‹‹ዛፍ ለሰዎች አልያም ለእንስሳት ጥላነት ከማገልገል ውጪ እንዴት የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊ ሊሆን ችላል?›› ይሉ ይሆናል። በርግጥ ዛፍ ሕይወት ያለው ነገር ቢሆንም እንደሰው ትኬት ቆርጦና ስታዲየም ገብቶ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ሊመለከት ይችላል ወይ? ሲሉም አክለው ይጠይቁ ይሆናል።። በርግጥ እውነትዎን ነው። ይሁንና ይህ ዛፍ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊ ሊሆን የቻለው ልክ እንደሰው ትኬት ቆርጦ ስታዲየም በመግባት ሳይሆን በሌላ ምክንያት ነው።
ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው ድረ ገጽ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ መሠረት በኡራጋይ ሁለተኛ ዲቪዥን የሚጫወተው ሬሲስቴኒካ የተሰኘው አነስተኛ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎቹ በተቀመጡበት ቦታ ወይም በእኛ ሀገር ስታዲየም አጠራር ካታንጋ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ዛፍ በማብቀል በዓለም የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል።። ልክ እንደሌሎቹ የክለቡ ደጋፊዎች ሁሉ ዛፉ በአባልነት እንዲመዘገብና ክለቡ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ሁሉ በነፃ እንዲታደም ተደርጓል ሲልም ዘገባው አመልክቷል።
ላ ቻቻሪታ የተሰኘው ይኸው እግር ኳስ ደጋፊ ዛፍ ከክለቡ ምስረታ በፊት የነበረ አንጋፋ ዛፍ በመሆኑ ክለቡና ደጋፊዎች ዛፉ የታሪካቸው አንዱ አካል አድርገው ይቆጥሩታል ያለው ዘገባው፤ ክለቡ ከሃያ ዓመት በፊት ለደጋፊዎቹ ተጨማሪ የኮንክሪት መቀመጫዎችን ለመገንባት ሲያስብ አንጋፋ የሆነውን የክለቡ ደጋፊ ዛፍ ለመቁረጥ እንኳን ሃሳብ አልነበረውም።
ይልቁንም በወቅቱ ስታዲየሙን ሲገነቡ የነበሩ መሐንዲሶች ዛፉ ሳይቆረጥ የደጋፊዎቹ መቀመጫ ግንባታ እንዲካሄድ ይጠይቃሉ። መሐንዲሶቹም ክለቡ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ደጋፊቹ በዛፉ ጥላ ስር በመሆን መከታተል እንዲችሉ የስታዲየም መቀመጫውን በዛፉ ዙሪያ ይገነባሉ።
ከዓመታት በፊት አንጋፋው የክለቡ ደጋፊ ዛፍ መቶኛ ዓመቱን ሲያከብር የክለቡ አስተዳደር ዛፉን በማክበር የክለቡ ቋሚ አባል እንዲሆን መወሰኑንና የአባልነት መታወቂያ ካርድም እንዲሰጠው መደረጉንም ዘገባው ገልጿል። ሮቤርቶ ጋርሴቴ የተሰኙት የክለቡ ፕሬዚዳንትም ‹‹ዛፉ እንደ አንድ የክለባችን ደጋፊ ይቆጠራል፤ ሃያ አራት ሰዓታት ሙሉ በስታዲየሙ ስለሚገኝም ታማኙ ደጋፊያችን ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።
ላ ቻቻሪታ የተሰኘው ዝነኛ ዛፍ የ100 ዓመት ዕድሜ ያለው መሆኑ ተነግሯል። በአሁኑ ወቅት 20 ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ በስታዲየሙ የኮንክሪት መቀመጫ መካከል በተዘጋጀለት ቀዳዳ አማካኝነት እድገቱንም ቀጥሏል፤ ‹‹ዛፉ ከክለቡ ደጋፊነትም ባሻገር ለሌሎቹ የክለቡ ደጋፊዎች ከፀሐይ መጠለያ በመሆንም ባለውለታነቱን አስመስክሯል›› ሲል ዘገባው አያይዞ ጠቅሷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 17/2011
አስናቀ ፀጋዬ