ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ሲፈለጉ ኅብረተሰቡ በቀላሉ መጠቆም እንዲችል ተጠርጣሪዎች በቅርብ ጊዜ የተነሱት ፎቶ በተለያዩ መንገዶች እንዲሰራጭ ይደረጋል፡፡ ይህም ተጥርጣሪዎች ወዲያው የመያዝ ዕድላቸውን ከማስፋቱም በላይ የፖሊሶችንም የፍለጋ ድካም የሚያቃልል ነው፡፡
ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው ድረ ገጽ ከወደቻይና ይዞት ብቅ ያለው መረጃ ግን ‹‹ፖሊስ ይፈለጋል!›› በሚል በድረ ገጹ ለሕዝብ ባሰራጨው የተጠርጣሪ ፎቶ ምክንያት ‹‹መሳቂያ መሳለቂያ›› ሆኗል ይለናል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በቻይና ዤንዢዮንግ ግዛት ፖሊስ ጂ ኪንጋሂ የተሰኘውን የአስራ ሰባት ዓመት ታዳጊ ተጠርጣሪ ፎቶ ‹‹ይፈለጋል!›› በሚል በድረ ገጹ ያሰራጫል፡፡ ‹‹ይፈለጋል!›› በሚል የተሰራጨው የታዳጊው ፎቶ ገና ትምህርት ያልጀመረ ሕፃን የሚመስል መሆኑ ደግሞ ነገሮችን የበለጠ እንዲወሳሰቡ ያደርጋል፡፡
ተጠርጣሪው ዕድሜው አስራ ሰባት የሞላው ቢሆንም፤ በዚህ ዕድሜ እርሱን የሚገልፅ አንድም ፎቶ ባለማግኘቱ ‹‹በሕፃንነቱ የተነሳውን ፎቶ ለመጠቀም ተገድጃለሁ›› ሲልም ፖሊስ ይገልፃል፡፡ በጥብቅ ከሚፈለጉ ሌሎች ተጠርጣሪ ግለሰቦች ጋር በድረ ገጽ የተለቀቀው የእምቦቀቅላው ፎቶም ብዙዎችን ማነጋገር ይጀምራል፡፡
በርካቶች ፎቶውን በማህበራዊ ድረ ገፆች አማካኝንት መቀባበላቸውን ተከትሎም ፖሊስ መሳቂያና መሳለቂያ ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ ስህተት መስራቱ የገባው ፖሊስ ታዲያ በማግስቱ ፎቶው በስህተት መለቀቁን በማመን ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ተጠርጣሪው ግለሰብ በቅርቡ የተነሳው ፎቶ የሌለ በመሆኑ የሕፃንነት ፎቶውን እንደተጠቀመም ያስረዳል፡፡ ፖሊስ ያቀረበው ምክንያት ነገሮችን የበለጠ በማወሳሰቡና ከበርካታ ሰዎች ተቃውሞ በመምጣቱም ፖሊስ በድረ ገጹ የለቀቀውን ፎቶ ያወርደዋል፡፡
በቻይና ተወዳጅ በሆኑት ዊቻትና ዌቦ በተሰኙ የማህበራዊ ትስስር ገፆች የተጠርጣሪው ጂ ኪንጋሂ ፎቶ መሰራጨቱን ተከትሎ ሰዎች በዤንዢዮንግ ፖሊስ የተለቀቁ ተፈላጊውን ተጠርጣሪ ምስል ማጥፋት ሲጀምሩ ፖሊስ ለ‹‹ይፈለጋል›› ዳግም የለቀቃቸውን የተጠርጣሪውን ሌሎች ሁለት የሕፃንነት ፎቶዎች ያገኛሉ፡፡
በዚህም ፖሊስ በድጋሚ ስህተት መስራቱ ይገባዋል፡፡ ሁለቱንም የተጠርጣሪውን ፎቶ ከድረ ገጹ ያወርዳል፡፡ ለተፈጠረውም ስህተት ምንም ዓይነት ማስተባበያ ሳያቀርብ ጥፋተኛ መሆኑን አምኖ ይቅርታ መጠየቁንና ከዚህ ስህተት በመማርም ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ስህተት እንደማይደግም መናገሩን ዘገባው አመልክቷል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2011
በአስናቀ ፀጋዬ