ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃል ገብተው አገሪቱን መምራት ከጀመሩ አንድ ዓመታቸውን ሊደፍኑ ነው።በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገራት ውጤታማ የሚባል ሥራዎች አከናውነዋል።ከዚህ ውስጥ ደግሞ በአገር ውስጥ ይሁን በውጭ የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ጥረት ማድረጋቸው ይጠቀሳል።
የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በፖለቲካው እየተሳተፉ ቢገኙም ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ አስተያየት የሰጡ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ይናገ ራሉ። በለውጡ እንቅስቃሴ ዓላማና ሃሳባቸውን ለህዝቡ በሰፊው እያዳረሱ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢ የለውጥ እንቅስቃሴው እታች ድረስ የወረደ ባለመሆኑ አሁንም ድረስ የከተማና የዞን አመራሮች የህዝብ ስብሰባዎችን እያ ደናቀፉ መሆናቸውንም ይገ ልፃሉ።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመ ንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተመረጡ ጊዜ ጀምሮ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በፖለቲካው ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጨምር ተስፋ ሰጪ ተግባራት ተከናውነዋል።ከነዚህም ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ በጋራ ለመስራት ያደረጉት ጥረት፣ መለወጥ የሚገባቸው የህግ ማዕቀፎች በተለይ የምርጫ ህጉ እንዲሻሻል መደረጉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት የቃል ኪዳን ሰነድ መፈራረማቸው፣ የጸረ ሽብርና የመገናኛ ብዙኃን ህጎች እንዲሻሻሉ እየተሰራ መሆኑና ሌሎች ተግባራት ተጠቃሽ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የፖለቲካ ምህዳሩ ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ሲነጻፀር የተሻለ ነገር ቢኖርም መሆን ከነበረበት አንፃር ሲታይ ግን ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩም ግን ያስረዳሉ። ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ቢኖሩም በሌላ ጎን ተስፋ አስቆራጭና አገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮች እንደሚስተዋሉ የጠቀሱት ፕሮፌሰር መረራ፤ ቅድሚያ ኢህአዴግ ለውጥ ለማምጣት መዘጋጀቱን፣ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ እንዲመጣ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲፈጠሩና በተለይ ስልጣን ለመል ቀቅ ምን ያክል ቁርጠኛ ነው የሚሉት ጥያቄዎች እንደሚመለሱ የተረጋገጠ ነገር አለመኖሩን ያመለክታሉ።
በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ወታደራዊ ስልጠናዎች ማካሄዳቸው አስጊ መሆኑንም ፕሮፌሰር መረራ ይገልፃሉ። እንደ ፕሮፌሰር መረራ ገለፃ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የጋራ አጀንዳ አልፈጠሩም። ብሄራዊ መግባባት የመፍጠሩ ጥያቄ ለመመ ለስ ከፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ ውጪ የተሰራ ሥራ የለም። በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ጉዳይ ስጋት መፍጠሩና የተፈናቀሉ ወገኖች መብዛት አገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትሆን አድርጓታል።
ገዥው ፓርቲን ጨምሮ በፓርቲዎች አካባቢ የሚታየው ነገርም ተስፋ ሰጪ አይደለም። በአዲስ አበባ ጉዳይ ከተማዋ የነዋሪዎቿ እና አዲስ አበባ የኛ ናት በሚሉ ቡድኖች ግጭት ቢፈጠር አላስፈላጊ ችግር በአገሪቱ ይፈጠራል። የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገም እየታሰበ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው። በቀጣይ ብሄራዊ መግባባት በመፍጠር መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አገሪቱ በምን ዓይነት መንገድ ትተዳደር የሚለው መሬት የያዘ ነገር እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ።
የአገሪቱ ፖለቲካ የሚመራበት ፍኖተ ካርታ ቢኖር ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ የሚል ቡድንን እና የህዝብ ቆጠራው ይካሄድ አይካሄድ የሚል ቡድንን ለማርገብና እርምጃ ለመውሰድ እንደ ሚያግዝ ያብራራሉ። የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተመረጡ አንድ ዓመት ውስጥ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካው ምህዳር ሰፍቷል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይጠቅሳሉ።
በምሳሌነትም ፓርቲያቸው ከሁለት ሳምንት በፊት በሆሳዕና ከተማ ስብሰባ ሲያዘጋጅ ስብሰባውን ለማደ ናቀፍ የከተማ አስተዳደሩ ብዙ ጥረት ማድረጉን ያስታውሳሉ። ነገር ግን ህዝቡ በጉል በቱ ፈንቅሎ ወጥቶ ስብሰባው መካሄዱን ይገልፃሉ። ሆኖም ከተማ አስተዳደሩ ስብሰ ባውን ወደሌላ ቀን አዘዋውሩ የሚለውን ትዕዛዛቸውን ባለመቀበል ስብሰባው በሰላም መጠናቀቁን ያስረዳሉ። በፖለቲካው ምህዳር ላይ አሁንም እንደቀድሞ አፈና አለ የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ አንድ ፓርቲ ስብሰባ ሊያካሂድ ሲፈ ልግ ከሁለት ቀን በፊት ማሳወቅ አለበት በሚለው መመሪያ መሰረት ፓርቲያቸው ቀድሞ ቢያሳውቅም ፈቃድ እየተከለከሉ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
በየአካባቢው ተፎ ካካሪ ፓርቲዎች ስብሰባ እንዲያካሂዱ ከመንግሥት ፍላጎት እንደሌለ ይጠቅሳሉ። በየክልሉ እነዚህ አደናቃፊ እንቅስቃሴዎች እያሉ የፖለቲካ ምህዳር ስፍቷል ሊባል እንደማይቻል ያብራራሉ። እንደ ፕሮፌሰር በየነ አባባል፤ ለውጡ ህዝቡ ድረስ መውረድ አለበት። የለውጥ እንቅስቃሴው ክልሎች፣ ዞንና ወረዳ ድረስ ሊወርድ ይገባል። በአሁኑ ወቅት ግን የለውጥ እንቅስቃሴው እታች አይታይም። በክልሎች አካባቢ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተስፋ ቆርጠው እንዲወጡ ጥረት እየተደረገ ነው። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ እንደሚናገሩት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተመረጡ ጊዜ ጀምሮ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካው ምህዳር ሰፍቷል።
ቀደም ብሎ የፖለቲካ ምህዳሩ የጠበበት ሁኔታ ነበር። ለህዝብ የሚታገሉ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ተገድቦ ነበር የቆየው። ይህን ሁኔታ ለማሻሻል የለውጥ ሀይሉ በወሰደው እርምጃ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡ ተደርጓል። ተፎካ ካሪ ፓርቲዎች አሁን ህዝባቸው ውስጥ ሆነው እንዲታገሉ እድል ማግኘታቸው ደግሞ ትልቅ ፋይዳ አለው። በሰላማዊ መንገድ የሚደረገውን ትግል ለማበረታታት መንግሥት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው ውይይቶች ጠቀሜታ አላቸው የሚሉት አቶ ቶሌራ፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ወደ አገር ከገባ በኋላ በሰፋ መልኩ ከህዝቡ ጋር እየተወያየ እንደሚገኝና የያዘውን ዓላማና ሀሳቡን ለማሳወቅ ዕድል ማግኘቱንም ይናገራሉ።
እንደ አቶ ቶሌራ ገለፃ፤ ህዝቡ የነፃነትና የዴሞክራሲ እጦት ስለነበረበት ተቃው ሞዎችን አስነስቶ ነበር። የህዝብ ጥያቄን ለመመለስ የመጣው ለውጥ ገና አንድ ዓመቱ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥም አዲሱ የለውጥ አመራር በሰላማዊ መንገድ ሥራዎችን ማከናወን ጀምሯል። በቀጣይ መንግሥት ባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያሉ ቅራኔዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መጣር አለበት። ድርጅቶች በበኩላቸው የገቡትን ቃል በማክበር ለውጡን ለማገዝ መስራት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
መርድ ክፍሉ