ወደኋላ ጥቂት ሄደው የሚያስታውሱ ሰዎች ያወቁታል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚያቀርባቸው የኦሮምኛ ድራማዎች ላይ ከሚታወቁ ዋነኛ ተዋንያን መሀከል አንዱ እሱ ነው፡፡ትወናው ኦሮምኛ ቋንቋን በማያውቁ ሰዎች ዘንድ ሁሉ ፈገግ የሚያሰኝ ጥበበኛ ነው፡፡አድማሱ ብርሃኑ! ጋዜጠኛ ጀሚል ይርጋ ስለእሱ ያሰፈረውን ጽሁፍ እነሆ አጋራናችሁ!
ብዙዎች በትወናው ያስታውሱታል፤ አድማሱ ብርሃኑ – ተዋናይ፣ ሙዚቀኛ፣ ተወዛዋዥ እና የሙዚቃ መሳሪያ (ትራምፔት) ተጫዋች የነበረ ታላቅ የጥበብ ሰው !ብዙዎች የሚጠሩት “አባ ለታ” በተሰኘው የመድረክ ስሙ ነው። አርቲስት አድማሱ ከአባቱ ከአቶ ብርሃኑ መገርሳና ከእናቱ ከወ/ሮ ዘነበች ጉሹ ሐምሌ 26 ቀን 1948 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ቢርመጅ ወረዳ፣ በቢላ ከተማ ነው የተወለደው።
የትውልድ ቀዬውን ገና በትንሽነቱ ለቆ ኑሮውን ከአክስቱ ጋር ጦላይ በማድረጉ ፣ ትምህርቱንም እዚያው ጦላይ እስከ አራተኛ ክፍል፣ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ደግሞ በማታ ትምህርት እስከ ሰባተኛ ክፍል ተምሯል፡፡ ለጥበብ የነበረው ፍላጎት በማየሉ በ1968 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ቴአትርና ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ) በባህል ድምፃዊነት በመቀጠር አገልግሎት የጀመረ ሲሆን፣ በድምጻዊነቱም “ያ ቱሩንጎ” እና “ቢቂልቱ ገነማ” የተሰኙት ዘፈኖቹ ተወዳጅነት አትርፈውለታል። ለሂርዻ ጋንፉሬ፣ ዳግም መኮንን፣ አስቴር አብዲ፣ ሀብታሙ ለሙ እና ለሌሎችም የዘፈን ግጥሞችን አበርክቷል–ከዘፋኝነቱ በተጨማሪ።
በሀገር ፍቅር፣ በራስ ቴአትርና በብሔራዊ ቴአትር በታዩ ዕውቅ እና ተወዳጅ የመድረክ ተውኔቶችም ላይ ተውኗል። ከተጫወታቸው ቴአትሮች መካከልም “ቴዎድሮስ”፣ “ስመኝ ስንታየሁ”፣ “ባልቻ አባ ነብሶ”፣ “የቬኑሱ ነጋዴ”፣ “እሳት ሲነድ”፣ “መልዕክተ- ወዛደር”፣ መቅድም እና “የቆሰሉ ምሽጎች” ይጠቀሳሉ።
በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ዕውቅናን ያገኘው እና ተወዳጅነትን ያተረፈው ግን የኢትዮዽያ ቴሌቪዥን በኦሮምኛ ቋንቋ ሥርጭት ከጀመረ በኋላ ያስተላልፍ በነበረው “Dhangaa” የመዝናኛ ፕሮግራም ነው። በዚህ ዝግጅት ላይ ይታዩ በነበሩ ጭውውቶችና ድራማዎች ላይ ከነ አርቲስት ታደሰ ጩቄ፣ ሙሉጌታ ባልቻ፣ ሁምኔቻ አሰፋና ከሌሎችም ጋር በመሆን በደራሲነት፣ በአዘጋጅነትና በተዋናይነት ተሳትፏል። ከሁሉም በላይ ለ “Dhangaa” ዝግጅት መወደድ የነበረው አስተዋፅኦ ከማንም የበለጠ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። የኦሮምኛ ቋንቋን የማይሰሙ ሰዎች ሁሉ ፕሮግራሙን እንዲከታተሉ ያስቻለና አቅም የፈጠረ ሰው ነበር።
አሁን የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) ቀድሞ የ”ኦሮሚያ ቴሌቪዥን” ላይም በ “Dheebuu” እና በመሰል ድራማዎች ላይም ተውኗል። “ለኪነ ጥበብ የታመነ” እንደሆነና “ለቁሳዊ ጥቅሞች የማይንሰፈሰፍ” ሰው እንደነበር በቤተሰቦቹና በሥራ ባልደረቦቹ ጭምር የሚመሰከርለት ይህ ታላቅ የጥበብ ሰው፣ በድንገተኛ ሕመም የካቲት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር ያረፈው። አርቲስት አድማሱ ባለትዳርና የሁለት ወንዶችና የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ነበር፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም