
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ከተሞች መሪ ፕላኖቻቸውን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻላቸው ለእድገታቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ገለጸ፡፡ የዓለም አቀፍ ከተማ ደረጃ ለመድረስ እንዲሁም ለነዋሪዎቹ ምቹ ለመሆን ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አማኑኤል ተሾመ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ከተሞች መዋቅራዊ ፕላኖቻቸው መሬት ባለመንካታቸው መዋቅራዊ ፕላኑ የሚለውና እነሱ የሚያድጉበት አቅጣጫ ፍፁም የተለያየ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ አዲስ አባባ ከተማን ጨምሮ የኢትዮጵያ ከተሞች የዓለም አቀፍ ከተማ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ርቀት ላይ ናቸው፡፡
ከተሞቻችን መዋቅራዊ ፕላን ቢወጣላቸውም፤ በፕላኑ መሰረት እያደጉ አይደለም፡፡ በሁሉም ደረጃ ያሉ ከተሞች መዋቅራዊ ፕላን ያለመተግበር ችግር አለባቸው ብለዋል፡፡ ለአብነትም አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ከተማ ደረጃ ለመድረስና ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ለማድረግ ብዙ ስራዎች ይቀሯታል፡፡ የከተሞች መሪ ፕላን (እቅድ) መሬት ሊነካ ባለመቻሉ ለከተሞች እድገት እንቅፋት ሆኗል፡፡ ይህን ለመቀየር የኢትዮጵያ ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ ብዙ መስራት ይጠብቃቸዋል፡፡
ነገር ግን እንደከተማ ተዋቅሮ እቅድ ውስጥ ተካትቶ ባይሰራም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማን ገፅታ ለመቀየር የሚደረጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሙከራዎችና ውጤቶች ለአገራችን ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተስፋ ሰጪ ቢሆኑም እንደነሱ አይነት ብዙ ፕሮጀክቶች ያስፈልጉናል፡፡ ከተማዋ ለነዋሪቿና ለጎብኚዎች ምቹ ከተማ እንድትሆን ገና ብዙ የቤት ስራዎች ይጠብቋታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት እንደአንድ ትልቅ አልሚ የከተሞችን እቅድ ሲወጣ ተከታትሎ በማስፈፀም፣ መስመር በማስያዝና በማስተግበር ዋና መሪነት ሚናውን ሊጫወት ይገባል። ስትራቴጂክ የሚባሉ ፕሮጀክቶችን መንግሥት ቀድሞ በመስራት ለሌሎች አልሚዎች አርአያ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
መሰረተ ልማቶች ለከተሞች ምቹነት ቁልፍ ሚና ስላላቸው እነሱ ላይ ትኩረት በማድረግ እንደቅደም ተከተላቸው ቅርጽ መያዝ እንደለባቸው የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፣ ለአብነትም እንደአብርሆት አይነት ቤተ መጻሕፍት በአዲስ አበባ በየአካባቢው ያስፈልጋል ብለዋል።
የከተሞችን እድገት ቅርጽ ለማስያዝና በእቅድ እንዲመራ ለማድረግ የሰው ሃይል ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል ነው ያሉት አቶ አማኑኤል፤ ከተማ ላይ የሚፈፀመው የጥፋት ውጤት ወዲያውኑ የሚታይ ባለመሆኑ በሙያቸው ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ባለሙያዎችና አመራሮች በጥንቃቄ መመደብ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
በተለይ በፕላንና ልማትና መሰል መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ ባለሙያዎችና አመራሮች ለከተሞች እድገት በጣም ወሳኝ ባለሙያዎች በመሆናቸው በእነሱ ብቃት ላይ የተለየ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
እንደ አቶ አማኑኤል ገለጻ፤ ውጤቱ የሚታየው በባለሙያዎቹ ብቃት ልክ ነው፡፡ ጥሩ ባለሙያዎች ካሉ ጥሩ ውጤት ስለሚኖረው ከተሞች በተለይም አዲስአበባ ጥሩ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች መመራት የተሻለ ነው፡፡
ፀጋዬ ጥላሁን
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2014