አዲስ ዘመን፡- ዓረና ለትግራይ ህዝብ ምን አይነት የፖለቲካና የኢኮኖሚ አማራጮችን ነው ይዞ የሚቀርበው?
አቶ ኣብርሃ፡- ዓረና ለ27 ዓመታት ለውጥ ያላመጣውን ግብርና መር ፖሊሲ ለብዙ ጊዜ ውጤት እንደማይኖረው ተገንዝቦ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በትግራይ ሕዝብ ለውጥ መምጣት ያልቻለው በፖሊሲ ችግር መሆኑን በመረዳትም ነው ለመለወጥ የተነሳው። በዚህም ግብርናውና ኢንዱስትሪው ተመጋግበው የሚሄዱበት ሥርዓት መመቻቸት እንዳለበት ስለሚያምን ዓረና የተቀናጀ ግብርና መር ኢንዱስትሪ ፖሊሲን እንደ አማራጭ ይዞ ቀርቧል። የፓርቲው የመጀመሪያው ትኩረቱ ግብርናን ማሳደግ ነው። ኢንዱስትሪ የግብርና ውጤቶች ገበያ በመሆኑም ግብርናውን ለማሳደግ የግድ ኢንዱስትሪ እንደሚያስፈልግ ያምናል። በኢኮኖሚ ፖሊሲውም የነፃ ገበያን መፍጠር ላይ ያተኩራል። ይህም ዜጎች የኢኮኖሚ ባለቤት የሚሆኑበት ሁኔታን መፍጠር ነው። በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግሥት የኢኮኖሚ ባለቤት በመሆኑ ኢኮኖሚው በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ስር ውሏል። በተቃራኒው ዓረና ከገዢው ፓርቲ በማላቀቅ ወደ ዜጎችና ግል ዘርፉ በማዛወር ብዙ ለውጦች እንዲመጡ ለማድረግ ይሠራል።
የህወሓት ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ አስተሳሰብ የሆነውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማስቀረት ዓረና በፖለቲካ ለውጥ የሚያደርግበት ዘርፍ ይሆናል። አስተሳሰቡ የአፈና መንገድ በመሆኑ በሊበራል ዴሞክራሲ ይተካዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በህወሓት/ኢህአዴግ ጊዜ ፓርቲና መንግሥት ባለመለያየታቸው መንግሥት የለም። በዚህም ምክንያት ሕዝብን ማስተዳደር ካለመቻሉ ባሻገር የተጠቃሚነት፣ ነፃነትና እኩልነት ጥያቄዎችንም ማስተናገድም አልተቻለም። በመሆኑም ዓረና በያዘው አማራጭ መንግሥትና ፓርቲን በመለየት ሕዝብን ከፓርቲ ተፅዕኖ ውጪ የሚያገለግል መንግሥት መመስረት ላይ ያተኩራል። ሌሎቹንም ችግሮች ለማቃለል በአገር ደረጃ ሕገመንግሥቱን በሕጋዊ መንገድ ለማሻሻልም ያስባል። ዓረና ከተመረጠ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ሕግ አውጪ እንጂ ሕግ ተርጓሚ አይሆንም። ሕግ መተርጎም የፍርድ ቤት ሥራና ሥልጣን ይሆናል። በተለያዩ ሁኔታዎችም ሥራዎቹን ክትትል ለማድረግ የሚያስችለውና ከውጤት የሚያደርሱ የአሠራር ሥርዓቶችን ይዘረጋል።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንደ አማራጭ ያነሱት የሊበራል ዴሞክራሲ አስተሳሰብ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ብሎም የትግራይ ክልል ካለችበት የኢኮኖሚና ፖለቲካ ደረጃ አንፃር እንዴት ይተገበራል? ውጤታማስ ይሆናል ብላችሁ ታስባላችሁ?
አቶ ኣብርሃ፡- ሊበራል አስተሳሰብ አንድ ዓይነት ሳይሆን የተለያዩ ደረጃዎችን የያዘ ነው። በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ሰው በአቅሙ ነው የሚሠራው። ምዕራባውያኑ የራሳቸው አቅምና በተለያዩ መስኮች ያሉበትን ደረጃ የሚመጥን የሊበራል አስተሳሰብን ያራምዳሉ። እኛ ደግሞ ለራሳችን በሚመጥን መልኩ ነው አስተሳሰቡን የምናቀነቅነው። የሊበራል ዋና አስተሳሰቡ ዜጎች እንዴት የኢኮኖሚ ባለቤት ሆነው ነፃነታቸው ተረጋግጦ ሀብት መፍጠር ይችላሉ? እንዴትስ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ነው። በዚህም ዜጎች ተወዳዳሪና አቅም እንዲኖራቸው ለማድረግ የመጀመሪያው ቁልፍ ተግባር የውድድር ገበያን መፍጠር ነው። በሌላ በኩል መንግሥት በሁሉም የፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ አይገባም።
በሊበራል አስተሳሰብም መንግሥት ጣልቃ የሚገባ ቢሆንም ልዩነቱ ግን በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ዓላማው የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ ወይንም ደግሞ ዜጎችን ሀብታም እንዲሆኑ ለመርዳት ነው ጣልቃ የሚገባው። በተቃራኒው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መንግሥት ጣልቃ የሚገባው ኢኮኖሚውንና ሰዎችንም ለመቆጣጠር ነው። ስለዚህ እኛ ጣልቃ ስንገባ የግል ዘርፉን ለማገዝ ብሎም ለዜጎች ዕድል ለመፍጠር እንጂ ኢህአዴግ እንደሚያደርገው ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠርና መንግሥትም ነጋዴም በመሆን ለኢኮኖሚው እንቅፋት ለመሆን አይደለም። ኢህአዴግ ልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብን ሲያነሳም ይደመጣል። ልማታዊ መንግሥት በራሱ ችግር አይደለም። ነገር ግን አስተሳሰቡ የሊበራል እንጂ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አይደለም። ልማታዊ መንግሥት ዜጎችን ለማበረታታት በኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማጎልበት መንግሥት ሊያግዛቸውና ሊያበረታታቸው ጣልቃ ይገባል ነው የሚለው። ኢህአዴግ ባለበት የሙስና ደረጃ እንዲሁም የተበታተነና ስለ ልዩነት የሚሰብክ ድርጅት በመሆኑና በብዙ መሠል ምክንያቶች የሊበራል መንግሥትን የመምራት አቅም የለውም። ዓረና ግን ከዚህ በተሻለና ውጤታማ መሆን የሚያስችሉ መንገዶችን በመቀየስ ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- በመጪው ምርጫ በክልሉ ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣት ከሌሎች ተቀራራቢ ሃሳብ ከሚራምዱ ፓርቲዎች ጋር ተዋህዳ ችሁ ወይም በጥምረት ለመሥራት የምታደ ርጉት ጥረት አለ?
አቶ ኣብርሃ፡- ዓረና በሃሳብ ከሚመስሉትና ከሚቀርቡት ጋር ለመሥራት ጥረቶችን ያደርጋል። ነገር ግን ገና ናቸው። በፕሮግራምና በፖሊሲ ከሚመስሉት ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት ፈጥሮ ከኢህአዴግ የተሻሉ አማራጮችን ይዞ የሚቀርብበትን ዕድል ለማመቻቸት እየሠራም ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህወሓት መንግሥት ከአመራርም ሆነ ከልማት አንጻር ለህዝቡ አጎደለ የምትሉት ቁምነገር ምንድነው?
አቶ ኣብርሃ፡- ብዙ ጊዜ ትክክለኛ ያልሆኑ ፖሊሲዎች በሕዝብ ላይ ለመፈፀም ሲሞክር ይወድቃል። በዚህም ሕዝብ ቢጎዳም እንኳ ኢህአዴግ ግን መልሶ ይደግመዋል። ግብርና መር ስትራተጂ ውጤታማ ያልሆነበትን ምክንያት ገምግሞ አካሄዱን ከማሻሻል ይልቅ እንደገና ሲደግመው ይታያል። በዚህም ተመሳሳይ ስህተት እየፈጠረ ተመሳሳይ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ለ27 ዓመታት በሥልጣን ላይ ሲቆይ ሕዝቡ ምንም ዓይነት ለውጥ አላመጣም። ለውጥ የለም ሲባል ምንም አልተሰራም ማለት ሳይሆን መንግሥት መሥራት ከነበረበት አንፃር ሲታይ ግን የተሠራው እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይታያል። ሌላኛው መሠረታዊ ያጎደለው ደግሞ ፍትሕ ነው። የትግራይ ሕዝብ ለ17 ዓመታት የታገለለት ዓላማ ሊሳካም ሆነ ግቡን ሊመታ አልቻለም። የትግራይ ሕዝብ እነዚህን እሴቶች ለማግኘት በርካታ ዓመታት ትጥቅ ትግል ቢያካሂድም እንኳ የፖለቲካ ምህዳሩ፣ ነፃነትና እኩልነትንም ቢሆን ማስፈን አልቻለም።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም የዓረና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገ/ስላሴ ሃሳባቸውን ለመግለፅ ንግግር በሚደርጉበት ወቅት በህወሓት ነባር ታጋዮች ጭምር ሃሳባቸውን እንዳይገልፁ ተደርጓል። በወቅቱ ድርጊቱን እንዴት ገመገማችሁት? ተግባሩስ ምንን ያሳያል?
አቶ ኣብርሃ፡- ድርጊቱ ብዙ አልተሰማንም። ምክንያቱ ደግሞ በትግላችን እስከ ድብደባ የሚደርሱ ብዙ አፈናዎች በመኖራቸው ነው። በወቅቱ የዓረና ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ንግግር በሚደርጉበት ወቅት ሃሳባቸውን እንዳይገልፁ በማጨብጨብ ለማስቆም ሲደረግ የነበረው ጥረት ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ገለልተኛ የሚባሉ መገናኛ ብዙሃን አባላት ተሳታፊ ሆነው ስለተሳተፉና ስላስተላለፉት እንጂ ከዚህ የባሰ ብዙ ችግሮችን አሳልፈናል። በእኛ ላይ ከሚደርሰው በደል አንፃር በማጨብጨብ ሰው እንዳይናገር ማፈን ቀላልና እንደ ችግር የማይታይ ነው። ከዚህ ቀደም ቅስቀሳ ስናደርግ በድንጋይ ተቀጥቅጠን ተወግረናል አልፎም ሰዎች በቢላዋ ታርደው ተገለዋል። የዚህ መሰል ችግር ሰለባ መካከልም አንዱ አቶ አምዶም ናቸው። እንዳይንቀሳቀሱና ቅስቀሳ እንዳያደርጉ እንዲታሰሩም ተደርጎ ነበር። እናም ጭብጨባው ሌላውን አስገረመ እንጂ ለእኛ ያጫረብን የግርምት ስሜት አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- በትግራይን ሕዝብ ላይ አንገት ለማስደፋት የሚሠሩ ሥራዎችና መከበብ እንዳለ በሰፊው ሲነሳ ይደመጣል። ዓረና ችግሩን እንዴት ይመለከተዋል?
አቶ ኣብርሃ፡- አንገት ለማስደፋት የሚባለው ከባድ ነው። ሁሉም እንቅስቃሴ አንገት ለማስደፋት እንደሆነ እየተተረጎመ የትግራይ ሕዝብ መጡብክ፣ ሊይዙክ ነው፣ ሊበሉክ ነው በሚል ውጥረት ውስጥ እንዲወድቅና ሌላ የፖለቲካ አማራጮችንም እንዳያይ ብሎም የፍትሕ፣ የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄዎች እንዳያነሳ ለማድረግ እንጂ ከበባዎች የሉም። እንደተባለው ከበባ እንኳ ቢኖርና ችግር ቢፈጠር አብረን የምንወጣው ይሆናል። ዓረና ከትግራይ ሕዝብ የወጣ ፓርቲ በመሆኑ በክልሉ ሕዝብ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ችግር አብሮ ይጋፈጣል ይከላከላልም። ነገር ግን ምንም ዓይነት ችግር በሌለበት ልንወረር ነው፣ ተከበናል በሚል ሕዝብን ማስደንገጥ ተገቢ ነው ብለን አናምንም።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ቀደምት የህወሓት አመራሮች በአሁኑ ወቅት ካሉ የህወሓት አመራሮች ጋር ሆነው በትግራይ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ተገናኝተዋል። የዳግም ግንኙነቱ አንደምታ ምንድን ነው?
አቶ ኣብርሃ፡- መድረኩን የትግራይ ንግድ ምክር ቤት ነው ያዘጋጀው። ጥሪውም በጋራ የክልሉ ሕዝብ የድል ቀን የሆነውን የካቲት 11 ለማክበር የተደረገ ነው። ባለፉት ዓመታት ህወሓት ሲዘክረው የነበረው ይህ ቀን ከ1993 ዓ.ም በኋላ ከፓርቲው የወጡ ሰዎችም ለብቻቸው ሲያከብሩት ቆይተዋል። በቅርቡ በተካሄደው መድረክ ግን በአንድነት አክብረውታል። ሠላማዊ ትግል ወቅት ፀብ ባለመኖሩም በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ሳቢያ የተለያየ የፖለቲካ አማራጭ በማቅረብ ጉዳይ ነው ሊለያዩ የሚገባው። ይህ ማለት ግን የቀድሞ የድርጅቱ አመራሮች አስተሳሰባቸውን ቀይረው ተመልሰው ወደ ህወሓት ገብተዋል ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። እነዚህ የቀድሞ ታጋዮች በዓረና ውስጥ ያሉ በመሆናቸውም ሲያደርጉ እንደነበረው አስተሳሰባቸውን ይዘው ይቀጥላሉ። ከህወሓት ጋርም ትግላቸውን የሚቀጥሉ በመሆኑም ወደ ህወሓት እንደገቡ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- ‹‹ኣብርሃ የፀረ ትግራይ ቡድኖች መጠቀሚያ እየሆነ ነው›› የሚሉ ትችቶች በስፋት ሲሰነዘርብዎት ይስተዋላልና በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ ኣብርሃ፡- የፀረ ትግራይ መጠቀሚያ እንደሆንኩ ተደርጎ የሚቀርቡ ትችቶች ተጨባጭ ማስረጃ የላቸውም። የማጥላላት ፖለቲካ ለማራመድ የሚደረግ ስትራተጂ ካልሆነ በቀር እኔ የምጽፈውም ሆነ የማደርገው እንቅስቃሴዬ ሁሉ የትግራይን ሕዝብ ማዕከል አድርጌ ነው። በትግራይ ሕዝብ ነው የምመረጠው የምሰራውም ለክልሉ ሕዝብ ነው። በዚህም የክልሉ ሕዝብ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚለውን ለይቼ ነው የምንቀሳቀሰው፡ የትግራይ ሕዝብ በማን ነው በደል እየደረሰበት ያለው በሚል ቢፈተሽ በህወሓት በመሆኑ የምቆመውም ፀረ ህወሓት ሆኜ ነው። እኔ ማስተዳደር የምፈልገውን ሕዝብ እያስተዳደረ ያለው ህወሓትን አሸንፌም ነው የትግራይን ሕዝብ ማስተዳደርና ያሉበትን መሠረታዊ ችግሮች ማቃለል የምችለው። ስለዚህ በህወሓት ላይ ሳተኩር የፀረ ትግራይ ቡድኖች መጠቀሚያ እንደሆንኩ ትችት ይሰነዘራል። ህወሓት ጠላቶች በሚል የሚፈርጃቸው ስላሉ እኔ ህወሓትን መቃወም እንደሌለብኝና መቃወምክን አቁም ለማለት ነው የፈለጉት። እኔ ደግሞ ከ10 ዓመት በፊት ጀምሮ ፀረ ህወሓት ሆኜ ስቃወም ቆይቻለሁ። አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተመረጠ በኋላ አይደለም መቃወም የጀመርኩት። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በሌሎች በመንግሥት አካላት ስህተት ተፈፅሟል ብዬ ሳምን ወደኋላ ሳልል እንዲታረም እቃወማለሁ። እኔ የምታገለው የትግራይን ሕዝብ ለመጥቀም እንጂ ማንንም ለመሳደብ አይደለም የፓርቲ አባል የሆንኩት።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ዓረና ሥልጣን ቢይዝ በምን ዓይነት መንገድ ህወሓትን ተቀብሎ ያስተናግደዋል ተብለው ሲጠየቁ ህወሓት እኛን ሲያደርገን በነበረው መንገድ ብለው ምላሾችን መስጠትዎ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። ህወሓት ደግሞ ሲገልጹ እንደነበረው አፋኝ ከሆነ ትክክልም እንዳልሆነ የሚያምኑ ከሆነ እንዴት ስህተቱን በመድገምና በዚህ መንገድ ሊያርሙት አሰቡ? አስተሳሰቡስ ትክክል ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ኣብርሃ፡- ይህን ምላሽ የሰጠሁት አንድ የህወሓት አባል ጋር ክርክር ሳደርግ ነው። በወቅቱ ህወሓት ጥሩ ነው የሚል መከራከሪያ ሃሳብ አነሳ። ስለዚህ ህወሓት ጥሩ ከሆነ እኛም እንደእርሱ እንሆናልን የሚል ምላሽን ሰጠሁት። ነገር ግን አልተቀበለኝም። ስለዚህ ህወሓት የፈፀመውን ድርጊት እንዳደርግ የማትሻ ከሆነ ድርጅቱ በዓረና ላይ መጥፎ ነገር እየሠራ መሆኑን ታውቃለህ ማለት ነው አልኩት። ንግግሩም የተነሳው በዚሁ ክርክር መካከል ነው። ከጽሁፌም በታች እንደዛ አይደለም ብያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ክልል ከአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይ ከራያ ጋር በተያያዘ የገባበት ውዝግብ አለ። ይህ ውዝግብ እንዴት ሊፈታ ይገባል ትላላችሁ? ችግሩንስ እንዴት ገመገማችሁት?
አቶ ኣብርሃ፡- ዓረና የችግሩን ምንጭ ለማጥራት ሞክሯል። በራያና በወልቃይትም በአካል በመገኘት ነዋሪውን አነጋግረናል። በውይይታችንም ዋናው ችግር አካባቢዎቹ በህወሓት ለመተዳደር ያለመፈለግ እንደሆነ ተረድተናል። በአማራ ክልል አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች የተሻለ አስተዳደርና ፍትሕ እንዲሁም አገልግሎት ያገኛሉ።በትግራይ ክልል ስር ያሉ ወረዳዎች ግን ብዙ በደል ይደርስባቸዋል። ፍትሕ ፈልገው ወደ ተለያዩ ተቋማት ሲያቀኑ ተገቢው አገልግሎት አይሰጣቸውም። ችግሩ እየተነሳ ያለው የራያና የወልቃት ሕዝብ የአማራ ማንነት ስላለው አይደለም። ዓረናም ህወሓትን አብረን ከሥልጣን በማውረድ ፍትህና ነፃነት በማስፈን አብረን እንኖራለን በሚል አነጋግሯቸዋል። መፍትሔው መሆን ያለበትም ሕዝብ መጀመሪያ ፍትሕ እንዲያገኝ መታገል እንጂ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል እንዲቀየር በማድረግ አይደለም። ጥያቄውም የህወሓትን አስተዳደር ያለመቀበል እንጂ ትግራዋይነቱን የመካድና የማንነት ጥያቄን ያነገበ አለመሆኑን ማወቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በነበረን ቆይታ ከዚሁ ከወሰን ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ችግሮች ተጠያቂው ኃላፊነቱን የሚወስደው አዴፓ ነው ብለውን ነበር። አሁን ደግሞ ችግሩን ወደ ህወሓት ገፍተውታልና ሁለቱ ሃሳብ አይጋጭም? ለመፍትሔው ትክክለኛውን የችግሩን ምንጭ መለየት ቀዳሚው ሥራ በመሆኑ የቱ ጋር ነው ችግሩ ያለው?
አቶ ኣብርሃ፡- በሁለቱም ክልሎች ያሉ አካላት ለግጭቱ የራሳቸው ሚና አላቸው። የትግራይ ክልል ችግሩን ከመፍታትና ለሕዝቦች ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ወደ ማስፈራራት እያመራ ነው። በተመሳሳይ የአማራ ክልል መንግሥትም የአማራ ክልልን ሕዝብ የፍትሕና የነፃነት ጥያቄ ሳይመልስ ወደ ሌላ እያየ ችግሩን እያፈናጠረ ነው። ይህም ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰዳቸው ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሁለቱም ክልል መንግሥታት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ሲያቅታቸው ወደ ግጭት መግባትና የተለያዩ ጠብ አጫሪ የሆኑ መግለጫዎችን እያወጡ ችግር እየፈጠሩም ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ፓርቲያችሁ እንደሚቃወም አሳውቋል። መነሻው ምንድን ነው?
አቶ ኣብርሃ፡- ማንኛውም ሥራ ሲሠራ በሠላማዊ መንገድ መሆን እንዳለበት ያምናል። በክልሎቹ መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ መፈታት ያለበትም የሁለቱም ክልል መንግሥታት ታርቀው፣ ተመካክረውና ተቀራርበው በመወያየት ነው። ችግሩም መፈታት ያለበት በመንግሥታቱና በሕዝቡ እንጂ መንግሥታቱና ሕዝቦች ሳይስ ማሙ ኮሚሽን ቢቋቋም ለውጥ አያመጣም። ለአብነት የትግራይ ክልል መንግሥት ኮሚሽኑን አልተቀበለውም። ሳይቀበለው ሥራ ቢጀመር ወደ ግጭት ያመራል ማለት ነው። ስለዚህ ሁለቱ መንግሥ ታት በቅድሚያ እንዲቀራረቡ በማድረግ ጉዳዩ እንዲፈታ ጥረት ማድረግ እንጂ በፌዴራል መንግሥት ኮሚሽን ተዋቅሯልና ይፈታል ማለት በሁለቱ ክልሎች መካከል ጦርነት ይኑር እንደ ማለት ነው። ዓረና የሚፈልገው ሠላም በሚያሰፍን መልኩ ችግሮች እንዲፈቱ በመሆኑም ኮሚሽኑ ውጤት አያመጣም በሚል አልተቀበለውም።
አዲስ ዘመን፡- በትግራይ ክልል መንግሥትና በፌዴራል መንግሥት መካከል ልዩነቶች እንደተፈጠሩ ይነገ ራል። በእርሶ ይህንን እንዴት ነው የሚመለከቱት? ለውጡንስ እንዴት ይገ መግሙታል?
አቶ ኣብርሃ፡- በህወሓትና በኢህአዴግ መካከል ልዩነት አለ ወይ የለም? የሚለውን ማወቅ አልችልም። መገመት ነው የሚቻለው። ግምት ደግሞ አያዋጣም። ጉዳዩ ሲነሳ ቢሰማም ልዩነት እንዳላቸው ግን ተጨባጭ ማስረጃ የለም። እንደ ፓርቲ አንድ ሆነው እየሠሩ እንደሆነ ነው የሚታወቀው። ህወሓት ግን የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት የትግራይ ሕዝብ ከፌዴራል መንግሥት ጋር እንደተጣላ፣ የፌዴራል መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ለመጨቆን፣ ለመደብደብና ለማጥፋት ዕቅድ እንዳለው በማስመሰል ያቀርባል። ልዩነቱም በሁለቱ መካከል እስከ ጦርነት ድረስ ሊያመራ እንደሚችል ለሕዝቡ እየተነገረው ነው።
በዓረና አቋም መሠረት መለያየታቸውንም ሆነ እንደማይግባቡ ይፋ እስካላደረጉ ድረስ ደግሞ በአንድነታቸው ነው የምናያቸው። በአገሪቱ ያለውን ለውጥ አስመልክቶም እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ከኢህአዴግ የምንፈልገው ቁልፍ ጉዳይ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት ነው። ይህ ደግሞ እስረኞችን መፍታት፣ መገናኛ ብዙሃንንና ሕዝቡን ነፃ ማድረግ፣ ፓርቲዎች እንደፈለጉ እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል እንዲሁም ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤትና ፖሊስን ነፃ ማድረግን ይጠይቃል።
በአብዛኛው ከዚህ አንፃር ጥሩ የሚባሉ ለውጦች ይታያሉ። በትግራይ ክልል ግን ምንም ዓይነት ለውጥ የለም። የፖለቲካ እስረኞች አልተፈቱም፣ መገናኛ ብዙሃኑ ነፃ አይደሉም፣ ምርጫ ቦርዱም እስከዛ ድረስ የዘለቀ መዋቅሩን አልዘረጋም። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ያለው የተወሰነ ተስፋ ሰጪ ለውጥ በትግራይ ክልል እየታየ ባለመሆኑ ለውጡ በሁሉም አካባቢ የሚታይ እንዳልሆነ ያሳያል። ከለውጡ ጋር በተያያዘ በአገር ደረጃ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ከፀጥታ፣ አለመረጋጋትና መፈናቀል ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉት ችግሮች ናቸው። ኢህአዴግ በሁሉም አካባቢዎች መንግሥታዊ ቁጥጥር ስለሌለው የፀጥታ ጉዳይ በጣም አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ለውጥ መጥቷል ብለው የጠቀሷቸውን ሀሳቦች የሚጋሩ አካላት እንዳሉ ሆነው በተቃራኒው ደግሞ አገሪቱ ስጋት እየተጋረጠባት እንደሆነና ለውጥ እንደሌለ ደግሞ ሲነሳም ይደመጣልና ይህን እንዴት ያዩታል?
አቶ ኣብርሃ፡- ከዚህ ቀደም የነበረው ህወሓት ኢህአዴግ በደህንነት መዋቅሩ ሁሉንም አገሪቱን ተቆጣጥሮ ስለነበር አንፃራዊ መረጋጋት ነበር። ነገር ግን ውጤታማ ነበር ማለት ደግሞ አይቻልም። ዜጎች አፈናን መሸከም እንደማይችሉ በይፋ ካመጹ በኋላ መዋቅሩ ጠፍቷል። ከጠፋ በኋላ ደግሞ የመንግሥት መዋቅር ሳይሆን ገዢ ፓርቲ ስለነበር ነፃ ተቋማቱ ባለመኖሩ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ሲዳከም በአመጽና በተለያዩ ምክንያቶች አለመረጋጋት መፈጠሩ ባህርያዊ ነው።
ገለልተኛ ተቋማት በሌሉበት የፓርቲ ወይንም የፖለቲካ ለውጥ ሲኖር አለመረጋጋቶች ይኖራሉ። ይህ ደግሞ በየትኛውም አገር ሊከሰት የሚችል ነው። ለውጥ የለም ማለት ባይቻልም ለውጡ ወደ ጥሩ ወይስ ወደ መጥፎ ጎዳና የሚወስድ ነው? የሚል መከራከሪያ ግን ሊነሳ ይችላል። አለመረጋጋት አለ አገሪቱም የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባታል በሚል የሚያነሱ አካላትም ለውጥ የለም ማለታቸው ሳይሆን ለውጡ ወደ መፈራረስ የሚወስድ ነው እያሉ ነው።
በእኔ ዕምነት ደግሞ ለውጡ ወደ መፈራረስ የሚወስድ አይደለም። ብዙ የፀጥታ ችግሮች ግን ሊኖሩ ይችላሉ። ምክንያቱ ደግሞ ኢህአዴግ በ27 ዓመታት የመንግሥት መዋቅር ሳይዘረጋ የአገዛዝ ሥርዓት መስርቶ መቆየቱ ነው። በዚህ ሂደት የህወሓት የደህንነት መዋቅር ሲዳከም አፋጣኝ መፍትሔን የሚፈልጉ የፀጥታ ችግሮች እያጋጠሙ ነው። ችግሮቹ በአግባቡ ካልተፈቱ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ማምራቱና መጥፎ ውጤትንም ሊያመጡ ይችላሉ። ስለዚህ ለውጡ ወደ ጥሩና ሕዝቦች ወደሚሹት አካሄድ እንዲያመራ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- ችግሮቹ ምን ዓይነት የመፍትሔ እርምጃዎችን ነው የሚሹት?
አቶ ኣብርሃ፡- ኢህአዴግ እንደምንም ብሎ መንግሥታዊ ተቋማትን በመዘርጋት በአገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ፀጥታን በማስፈን ሕዝብ በመንግሥት ላይ ዕምነት እንዲኖረው ማስቻል ይጠበቅበታል። ህዝብ ጠብመንጃ መግዛት እንደማያስፈልገው፣ መንግሥትና የፀጥታ መዋቅሩ ከስጋት እንደሚጠብቁት እስኪያምን ድረስ መንግሥት ሁሉንም ወደ ጎን በማለት ለሠላም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መረጋጋትን ማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየትና እንዴት የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ እንደሚገባ መምከር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን!
አቶ ኣብርሃ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
ፍዮሪ ተወልደ