ስፖርትና ሰላም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው።ስፖርት ሰላምንና አብሮነትን እንዲገነባ ውድድሮች ትልቅ መድረክ ናቸው።ውድድሮችን ለማካሄድ ደግሞ ሰላማዊ አውድ ያስፈልጋል።ይህንን በገንዘብ የማይተመን የስፖርት ጥቅም ለህብረተሰቡ በማቅረብ ረገድ የተለያዩ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ይህንን ታሳቢ በማድረግም የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልቂጤ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።መጠሪያውን ከቋንቋው የተዋሰውና ‹‹ኬር ኦድ›› የተሰኘው ይህ የጎዳና ላይ ውድድር ‹‹ለኢትዮጵያ ሰላም እንሩጥ›› በሚል መሪ ሃሳብ ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ ከ20ሺ ያላነሱ የከተማዋን ነዋሪዎች በማሳተፍ ከትናንት በስቲያ ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ ስፖርት በውጤታማነት ቀዳሚ በሆነው አትሌቲክስ በርካታ ውጤታማ አትሌቶችና አሰልጣኞችን ማፍራት ተችሏል።ይሁንና አገሪቷ በስፖርቱ እንዳላት አቅምና የተፈጥሮ ሁኔታ በሚገባት ልክ ተጠቃሚ ለመሆን አልቻለችም።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቂት የአትሌቲክስ ውድድር የሚያካሂዱ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በመታየት ላይ ይገኛል።ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የኬር ኦድ የጎዳና ላይ ሩጫ ነው።የጉራጌ ዞን ያፈራቸው የአትሌቲክሱ ዓለም ከዋክብት የቀድሞ አትሌትና በዚህ ወቅት በግሎባል ስፖርት ማኔጅመንት የኢትዮጵያ ተወካይ ሆኖ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው ተሰማ አብሽሮ፣ ወንድሙ አትሌት አየለ አብሽሮ፣ የኦሊምፒክ ቻምፒዮናውና የ10ሺ ሜትር ፈርጥ የሆነው ወጣቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የስፖርቱ ባለሙያዎችና ወዳጆች የተመሰረተ ማህበር ነው።ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ውድድሩን ሲያካሂድ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ በወልቂጤ ከተማ እጅግ ደማቅ በሆነ መልኩ አካሂዷል፡፡
በውድድሩም ላይ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስተር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቢኒያም ምሩጽ ይፍጠር፣ የጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ ስመጥር አትሌቶችና አሰልጣኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል።
15 ኪሎ ሜትር በሸፈነው ውድድር ላይም በወንዶች ወጣቱ አትሌት ድንቃለም አየለ አሸናፊ ሆኗል።በአፍሪካ ቻምፒዮና 5ሺ ሜትር ውድድር 4ኛ ደረጃን በመያዝ የዲፕሎማ ባለቤት የነበረው አትሌቱ፤ የአየር ሁኔታውና ሩጫው የሚደረግበት ስፍራ ውድድሩን ፈታኝ እንዳደረገበት ተናግሯል።በሴቶች ደግሞ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የኦሊምፒክ ብር ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችው ጠንካራዋ አትሌት ሶፊያ አሰፋ በሴቶች ዘርፍ በቀዳሚነት ማጠናቀቅ ችላለች።አንጋፋዋ አትሌት መሰል የሃገር ውስጥ ውድድሮች መብዛታቸው ለአትሌቶችም ሆነ ለስፖርቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁማለች።
የኬር ኦድ ልማትና ስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ፤ ኬር ኦድ የሚለው ቃል በራሱ ፍቅርና አንድነትን የሚሰብክ መሆኑን ይገልጻል።የሩጫው ዓላማም ሰላምን መስበክ በመሆኑ ሁሉም በያለበት ይህንኑ ሃሳብ ማስተላለፍ እንደሚገባም አሳክቷል።የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ሰላምን ማዕከል በማድረግ ከመሮጥ ባለፈ ስለ ኢትዮጵያ ሰላም ሁሉም የሚገባውን ማድረግ እንዳለበት ጠቁማለች።
ሩጫው ያነገበው ዓላም ጥልቅ እና ትልቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ፤ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ናቸው።ይህ ወቅት ኢትዮጵያ በበርካታ የውጪና ውስጣዊ ችግሮች ውስጥ እያለፈች ያለችበት በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሰላም ባለፈ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል።በመሆኑም ከሩጫው ጎን ለጎን ለሰላም መረባረብ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
ውድድሩን ከአንድ እስከ ስድስት ባለው ደረጃ አጠናቀው መግባት የቻሉ አትሌቶ ከ75ሺ እስከ 5ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።የዚህ ውድድር አካል የሆነና 10ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የሩጫ ውድድር በቅርቡ በቡታጅራ ከተማ የሚደረግ ሲሆን፤ በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው የወልቂጤ ሶስተኛው ዙር የ15 ኪሎ ሜትር ውድድር ጀምሮ ከተለመደው የሰኔ ወር ወደ ግንቦት ወር ተቀይሮ እንደሚደረግም ተጠቁማል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2014