ሳምንቱ ለሙዚቃ አፍቃሪው ህብረተሰብ አሳዛኝ ነበር፡፡ በትግርኛ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው እና ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈው ድምጻዊ ዳዊት ነጋ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለህክምና በሄደበት ክሊኒክ በድንገት ማረፉ መሰማቱ መላው ኢትዮጵያውያንን አስደንግጧል። እሁድ አመሻሽ ላይ የተሰማው ዜና እንኳን ለሌላው ሕዝብ ይቅርና ዳዊትን በቅርብ ለሚያውቁት እንኳን ያልተጠበቀ ዱብእዳ የሆነ ነበር፡፡ ከእረፍቱ ዜና መሰማት በኋላ የወጡ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት ድምጻዊው ክሊኒክ ውስጥ ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር ሲነጋገር የሚያሳይ ፎቶ በወቅቱ ደህና እንደነበር የሚያሳይ ሲሆን የሞቱ ዜና አስደንጋጭ የሆነውም በዚህ የተነሳ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ለሞት ያበቃው ህመም ምን እንደነበር ወደፊት ሊታወቅ የሚችል ጉዳይ ሆኖ ዜና እረፍቱ ግን አሳዛኝ እና ልብ ሰባሪ ነበር፡፡
ዳዊት የመቐለ ተወላጅ ነው፡፡ የልደቱ ቀንም ሚያዝያ 2 /1980 ዓ.ም ነው፡፡ በሙዚቃ ቪዲዮዎቹ ላይ ድንቡሽቡሽ ብሎ ሲታይ ከደህና ቤተሰብ የተወለደ የሚመስለው ዳዊት ሀቁ ግን ወላጆቹን ገና በ10 ዓመቱ አጥቶ በብዙ መከራ ተፈትኖ ያደገ ልጅ ነበር፡፡ ከወላጆቹ እረፍት በኋላ ዳዊት የኖረው እማማ ታደሰች የሚባሉ የእናቱ የልብ ወዳጅ የነበሩ ጎረቤት ጋር ነበር፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ ቤት ተከራይቶ መኖር ጀምሮ ነበር፡፡ በወቅቱ ለቤት ኪራይ 200 ብር ይከፍል የነበረ ሲሆን እሱን መክፈል ቀላል አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ ኪራይ ገንዘብ አልሞላ ሲለው አንዳንዴ በእኩለ ሌሊት በአጥር ዘልሎ እየገባ ሌላ ጊዜ ጓደኞቹ ጋር እያደረ ሲሳካለትም ኪራዩን እየከፈለ ኑሮውን ገፋ፡፡ በወቅቱ ስለነበረው አኗኗር ሲናገር “ሲጋራ እሸጥ ነበር፡፡ መቀሌ ውስጥ የሚሸጠውን ነገር ሁሉ ሸጫለሁ” ይላል፡፡
ዳዊትና ሙዚቃ የተዋወቁት ገና በልጅነት ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ ለሙዚቃ ጥልቅ ፍቅር እንዳደረበት የሚናገረው ዳዊት በ15 ዓመቱ አካባቢ የሙዚቃ ፍላጎቱን እና ህልሙን እውን ማድረግ በማሰብ “ሰርከስ ትግራይ” በሚባለው የሰርከስና ሙዚቃ ቡድንን በዘፋኝነት ለመቀላቀል ጥያቄ አቀረበ። ጥያቄው በጊዜ መልካም ምላሽ ባያገኝም ወደ ማርሽ ባንድ እንዲቀላቀል እና ከበሮ (ድራም) እንዲጫወት እድል ተሰጠው። ለሰባት ዓመታት ገደማ የማርሽ ባንዱ ድራመር በነበረበት ጊዜ ሁሉ ግን በውስጡ ዘፋኝ የመሆን ፍላጎት እና ህልም ስለ ነበረው ለመዝፈን ከመሞከር አላቆመም። ይህ ህልሙም በመጨረሻ ተሳካና ከሕዝብ ጋር ያገናኘውን ባባኢለን የተሰኘ ሙዚቃ ተጫወተ፡፡ ሙዚቃው ከዳዊት አስገምጋሚ ድምጽ ጋር ፍጹም የተዋሀደ ፤ የትግርኛ ባህላዊ ሙዚቃ ለዛ ያልጠፋበት ፤ ዘመናዊነትን በልኩ የደረበ በመሆኑ እንኳን ትግርኛ በሚሰማው ሕዝብ ይቅርና ትግርኛ በማይሰማው ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት አገኘ፡፡ ከዚያን በኋላ የዳዊትን የስኬት ጉዞ የሚያስቆመው አልተገኘም፡፡ “ዳኣመና”፣ “ባባ ኢለን”፣ “ሕድያት መቀለ”፣ “ወዛመይ”፣ “ዘዊደሮ”፣ “ብነጸላይ”፣ “ቅዱስ ጸባያ” እና “ቸኮላታ” ዳዊት የታወቀባቸው ሙዚቃዎች ሆኑ። በተለይ ባባኢለን ፤ ወዛመይ ፤ ዘዊደሮ እና ብነጸላይ በጣም ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፈውለታል፡፡ እስካሁን በዩቲብ ባላቸው እይታ ብንመዝናቸው እንኳ ወዛመይ ከ19 ሚሊዮን በላይ ፤ ዘዊደሮ 8 ሚሊዮን ገደማ ፤ ባባኢለን ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ፤ ብነጸላ እንዲሁ ከ8 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አግኝተዋል፡፡
ከዓመታት በፊት “ኦሮሚያ” በሚል ርዕስ በትግርኛ፣ ኦሮሚኛና በአማርኛ የሰራው ሙዚቃ ለአድናቂዎቹ ማድረሱም ይታወሳል። የዘፈኑ ይዘት አንድ ወጣት በአንዲት የኦሮሞ ኮረዳ ፍቅር መሸነፉን እንዲሁም ስለውበቷና ስለማንነቷ ይተርካል። ድምጻዊ ዳዊት፣ በ2011 አክሱማይት የተሰኘ የሙዚቃ ሰንዱቅ (አልበም) ወደ ሕዝብ አድርሷል። የመጨረሻው ነጠላ ዜማው “አጆኪ ትግራይ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት ስለተለያዩና መገናኘት ስላልቻሉ የትግራይ ቤተሰቦች ናፍቆት ገልጿል።
ዳዊት የሙዚቃ ከፍታው ላይ ይድረስ እንጂ ሕይወቱ ከባድ ነበር፡፡ ነገር ግን መንፈሰ ጠንካራ እንደሆነ ይናገራል። “እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ሰው ይፈተናል። ዋናው ነገር ይሄን ፈተና እንዴት አድርገህ ታልፈዋለህ የሚለው ጉዳይ ነው” ይላል ስላለፈው ሕይወቱ ሲናገር። አክሎም “ስኬት ቅርብ ነው ጠንካራ ከሆንክ” በማለትም ለወጣቶች ከሕይወት ልምዱ ያካፍላል፡፡ በእርግጥም ጠንካራ መሆኑ ብዙ አግዞት ከማርሽ ባንድ የተነሳው ወጣት ድምጻዊ በኮክ ስቱዲዮ አልበም ካወጡ ዝነኛ የደቡብ አፍሪካ እና አንጎላ አርቲስቶች ጋር ሙዙቃ እስከማቅረብ ደርሷል፡፡ ካሌብ ሾው በተሰኘ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ሰውን በሕይወት እያለ ስለማድነቅም ሲጠየቅ “ሰውን በሕይወት እያለ ነው ማመስገን ያለብን፡፡ እንኳን ለሀገር የሰራ ይቅርና የራስህ ሕይወት ያሸነፈ ሰው አድናቆት ይገባዋል፡፡ ማድነቅ መሰልጠን ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡ ድምፃዊ ዳዊት ነጋ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነበር።
ከዜና እረፍቱ በኋላ የሙያ አጋሮቹ ማዘናቸውን በማሕበራዊ ሚዲያ የገለጹ ሲሆን ከነዚህም መሀከል የሙዚቃ ሀያሲው እና የአዲስ አበባ ባህል ፤ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሰርጸ ፍሬስብሀት “የወጣት፣ ያውም የትልቅ ባለተስፋ ጠቢብን የሕልፈተ ሕይወት አስደንጋጭ ዜና መስማት በጣም ያሳዝናል። ነፍስ ኄር “ብሏል፡፡ ድምጻዊ ሳሚ ዳን “ነብስ ይማር ወንድሜ፤ እረጅም የስኬት መንገድን ብንመኝም ፈጣሪ የፈቀደው ግን ሆኗል” ሲል ሌሎችም እንዲሁ ኀዘናቸውን ገልጸዋል። በርካታ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ኀዘናቸውን በስፋት የገለጹ ሲሆን ሙዚቃው ትግርኛ ቋንቋን ሳይሰሙ እንኳ ይወዷቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የአርቲስቱ ሥርዓተ ቀብር ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም