ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ አንድ ዓመት ሊሞላቸው የቀናት ዕድሜ ብቻ ይቀራሉ፡፡ በዚህ ወቅትም በርካታ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡ ፡ በሌላ በኩል ለውጡን የሚገዳደሩ እንቅፋቶችም ከለውጡ ጎን እንደተሰለፉ እስካሁን ዘልቀዋል፡፡
በአንድ ዓመቱ የለውጥ ጉዞ ውስጥ ከተገኙ ስኬቶች ውስጥ በዲፕሎማሲ ዘርፉ የተገኙት ዓለም አቀፍ እውቅናና አድናቆት ጭምር የተቸራቸው ናቸው፡፡ በተለይ ከኤርትራ ጋር ላለፉት 20 ዓመታት የነበረው ሞት አልባ ጦርነት አብቅቶ ሁለቱ ሕዝቦች የቀደመውን አብሮነት እንዲያጠናክሩና በሁለቱ አገራት መካከል የቆየው የስጋትና የጥርጣሬ መንፈስ በትብብር ላይ በተመሰረተ ግንኙነት እንዲተካ የተሰራው ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን በተለይ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና ለሕዝቦቻቸው እድገት በጋራ ለመስራት የተካሄዱ ውይይቶችና የተደረሰባቸው ስምምነቶች በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ ውጤቶች ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ከሚችሉት የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የአረብ አገራትም ጋር የተካሄዱ ውይይቶችና መግባባት የተፈጠረባቸው ጉዳዮችም ኢትዮጵያ ከሁሉም አገራት ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ፍላጎት በተግባር ያሳየችበት ነው፡፡
ሌላው የለውጡ ትሩፋት በአገር ውስጥ የተገኘው የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት እንቅስቃሴ ነው፡፡ አገራችን ከለውጡ በፊት በዓለምአቀፍ መድረክ ጭምር ከምትወቀስባቸው ጉዳዮች አንዱ የሰብዓዊ መብት አያያዝና የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም መንግሥት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ አድርጓል፡፡ ከተወሰዱ እርምጃዎችም ውስጥ ታራሚዎችን በይቅርታና በምህረት የመልቀቅ፣ በሽብርተኝነት የተከሰሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ክሳቸው እንዲነሳላቸውና ወደ አገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ዕድል መስጠት፣ የሚዲያውን ነፃነት ማስፋት፣ የምርጫ ቦርድና የፍትህ ተቋማትን በአዲስ መልኩ የማደራጀት እና መሰል እርምጃዎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን በአገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ ችግሮችንም ለመፍታት ትላልቅ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በእነዚህ እርምጃዎችም የኃይል አማራጭን በመከተል ትጥቅ ያነገቡና በረሃ የገቡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር በይፋ ተኩስ አቁመው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገራቸው ተመልሰው ሰላማዊ ትግል እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡
በኢኮኖሚ መስክም የተወሰዱት እርምጃዎች ሰፊና መሠረታዊ የፖሊሲ እርምጃዎችን ያካተቱ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ በተለይ ትላልቅ የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር የተወሰዱ እርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን በጥቁር ገበያውና በሕገወጦች አማካይነት ተከስቶ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ በሕገወጦች ላይ የተወሰደው እርምጃና የተገኘው
ስኬትም ኢኮኖሚው እንዳይወድቅ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ከአንድ ዓመት በፊት አጋጥሞ የነበረው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመጠኑም ቢሆን መሻሻል አሳይቷል፡፡
በአገራችን ትልቅ የኅብረተሰብ ቅሬታ ምንጭ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታትም የመንግሥት ተቋማትን አሠራር እና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚያስችሉ ሪፎርሞች ተካሂደዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመንግሥት አስፈፃሚ ተቋማትን በአዲስ መልኩ በማደራጀት ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ ተቀይሷል፡፡እነዚህ መልካም ተግባራት ለውጡን ወደፊት የሚያስቀጥሉ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ናቸው፡፡
ያም ሆኖ ግን በለውጥ ሂደቱ ውስጥ ፈተናዎች ማጋጠማቸው አልቀረም፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ በየቦታው እየተከሰተ ያለው ግጭትና የሰላም መደፍረስ ነው፡፡ በተለይ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች እያጋጠመ ያለው ሕገወጥነት ቀስ በቀስ ፈሩን እየሳተና እየሰፋ ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ የሃይማኖት ተቋማት መውደምና የዜጎች መፈናቀል መንስኤ ሆኗል፡፡ እነዚህ ተግባራት ደግሞ ለውጡን ከማሰናከልም ባለፈ ሀገርን የሚያፈርሱ አደገኛ አዝማሚያዎች ናቸው፡፡ስለሆነም መታረም አለባቸው፡፡
ለምሳሌ በደቡብ ክልል በጌዲኦና በጉጂ ዞን አዋሳኞች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ እንዲሁም በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ በርካታ ንብረት ወድሟል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ከሚኖሩበት ቀያቸው እየተፈናቀሉ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፡፡ በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኞች አካባቢዎችም የሚነሱ ውዝግቦች አካባቢውን ለውጥረት ዳርገዋል፡፡ በአዲስ አበባም ከባለቤትነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚራገቡ አሉባልታዎችና የተዛቡ መረጃዎች የሰላም ስጋት ሆነው ቀጥለዋል፡፡
ነገር ግን ከፍተኛ የሕዝብ ተነሳሽነትና አገራዊ መግባባት እየተፈጠረ ባለበትና አገራዊ አንድነትና እድገት ብሎም የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትግል እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ግጭቶችና ዜጎችን የማፈናቀል ተግባራት አገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥሉና አገርን የሚበታትኑ ተግባራት በመሆናቸው ለመፍትሄያቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብም የእርምት እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡
አሁን የተጀመረው ለውጥ ከዳር ሊደርስ የሚችለውና ዜጎችም ከዚህ ለውጥ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ሰላም ሲኖር ብቻ መሆኑን መገንዘብና ለዚህም እያንዳንዱ ዜጋ መረባረብ ይጠበቅበታል፡፡ ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ አረሞችም ሳይጎመሩ በወቅቱ ሊነቀሉ ይገባል፡፡ በመሆኑም የተጀመረውን ለውጥ ወደ ፊት ለማስቀጠል መንግሥትም ሆነ ኅብረተሰቡ የችግሮቹን መንስኤ ቆም ብሎ ማጤንና ሆን ብለው ግጭት የሚፈጥሩ አካላትን በመለየት ድርጊታቸውን ማስቆም ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት17/2011 e