ምግብ፣ መጠለያና ልብስ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ናቸው። ሰላም ደግሞ የነዚህ ሁሉ መሰረት ነው። ሰላም ከሌለ ህይወት ዋስትና ሊያገኝ አይችልም። ሃብትና ንብረትም አይታሰብም። ቤተሰብ መመስረትም ሆነ ልጅ ወልዶ ማሳደግ አይቻልም። ቀጣይ ትውልድ ለማፍራትም አይታሰብም። ሰላም የብዙ ቁምነገሮች ድምር ውጤት ነው። የሰላም እጦት የሀገር ህመም ነው።
የሰው ልጅ ሲታመም መላ አካሉ እንደሚታወከው ሁሉ ሰላም ሲጠፋም አገር ይታመማል፤ አገር ይታወካል። የሰላም እጦት የሚያስከትለውን አደጋ ለመረዳት የግድ ግጭት ውስጥ መግባት አይጠበቅብንም። ያሳለፍናቸው መንገዶች በራሳቸው በቂ ተሞክሮ አላቸው። ከዚህ ቀደም በጥቂቱም ቢሆን በሰላም እጦት ዋጋ የከፈልንባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ለምሳሌ በደርግ ዘመነ መንግስት ከአጠገቡ ሰው ሲሞት ያላየ ኢትዮጵያዊ የለም እስከሚባል ድረስ የህይወት መስዋዕትነት ተከፍሏል። በኢህአዴግ ዘመንም ቢሆን አልፎ አልፎ እዚህም እዚያም በሚከሰቱ ግርግሮች የጠፋውን ክቡር የሰው ህይወትና በኢኮኖሚያችን ላይ የተከሰቱትን ቀውሶች መርሳት አይቻለንም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው ሰብአዊ እርዳታ መጠበቅ ግድ የሆነባቸው ዜጎችን መመልከቱ ሌላው የወቅቱ ማሳያ ነው። ሰሞኑን እንኳን በጌዲኦና በጉጂ አካባቢ እንዲሁም በአማራ ክልል መስራት እየቻሉ በሰላም እጦት ለእርዳታ የተዳረጉ ዜጎችን ማየት ምን ያህል ስሜት እንደሚጎዳ ማየት በቂ ነው። አሁን አሁን በአገራችን እየታየ ያለው የግጭት እና ሁከትን የመፍጠር አዝማሚያ ግን ቶሎ መፍትሄ ካልተበጀለት ከዚህም በላይ ዋጋ ለመክፈል እንገደዳለን።
በተለይ በየጊዜው በሚፈጠሩ አጀንዳዎች ቡድን መስርቶና ጎራ ለይቶ በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረገው የቃላት ጦርነት ግጭትን ከመፍጠር አልፎ ወደ ከፋ የርስ በርስ ጦርነት ሊከተን የሚችል ስለሆነ በዚህ ጉዳይ መንግሥት ፈጣንና ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ ይገባል። በተለይ ባለቤት በሌለውና ሃሳቡን ማን እንዳመነጨው በውል በማይታወቀው የማህበራዊ ሚዲያ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ለዘመናት አብሮ የኖረን ማህበረሰብ እርስ በርስ ለማጋጨት የሚጥሩ ኃይሎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። አሁን አሁን ብሄርና ማንነትን መሰረት ያደረጉ ትርክቶች ከምሁራን ወጥተው የፌስቡክ አርበኞች አጀንዳ እየሆኑ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ ሲነሳ ታሪክ ለማስተማር ድፍረት የተሞላው ትንታኔ የሚሰጡ የፌስቡክ ምሁራን፣ ስለአማራና ትግራይ ጉዳይ ሲነሳ ወልቃይትን ለፈለገው አካል እየሰጡ የሚደሰኩሩ አርበኞች፣ የሲዳማ የክልል ጥያቄም ሲነሳ ተነሳ ታጠቅ ብሎ ከመፍትሄ ይልቅ ጦር ለማንሳት የሚፎክር ታጋይ፣ ግለሰቦች በራሳቸው ጉዳይ ሲጋጩ የብሄር ግጭት አስመስሎ የሚያቀርብ ሴረኛ ወዘተ የማኅበራዊ ሚዲያ ቋሚ ተሰላፊ በዝቷል።
ይህ ግን ከበስተጀርባው ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ሰላምን ለማደፍረስ በሚፈልጉ ኃይሎች የውሸት አካውንት የሚሰራ ደባ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። መንግሥት ባለፈው አንድ ዓመት ያከናወናቸውና በዚህ አገር ሊደረጉ አይችሉም ተብለው የሚታሰቡ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መኖራቸውን መገንዘብ ግን ለሁሉም ጠቃሚ ነው። በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በተወሰዱ እርምጃዎች የተገኘውን ውጤት መረዳትና መንከባከብ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ህብረተሰቡ ይጠበቃል።
ለዚህ ደግሞ ህግና ሥርዓትን ጠብቆ መስራትና መኖር አስፈላጊ ነው። በመሆኑም አሁን በየቦታው የሚታየውን የለውጥ ጉዞ በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠልና አገራችንን ከድህነት በማውጣት መጪውን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ዋነኛ መንገዱ ሰላማችንን ማስጠበቅ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል። ለነገው ትውልድ የተሻለችና ምቹ የሆነች ሀገር ለማውረስ ዋነኛው ዋስትናችንም የዛሬ ሰላማችን ነው። ሰላሟ የደፈረሰ አገር ለነገው ትውልድ ትቶ መሄድ ኃላፊነትን መዘንጋት ብቻ ሳይሆን ቀጣዩን ትውልድ ለመከራና ስቃይ መዳረግ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
አባቶቻችን የበለፀገች ሀገር ማቆየት ባይሆንላቸውም ሰላምና ፍቅር እንዲሁም አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር አስረክበውናል። ይህ ደግሞ ትልቅ ሀብት ነው። በተለይ ሰላምን ማረጋገጥ የወቅቱ የአገራችን ትልቁ የቤት ስራ በመሆኑ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሰላም ላይ ትልቅ የቤት ስራ እንደሚጠብቀን አውቀን መስራት ይገባናል።
መሽቶ በነጋ ቁጥርም ሰላምን የሚያደፈርስ አጀንዳ እየፈጠሩ ህዝብን ከህዝብን ለማጋጨትና ሀገር ለማፍረስ ጥረት የሚያደርጉ አካላትንም ሀገርን ማልማት ቢያቅታችሁ የእንኳን ጥፋት አካል አትሁኑ ልንላቸው ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ስለሰላም በህግ አምላክ ሊባሉ ግድ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011