ቦታው ቦሌ ክፍለ ከተማ ነው። በቅርቡ ተገኝተን እንዳስተዋልነው በክፍለ ከተማው ሁለት ወረዳዎች በሚገኙ ፋና እና ንስር ሸማች ማህበራት አልሚ ምግቦች ክፍፍል ተካሂዷል። ብዙ ነፍሰ ጡር እናቶች፤ አጥቢ (እመጫት) እናቶች በመርሐ ግብሩ ታድመዋል። ዕድሜያቸው ከወር ጀምሮ እስከ ሦስት ዓመት የሚገመት ሕፃናትን ያቀፉና ያዘሉም ይገኙበታል። ከእናቶቹ አንዳንዶቹ ፈዘዝ ያሉ ይመስላሉ። ያቀፉና ያዘሏቸው ሕፃናት የፋፉ አይደሉም። ቀጫጭንና መጠናቸው ትንንሽ ነው ። ክብደታቸው ቀላል ለመሆኑ በእቅፍና እዝላቸው ውስጥ ጎልተው አለመታየታቸው ይመሰክራል። ከታቀፉትና ከታዘሉት ሦስት ዓመት የሞላቸው ሕፃናት ከሌላው ሰውነታቸው ይልቅ ሆዳቸው ጎልቶ ይታያል። የእጅና የእግር አጠቃላይ አካላቸው ከሲታ ነው። ሰውነታቸው የጫጫ ይመስላል። እንደአዋቂዎቹ የፊት ገጽታዎች ፈዝዘዋል። ንቁና ደስተኛ አይመስሉም።
ሁኔታቸው ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ተጉዤ ስለተመጣጠነ ምግብ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ የተማርኩትን አስታወሰኝ። በተለይ ተመጣጣኝ ምግብ እጥረት ያለበት ሰው በከፍተኛ ሁኔታ የሰውነት ክብደቱ እንደሚቀንስ ፤ ኃይል እንደሚያጣ ፤ ገጽታው ላይ መፍዘዝ የሚታይበት የመሆኑ ምልዕክት መጣልኝ።
ወይዘሮ ዘቢደሩ በላይ እንደነገሩን የያዟት ሕፃን ሦስት ዓመት ሆኗታል። ፊቷ ድንቡሽ ያለ ነው። አስተያየቷ ፍዝ ይመስላል። ምክንያቱም ዓይኗ ለረጅም ጊዜ ዕይታ ውስጥ ቢሆንም ትኩረቷ ምንም ዓይነት ነገር ላይ እንዳላረፈ በግልፅ ይስተዋላል። ወይዘሮዋን ከዚህ በፊት አልሚ ምግቦችን መግበዋት ያውቁ እንደሆን ጠየቅኳቸው። እሳቸውም ዓይናቸውን ካተኮሩበት ሳያነሱ ከየት መጥቶ ለእንጀራ በሽሮውም በሆነልኝ ሲሉ ነበር የመለሱልኝ ። እንደመልሳቸው ሕፃኗ ብዙም ጤና የላት። በቅርቡ ሆስፒታል ወስደዋት ፕሮቲን እጥረት አለባት ተብላለች። በቦታው የተገኙት በወረዳው በደሃ ደሃ ተመልምለው አልሚ ምግብ ውሰዱ ተብለው በመሆኑ እጥረቱን ይተካላታል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
ወይዘሮ ዓለምፀሐይ በዳዳ የፊት ገጽታዋ ሲስተዋል ሃሳብ የገባው ይመስላል። እንዳወጋችን በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 3 ነዋሪ ነች። ያዘለችውን የአንድ ዓመት ልጅ ጨምሮ ሦስት ሕፃናት ልጆች አሏት። ቀደም ሲል የቤተሰብ ምጣኔ ግንዛቤ ያላት ባለመሆኑ በዓመት ልዩነት ነው የወለደቻቸው። ሁለቱ ሆዳቸው ጎልቶ ቢታይም ሌላው ሰውነታቸው የመነመነ ሆኖ ይታያል። ሲጫወቱ በተደጋጋሚ ይወድቃሉ። ያለቅሱና ይነጫነጫሉም። ታናሻቸው ቢሆንም ታላቃቸው የሚመስለው ያዘለችው ሕፃን ነው። ተመጣጣኝ ምግብ ልትመግባቸው የሚያስችል ገቢ የላትም። የምትደዳደረው ቋሚም ባይሆን ባለቤቷ ያገኘውን ሰርቶ አልፎ አልፎ በሚሰጣት ገንዘብ ነው። ይሄ በሸማች ማሕበሩ እንደተሰጣት ያለውን የቆርቆሮ ወተት፣ ፓስታ፤ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ አልሚ የሚባሉትን ምግቦች መሸመት ቀርቶ ለዕለት ዳቦ መግዣም አይበቃም ። ልጆቿ በአብዛኛው በእናት ጡት ወተት ቢያድጉም ከስድስት ወራቸው በኋላ በቂ ወይም ተጨማሪ የሚባለውን ምግብ አላገኙም። በመሆኑም በየጊዜው ይታመማሉ። ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት የአልሚና የተመጣጣኝ ምግቦች ድጋፍ ተሰጥቷት አታውቅም ። ድጋፉ ሲደረግላት የመጀመርያዋ ነው።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ የሆነችው ወጣት መስከረም ወንድሙ ሌላዋ የድጋፉ ተጠቃሚ ናት። ከጉራጌ ዞን ዶቤ ከሚባል አካባቢ ነው የመጣችው። የግለሰብ ቤት ኪራይ ውድ በመሆኑና አቅሜ ስለማይፈቅድ በጉልበቴ እያገለገልኩ ዘመድ ጋር ተጠግቼ ነው የምኖረው የምትለው መስከረም ቋሚ የምትለው ሥራ የላትም። ኑሮዋን ያገኘችውን በተለይም ሹሩባ እየሰራች ስትገፋ ነው የቆየችው። ልጅ ከወለደች በኋላ ግን ስላላመቻት አቁማዋለች። የዘጠኝ ወር ሕፃን ልጇንና ራሷን መመገብ የሚያስችላት የተለያዩ ተመጣጣኝና አልሚ ምግቦችን በነፃ አግኝታለች። ዘይትን ጨምሮ ዱቄት፣ የቆርቆሮ ወተት (ኒዶ ) ፣ ምስር ክክ፣ ማኮሮኒ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ካገኘቻቸው ይጠቀሳሉ። የተመጣጠነና የአልሚ ምግብ ድጋፉን በዚህ ኑሮ ውድነት ማግኘት ለእሷ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ድጋፉ ክረምቱን ሙሉ ዘላቂ ነው መባሉ ተስፋዋን አለምልሞላታል። ድጋፉን ሳገኝ የመጀመሪያዬ ነው የምትለው መስከረም በነፍሰ ጡርነቷ ብታገኘው ሕፃን ልጇ የበለጠ ዕድገቱ የሰመረ ይሆን እንደነበር ለ15 ቀን በወሰደችው ከአመጋገብ ጋር የተያያዘ ስልጠና መገንዘቧንም ትናገራለች።
እናቶች ነፍሰ ጡር ሲሆኑ ለራሳቸው ከሚያስፈልጋቸው ምግብ በተጨማሪ ለፅንሱ ዕድገት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ተመጣጣኝና አልሚ ምግቦችን መመገብ እንዳለባቸው ተገንዝባለች። ከስልጠናው እናት ሕፃኑን ከፀነሰችበት እስከ ውልደቱ ባሉት 270 ቀናት የአመጋገብ ሥርዓት ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም መረዳቷን ታወሳለች።
ከሥልጠናው በፊት ግንዛቤ ባይኖረኝም ለልጄ እስከ ስድስት ወር ጡቴን አጥብቸዋለሁ። አሁንም እያጠባሁት ነው። በተጨማሪም ጡቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁለት ዓመት እስኪሞላው ተጨማሪ ምግቦችን እየመገብኩት እገኛለሁ። ድጋፉ ልጄን በዘላቂነት እንድመግብ ይረዳኛል ብዬ አስባለሁ ብላናለች በቀጣይነቱ ላይም ተስፋ እንዳላት በማከል።
ራሴን አሞኛል። በጣም እያዞረኝ ነው ስትል ትክዝ፤ ፍዝዝ፤ ቅዝዝና ድክምክም እንዳለች ለጥቂትና አጭር ጥያቄዬ የሰለቸ በሚመስል ስሜት መልስ የሰጠችኝ ወይዘሮ ሀና ደጉ ነች። እንደመልሷ ድጋፉን ስትወድስ ያገኘኋት አንድ ዓመት ከሰባት ወር ዕድሜ ባለው ሕፃን ልጇ አማካኝነት ነው። ልጇ ተመጣጣኝና አልሚ ምግቦችን በማግኘቱ ዕድለኛ ነው ባይ ነች። በሕፃናት አስተዳደግና አመጋገብ ዙርያ ለ15 ቀን በተሰጣት ሥልጠና ዕድሉን ማግኘት የነበረበት ከስድስት ወር በኋላ መሆኑን በመረዳቷ ልጇ ተጨማሪ ምግብ ከሚያስፈልገው ወቅት ተላልፎ ቢሆንም አልሚ ምግቡ ደርሶለታል ትላለች። ያገኘችው ድጋፍ በእህል፣ በእንስሳት ተዋጽኦ፤ በአትክልትና ፍራፍሬ መበልፀጉን ታወሳለች። ስራ ስለሌላትና መግዣ ገንዘቡ ስላልነበራት ፤ የነዚህን ውህዶችና በንጥረ ነገሮች የበለፀገ ገንፎ ዱቄት አዘጋጅታ ባለመስጠቷ ከዚህ ቀደም የወለደችው የ10 ዓመት ልጇ የጓደኞቹን ያህል የትምህርት ፍላጎት የለውም። ትምህርት ቤት ቢሄድም ለትምህርቱ ትኩረት አይሰጥም ። አቀባበሉም ደከም ያለ እንደሆነ መምህራኖቹ እንደነገሯት ትገልፃለች። በአንዳንድ ነገሮች ንቁ እንዳልሆነም ታወሳለች። ዕድገቱና የሰውነቱ መጠንም በዕድሜው ልክ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነም ትጠቅሳለች። በሥልጠናው እንዲህ ዓይነቱ የጤና ችግር ሕፃናት ከጽንስ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመታቸው በቂና በንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦች ባለማግኘታቸው የሚመጣ መቀንጨር የተሰኘው በሽታ እንደሆነ መገንዘብ ችላለች። ግንዛቤውን ማግኘቷ ልጇን በሚገባ ለመንከባከብ እንድትተጋ አድርጓታል።
የድጋፍ መርሐ ግብሩ በፋናና ንስር ሸማች ማሕበራት የተደረገ ሲሆን በተገኘሁበት ፋና ሸማቾች ማሕበር በክፍለ ከተማው ስድስት ወረዳዎች የሚገኙ አጥቢ ፤ ነፍሰ ጡርና ዕድሜያቸው እስከ ሶስት ዓመት የደረሰ ሕፃናት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
ብዙዎቻችን ምግብ አመጋገብን ረሃብን ከማስታገስና ከመጥገብ ጋር እናያይዘዋለን። ሆኖም ዓላማው ይህ ብቻ ሳይሆን ገና ከጠዋቱ አእምሯዊና አካላዊን ጨምሮ ሁለንተናዊ የሰውነታችንን ግንባታ ማዕከል በማድረግ የተመጣጠነ መሆንም ይኖርበታል ሲሉ ስለድጋፉ ማብራሪያቸውን የጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሀና የሺንጉስ ናቸው።
ያልተመጣጠነ ምግብ ዕድገትን ያቀነጭራል። መቀንጨር የሚከሰተውም የሕፃናት ዕድሜና ቁመት ሳይመጣጠን ሲቀር ነው። በሽታው ከጽንስ ጀምሮ ሕፃናት ሁለት ዓመት እስኪሞላቸው የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ከሥርዓተ ምግብ መዛባትና አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የወደፊት አገር ተረካቢ የሆኑትን ሕፃናትን ከዚህ የጤና ችግር መታደግ የሚያስችል የአልሚ ምግቦች ድጋፍ ውሱን ሆኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል። የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ከእናት ጽንስ ጀምሮ እስከ ሁለትና ሦስት ዓመት ይዘልቃል። ሆኖም በዚህ ወቅት ነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች እንዲሁም ሕፃናት የዓልሚ ምግቦች ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጡ እንዳሉም አክለዋል። አካል መቀጨጩንና ቁመት ማሳጠሩን አስታውሰው በአእምሮ ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን የሚያደርስ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል። ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ የጤና ችግሩን ለማቃለል የከተማው አስተዳደር ከሌሎች ዘርፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መገኘቱንም አንስተዋል። በመርሐ ግብሩ ገቢያቸው ዝቅተኛ ለሆነና ገቢ ለሌላቸው በ11ዱ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ለሆኑ ለዘጠኝ ሺህ እናቶች የተደረገው የአልሚ ምግቦች ድጋፍ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ድጋፉ የተያዙትን ቀጣይ ሁለት የክረምት ወራቶች ጨምሮ በ2015 ዓ.ም ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ ተመቻችቷልም ብለዋል።
ከጽንስ ጀምሮ በሚከሰት በሽታ በኢትዮጵያ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ለጉዳት መዳረጋቸውን ቆየት ያሉ ጥናቶች ያመለክታሉ። በፈረንጆቹ 2016 የተደረገን ጥናት ዋቢ አድርጎ ከጤና ሚኒስቴር የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ 38 በመቶ ያህል የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመቀንጨር በሽታ ተዳርገዋል። ነገር ግን በመከላከሉ ረገድ ኢትዮጵያ በሰራችው ባለ ዘርፈ ብዙ የተቀናጀ ሥራ በፈረንጆቹ 2017 ዓ.ም 20 በመቶ ያህሉን ችግር መቀነስ ችላለች። ችግሩን መቀነስ ካስቻላት ዋናውም ነፍሰ ጡር እናቶችና ዕድሜያቸው እስከ ሁለት ዓመት ላሉ ሕፃናት አልሚ ምግቦችን በስፋት በማቅረብ ነው።
ሕብረተሰቡ በተለይም ነፍሰ ጡር እናቶች ተመጣጣኝ ምግብ እንዲመገቡ የሚያስችል ግንዛቤ ፈጠራ ላይም በብርቱ ስትሰራ መቆየቷም መሆኑ ለውጤቱ መመዝገብ ላቅ ያለ ሚናን ተወጥቷል ። እንደ ጥናቱ በሽታው እናቶችንና ሕፃናትን ከመጉዳቱ ባሻገር በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ላይም በየዓመቱ 16 ነጥብ 5 በመቶ የራሱ ተፅዕኖ ያሳድራል። በየዓመቱ 58 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚያሳጣት በመሆኑ ለነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች እንዲሁም ለሕፃናት እየተደረገ ያለው የዓልሚ ምግብ አቅርቦት ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥል ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2014