርጥ ዘሮች እንሁን።
ጥሩ ዘሮች ጥሩ አበባና ጥሩ ፍሬ ከመሆን ሌላ አማራጭ የላቸውም። የእኛም አማራጭ ሊሆን የሚችለው ጥሩ ዘሮች በመሆን ለትውልዱ ሰላሳና ስልሳ መቶም ማፍራት ነው። ነገ ላይ ትውልድ የሚጠረጥረው የእኛን የዛሬ ፍሬ ነው። ነገ ላይ ትውልዱ ገልጦ የሚያነበው የእኛን የዛሬ ታሪክ ነው። ነገ ላይ ትውልዱ ቀና የሚለው ወይም አንገቱን የሚደፋው በእኛ የዛሬ ሀሳብ ነው። የሀሳብ ፍሬአችን ነገ ለሚፈጠረው አዲስ ትውልድ የበረታ ጉልበት አለውና ሰው መሆን ይጠበቅብናል ። በሀሳባችን የትውልዱን ድልድይ እንገንባ። በተግባራችን ለሌሎች ድልድይ እንሁን። በእርቅና በተግባቦት የተጠረገ፣ ከዛሬ ወደ ነገ መሄጃ መንገድ እስካልሰራን ድረስ ከመተቻቸትና ከመነቃቀፍ አንወጣም።
ከጥንት እስከዛሬ የሀገራችን ስቃይ መነሻው ፖለቲካ ነው። ፖለቲካው የማይገባበት የማህበረሰብ ክፍል ስለሌለ እድፉ አይለቀንም። ይሄን እድፍ እናጠራ ዘንድ ብሄራዊ ምክክር አስፈልጓል። የብሄራዊ ምክክሩ ዋና አላማ በጋራ ሀሳብ የጋራ ሀገር መፍጠር ነው። በጋራ ሀሳብ የጋራ ሀገር ለመፍጠር ደግሞ በፖለቲካም ሆነ በሌላ ምክንያት የተበላሹ ችግሮቻችንን የምናሸንፍበትን የበረታ ሀሳብ ማዋጣት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ባለፉት ሀምሳ አመታት ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ብዙ ችግሮችን ፈጥረናል። እነዚህ ችግሮች ፈረሰው ድልድይ እንሰራ ዘንድ ሀገራዊ ምክክር የግድ ይላል። ሀገራችንን እያሰቃያት ያለው እንዲህ አይነቱ በሀሳብ አንሶ በችግር የመላቅ አባዜ ነው።
በሀሳብ አንነስ ..በሀሳብ የምናንስበት ጊዜ ያበቃል ፤ ምክንያቱም የሀገራዊ ምክክሩ አላማ በሀሳብ የላቀ ማህበረሰብ መፍጠር ነው። ከትላንት ጀምረን እሹሩሩ ስንላቸው የነበሩ ችግሮች አሉ። ከማን እንደጸነስናቸው ሳናውቅ በውሸት ያረገዝናቸው፣ አርግዘንም የወለድናቸው፣ ወልደንም እያረስናቸው ያሉ ዛሬ ላይ እኛኑ እያጠቁን ያሉ ችግሮች ግብዐተ መሬታቸውን ለማፍጠን ያለን አማራጭ መነጋገር ብቻ ነው።
ባለ ማሰብ፣ ባለመግባባት፣ ባለመነጋገር የአእምሯችንን በር ቆልፈን ጊዜ ያለፈባቸውን ድርጊቶች እየከወንን ጊዜው ያለፈበት ሀገርና ህዝብ ፈጥረናል። አሁን የምፈራው ለምንም የማይጠቅም ወደ ኋላ የሚያስብ ጊዜ ያለፈበት ትውልድ እንዳንፈጥር ነው። ሁሉም ነገር በእኛ እንዲበቃ ለሚመጣው ትውልድ ስንል መስዋዕት መክፈል አለብን። እኛ ላይ የሆነው የጦርነት፣ ያለመግባባት ስቃይ በልጆቻችን ላይ እንዳይደገም ዛሬ ላይ የእርቅ መሀላ እንፈጽም።
ሀሳብ በሀሳብ እንጂ በጦርነት አይሻርም። ሀሳቦቻችንን በሀሳብ የመምረጥ ጥበብን እንማር። ዛሬ ላይ ከተቀረው አለም በብዙ ነገር ወደ ኋላ ቀርተናል። ኢትዮጵያዊነት ያነጸውን የአባቶቻችንን የአንድነት ድልድይ ዛሬ ላይ በብሄር ሸር ሽረንዋል። የአባቶቻችንን የፍቅር ድልድይ ዛሬ ላይ በኔነት አፍርሰነዋል። የዛን ትውልድ የጽናት ድልድይ ባለመግባባት ንደነዋል። ወደ ድሮ እንመለስ ዘንድ የፍቅር አሻራ ያረፈበት የይቅርታ ድልድይ ግድ ይለናል።
በአንድ አይነት ግጥም፣ በአንድ አይነት ዜማ አንድ ላይ ሆነን ስለሀገራችን የምንዘምርበት ጊዜ ላይ ነን። ፊተኝነት እንደናፈቀን እንዳይቀር ከኋላ ያስቀሩንን ችግሮቻችንን አሸንፈን መቆም ይጠበቅብናል። የጥንቱን የአንደኝነት ክብራችንን ለመመለስ ብሄርን ሳይሆን ሰውነትን ያስቀደመ የፖለቲካም ሆነ የማህበራዊ እሴት ያስፈልገናል። አለም በየቀኑ ሌላ አይነት ናት..እኛ ግን ሁልጊዜም አንድ አይነቶች ነን። ለውጥ ደግሞ የተለየ መሆን ይፈልጋል..ከዘመኑ ጋር የዘመነ፣ ከጊዜው ጋር የተስተካከለ አእምሮና ልብ ይፈልጋል። አዲስ እንሁን።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 /2014