ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እንደ ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ስራ የበዛበት በዓለም ስለመኖሩ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም። ይህ ሰራዊት በዚህች ጥቂት ዓመት በብዙ ተግዳሮቶች ውስትጥ አልፏል፣ በከሃዲዎች ጀርባውን ተወግቷል፣ በራሱ ወገን ግፍ ተሰርቶበታል። ከመደበኛ ጦርነት ውጪም እዚህም እዚያም የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ለማስቆም ሌት ተቀን እየተጋ ነው ።
ይህ ሰራዊት በዋናነት የአገርን ዳር ድንበርን ከውጪ ወራሪ ሃይሎች በመጠበቅ ላይ ብቻ አልተወሰነም። በተለያዩ ክልሎች ሽብርተኛ ቡድኖች ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት የግፍ ግድያና ዘር ተኮር ጭፍጨፋ፣ግጭቶችና ሌሎችም ተመሳሳይ የጸጥታ ችግሮች ለሰራዊቱ ተጨማሪ ስራ ሆነውታል።
አገር እንዲህ በውጪም በውስጥም ጠላቶች እንደ ቆዳ ተወጥራ ባለችበት በዚህ ወቅት መከላከያ ሰራዊት በትንንሽ ግዳጆች ሲባክን ማየት አገርን ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ብሎ ለመናገር ወታደራዊ ምሁር መሆንን አይጠይቅም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከገንዘብ፣ከቁሳቁስና ከሞራል ድጋፍ ባለፈ በምን መልኩ ሊደግፈው ይገባል የሚለው ጥያቄ የዚህ ጽሁፍ ዋንኛ ማጠንጠኛ ነው ። የዚህ ጥያቄ ምላሽ የሁሉንም ኢትዮጵያዊና የክልል መንግስታት ጥንካሬ እና ቀናኢነትን የሚሻ ይመስለኛል ፡፡ መከላከያ ሰራዊት እንዲህ በየቦታው በትንንሽ ግዳጆች እንዲወጠርና ስራ እንዲበዛበት ካደረጉ ምክኒያቶች በቅድሚያ ጥቂቱን መመልከት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የመፍትሄው አካል እንዲሆን ሞራል ይሰጣልና በስሱ እንመልከተው።
የፈረደባት ይህች ሰኔ ወር የኢትዮጵያውያን የፈተናና የክፉ ወር መገለጫ እየሆነች መምጣቷ ለምን ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከሁሉም ይቀድማል። በግልጽ እንደሚታወቀውና ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደተስተዋለው ሰኔ በመጣ ቁጥር ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በየደረጃው የሚካሄደውን የውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል የውጪ ሃይሎች የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ለዚህም የውጪ ሃይሎች በቀጥታ ወረራ መፈጸም ባይችሉ እንኳን የአገር ውስጥ ባንዳዎችን ተጠቅመው ቢቻል አገር እንድትፈርስ ካልተቻለም እንዳትረጋጋ ለማድረግ ቁጭ ብለው እንደማያድሩ ለማንም ግልፅ ነው።
ሌላው ቢቀር ሰሞኑን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ በርካታ ዜጎች በራሳቸው አገር ወታደሮች እየተገደሉ ባለበት ሁኔታ የሰው ድንበር ገብቶ ‹‹በጣት የሚቆጠሩ ወታደሮቼ ተገድለዋልና ጦርነት ካልገጠምኩ›› የሚል ጩኸቴን ቀሙኝ አይነት ጫጫታ ለምን እንደተፈጠረ ነጠብጣቦችን መገጣጠም ኢትዮጵያ ላይ ስለሚዶለተው ሴራ ግልጽ ስእል ይሰጣል ።
ይህ እንዳለ ሆኖ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በአንድ ጊዜ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች በግልጽ መከላከያ ሰራዊትን አንድ ቦታ ላይ ትኩረት እንዳያደርግና በየቦታው በትንንሽ ችግሮች እንዲወጠር(decentralize) የማድረግ የውጪም የአገር ውስጥም ጠላቶች ስትራቴጂ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።
ሰራዊቱን የውጪዎቹም ሃይሎች ይሁኑ የአገር ውስጥ ባንዳዎች ይፈሩታል። ገና ስሙ ሲጠራ የሚርዱ የጠላት ሃይሎች ይህ ሰራዊት ትኩረቱን አንድ ቦታ አድርጎ ተረጋግቶ ሊገጥሙት አይደለም ሊሞክሩት አይደፍሩም።ያላቸው ምርጫ ሰራዊቱ አንድ ቦታ ላይ ትኩረትና ሃይሉን እንዳይሰበስብ በማድረግ አቅሙን ማሳሳት ነው። ከዚያም እድላቸውን መሞከር ነው።
ይህ ስትራቴጂ ሰራዊቱን በብሔር መከፋፈል የተሰኘ ሌላም ገጽ አለው። ይህ አልተሳካም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ሆኖ አሳፍሯቸዋል። ለዚህ ደግሞ አንድ ግልጽና ግልጽ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል። በየአካባቢው በሚነሱ የጸጥታ ችግሮች ለመከላከል በወሰዳቸው ግዳጆች ይህንን በተጨባጭ አስመስክሯል፤ መካድ አይቻልም።
እርግጥ ነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዲህ ስራ ቢበዛበትም አገር ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከትና ለማስቀረት አቅሙም ዝግጅቱም አለው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ ደጋግመው ስለመከላከያ ሰራዊቱ የሚናገሩትም ይህንኑ ነው። ሰራዊቱ የሚዘጋጀው አገር ውስጥ እዚህም እዚያም ተበታትነው በንጹሃን ዜጎች ላይ የሽብር ተግባር ለሚፈጽሙ ቡድኖች አይደለም።
የሰራዊቱ ዝግጅትና አቅም ከዚህም ይልቃል። ሰራዊቱ ይህን ታላቅ አቅም ስላለው ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በትንንሽ ግዳጆች እንዲወጠር መፍቀድ የለበትም። መንግስትም ቢሆን ይህን ጉዳይ ሳያስበው አይቀርም። ጉዳዩ አሳሳቢ ባይሆን እንኳን መከላከያ ሰራዊት በአንድ ቦታ ላይ ትኩረቱን ሰብስቦ ዝግጁ ሆኖ መቆየቱ የአገር ጠላቶች የሚፈልጉትን ጥቃት መፈጸም አይደለም እንዳያስቡት ሊያደርግ ይችላልና ሃሳቡ አይናቅም።
በዋናነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ ከአካባቢው የጸጥታ አካላት ጋር በቅርበትና በመናበብ መስራት ይጠበቅበታል ። በየትኛውም እርከን ላይ ያሉ የጸጥታ አካላትም በተመሳሳይ ከሕዝብና በየክልሎቹ ከሚገኙ የተሻለ ዝግጅት እንዲሁም አቅም ካላቸው የጸጥታ አካላት ጋር ተናበው በመስራትና ለሚፈጠሩ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የደህንነት አገልግሎቶች አቅም ተጠናክሮና ዘምኖ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ማነፍነፍ እንዲችሉ ማድረግ ከተቻለ በውስጥ ጠላቶች የሚፈጠሩ ችግሮች ከአካባቢ ታጣቂዎችና ከክልል ልዩ ሃይሎች አቅም የበለጡ ሊሆኑ አይችሉም ። የሚፈጠሩ ችግሮች የቱንም ያህል ከአቅም በላይ ቢሆኑ እንኳን እንደሰሞኑ ምንም አይነት ጦር መሳሪያ ባልታጠቁና ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጠሩ ዘግናኝና አሳፋሪ ጭፍጨፋዎች የመደገም እድላቸው ጠባብ ይሆናል።
ይህን ተፈጻሚ ማድረግ ከተቻለ መከላከያ ሰራዊቱን በትንንሽ ግዳጆች ከመባከን ተረፈ ማለት ነው። በዚህም ትኩረቱን በሌሎች ዋና ዋና ችግሮች ላይ ማድረግ ይቻለዋል። ይህም ኢትዮጵያ በውስጥ ለሚገጥሟት ፈተናዎች ረጅም እጃቸውን የሚያስገቡ የውጪ ሃይሎች ቆመው እንዲያስቡ በማድረግ ችግሩን ከምንጩ የማድረቅ ርምጃ ሊሆን ይችላል።
ይህን ተፈጻሚ ለማድረግ ኢትዮጵያ ያለችበት የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ግን ሕዝቡን የሰላም አቅም አድርጎ ማደራጀትና ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም ማድረግ ከመንግስት የጸጥታና የደህንነት አካላት የሚጠበቅ ጥልቁ ስራ ነው ። የክልል መንግስታት እስከ ቀበሌ ባለው የስልጣን እርከን የሚገኙ የጸጥታ አካላት የስራ ሃላፊዎችን ቁርጠኝነት እንዲሁም የፖለቲካ ታማኝነት ፈትሸው ውስጣቸውን ከባንዳዎች ማጽዳት ለነገ የሚሉት የቤት ስራ መሆን የለበትም። በሁለት ቢላ ከሚበሉ አካላት የተነሳ ንፁሀን የነፍሰ ገዳዮች አሰቃቂ ጥቃት ሰለባ መሆን የለባቸውም። ለዚህ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ወሳኝ ነው ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 /2014