የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ የካፒታል ገበያ እንዲፈጠርና የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ዘመኑ በሚፈልገው ደረጃና ይዘት እንዲጓዝ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል። በዚህም እ.ኤ.አ እስከ 2020 በአገሪቱ የካፒታል ገበያ እውን እንደሚሆን ይፋ አድርጓል።
የካፒታል ገበያ ዓለም አቀፍ ተሞክሮው እንደሚያመለክተው፤ ትልልቅ ኩባንያዎች የሚሳተፉበትና የሚሰሩበት ብቻ ሳይሆን ራሱም በሂደት ትልልቅ ኩባንያዎችን የመፍጠር አቅም አለው። በዚህም ሀብት ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች በሚያመነጩት የፈጠራ ሃሳብ አማካኝነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምቹ መደላድል ይፈጥራል።
መንግስትም እንዲህ ያለውን የገበያ ሥርዓት በአገሪቱ ለማስተዋወቅ ሲያስብ መሰረት የሚያደርገው በመንግስት እጅ ያሉትን ኢትዮ ቴሌኮም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኤሌክትሪክ ሃይልን የመሳሰሉ ትልልቅ ተቋማትን፤ እንዲሁም ግዙፍ የሃይል ማመንጫዎችን የተወሰነ ድርሻ በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ይዞታ እንዲተላለፉ በማድረግ ነው። እንዲህ ሲሆን ተደጋግሞ እንደሚነገረው መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚያስጠብቅ ይታወቃል።
ሁሌም አዲስ ነገር ሲጀመር ሁልጊዜ መልካሙን ብቻ ይዞ ይመጣል ማለት አይደለም። ይልቁንም ብዙ ተግዳሮቶችንና ቀደም ሲል የማይታወቁ ችግሮችን ሁሉ ሊይዝ ይችላል። እነዚህ ሁሉ ታዲያ እንደ ፈተና ታይተው ችግሮችን አስቀድሞ በመተንበይ የሌሎችን ልምድ በመቀመር እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይቻላል። ይገባልም። ምናልባት ቢከሰቱም፤ በጊዜያዊነት አስቦ በዘላቂነት እንዳይኖሩ ለማድረግ መስራት ተገቢ ነው።
እንዲህ ዓይነቱን የመንግስት አካሄድ የዘርፉ ባለሙያዎች በአብዛኛው ይደግፉታል። የባለሙያዎቹ ድጋፍ የሚመነጨውም በገበያው የአክሲዮን ግዥ ተሳታፊ ሆነው ስለሚጠቀሙት የሀገሪቱ ዜጎች፤ በአክሲዮን ሽያጩ ስለሚሰፍነው የሀብት ክፍፍል በማሰብና ሌሎች ተጨማሪ የኢንቨስትመንት እድሎች መኖራቸውን ታሳቢ አድርገው ነው። እነዚህ ሁሉ ተደምረው ደግሞ የአገርን ኢኮኖሚ የማሳደግ፤ ሥርዓቱን የማዘመን ውጤት ይኖራቸዋል።
ይህ ሲሆን ግን፤ አስፈላጊው ዝግጅትና ቅድመ ሁኔታ መኖር አለበት። የካፒታል ገበያ የሚመራበት የራሱ የህግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል። ይህ የህግ ማዕቀፍ ዓለም አቀፉን ሁኔታ ያገናዘበ፤ የሀገሪቱ ፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ያጣቀሰ፤ የመንግስትንና የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ መቀረፅ ይኖርበታል። ይህ የገበያ ሥርዓት በራሱ ከኩባንያዎቹ የሚጠይቀው ግልፅነትና ደረጃውን የጠበቀ የሂሳብ አያያዝ ሥርዓት፤ እንዲሁም ሽርክናውና ሸሪኮቹ የሚተዳደሩበት ህግና ደንቦች ዓለም አቀፉን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ መዘጋጀት አለባቸው። ለዚህም አገር በቀሎቹ ኩባንያዎች መዘጋጀት አለባቸው።
እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ህግና ሥርዓትን የሚያስከብሩ፤ የካፒታል ገበያውን የሚመሩ አስፈላጊ የህግ ማዕቀፎችን የሚያወጣና መስፈርቶችን የሚያዘጋጅ፤ እነዚህንም በአግባቡ የሚያስተዳድርና የሚመራ ተቋም መገንባት አለበት።
የካፒታል ገበያ በሥርዓት ከተመራ የውጭ ባለሀብቶችን በህግ አግባብ የሚጋብዝና የሚያመጣ በመሆኑ እንደ አንድ የውጭ ምንዛሬ ሀብት ማመንጫ የሚታይ ነው። በመሆኑም በዚህ አዲስ የገበያ ምህዳር አገር በቀል ባለሀብቶች፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል የማመቻቸት ስራ ከወዲሁ ሊሰራ ይገባል። እስካሁን በመንግስት ስር ያሉ፤ ነገር ግን በደረጃውና በሽርክና ወደ ግል ይዞታ የሚሻገሩትን ተቋማት በተመለከተ የሀገርን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ የማሸጋገር ስራው መተግበር ይኖርበታል።
ከሁሉም በላይ ለዚሁ አዲስ ለሚተገበረው የካፒታል ገበያ አጀማመር አፈፃፀምና በውል ስር ሰድዶ እንዲዘለቅ ለማድረግ የዘርፉ ባለሙያዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ኃላፊነታቸውም የሀገርን ጥቅምና የመንግስትን ፍላጎት የሚያሳኩ ልምዶችን በመቀመር ደረጃውን የጠበቀ የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት፤ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
የኢፌዴሪ መንግስትም ከዓመታት በኋላ ይሳካል ያለውን አገራዊ ህልም ዕውን ለማድረግ፤ የካፒታል ገበያ የሚመራበትን ሥርዓት ከማደራጀት፤ አሰራሩን ዘመናዊና አቅም በሚፈቅደው ልክ ማድረግ፤ ከሀገርና ከመንግስት ጥቅም፤ እንዲሁም ባለሀብቱ አመኔታ የሚጥሉበት እንዲሆን በሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት መመራት ይገባዋል። በዚህም የካፒታል ገበያው እውን ማድረግ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2011