የሩሲያዋ ክራስክኖያስክ የተሰኘች ከተማ ሽር ጉድ ስትልለት የቆየችውን ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ አካሂዳለች። ስፖርት ወዳዶች ይህንን ሲመለከቱ መቼም «በየትኛው ስፖርት ይሆን?» የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም። በእርግጥ ውድድሮች ከስፖርት ባሻገርም በተለያዩ ዘርፎች መዘጋጀታቸው አይቀርም። ይህንን የውድድር ዓይነት ሲያውቁ ግን መሳቅዎና መደነቅዎ አይቀርም (በእኔ ይሁንብዎ)።
ይህ ውድድር ከተለመደው የተለየ ሲሆን፤ ለመሳተፍ በስፖርት ሜዳ እና ጂምናዚየሞች አድካሚ ልምምድ መስራት እንዲሁም የስፖርት ትጥቅና ቁሳቁስ ይዞ መቅረብ አይጠበቅም። በውድድሩ ለመሳተፍ ጉንጭዎን ማጠንከረና እጅዎን ለሰላ ጥፊ ማዘጋጀት ብቻ ነው ያለብዎ። ከዚያማ የመማታትና የጭካኔ ልምድና ችሎታዎን ተጠቅመው ተፎካካሪዎን መጠፍጠፍ ብቻ ነው። አሁን ነገሩን የተረዱት ይመስለኛል፤ የሩሲያዋ ከተማ ያሰናዳችው የጥፊ ሻምፒዮና ነው።
ይህ ውድድር በህዝቡ ዘንድ የተወደደ ሲሆን፤ ያለፈው ዓመት ልክ በዚህ ወቅት በሞስኮ ተካሂዶ እንደነበረ የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያሳያል። ያኛውን ሻምፒዮና የሚለየው ግን አካላቸውን ለዚሁ ሲሉ ባዳበሩ ስፖርተኞች መካከል መካሄዱ፤ ይሄኛው ደግሞ ፍላጎቱ ባላቸው መካከል በመሆኑ ነው። አዘጋጆቹ እንዳስታወቁት ከሆነም ይህንን ውድድር ለማዘጋጀት ያነሳሳቸው ፍላጎቱ ላላቸው ሰዎች እድሉን ለማመቻቸት ሲሉ ነው።
ውድድሩ እንዲህ ነው፤ ተሳታፊዎች ከተዘጋጀው ጠረጴዛ ፊት ለፊት ይቆማሉ። ከዚያም ተራ በተራ የቻሉትን ያህል ኃይል በማውጣት በጥፊ ይመታታሉ። በዚህ መካከል የአንዱ አመዝኖ ሌላኛውን ማንገዳገድ ከቻለ አሸናፊ ይሆናል። ይህ ካልሆነ ግን ከሶስት ሶስት ጥፊ በኋላ ዳኛው አስቁመው በቴክኒካዊ ብቃታቸውና በሰነዘሩት ኃይል ተመስርተው አሸናፊውን ይለያሉ።
ውድድሩ እውቅና ያገኘ ባይሆንም ጥቂት ህጎች ግን አሉት። ለአብነት ያህል ጉዳትን ለመቀነስ በሚል በእጅ መዳፍ መማተት አይፈቀድም፣ ከጉንጭ አልፎ ጥፊውን በአይን እና ጆሮ ላይ ማሳረፍም የተወገዘ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ግዙፍ አካልና እንደ አንበሳ የሰፋ መዳፍ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ሲገጥሙ ጉንጭን እንደ ወረቀት ስለሚያርገበግቡ ጉዳቱ ሚዛንን ስቶ እስከመውደቅ ያደርሳል።
በዚህ አስደናቂ ውድድርም የ28ዓመቱና 168 ኪሎ ግራም የሚመዝነው አርሶ አደር ቫስሊ ካሞቴስኪ ሻምፒዮን በመሆኑ የ470ዶላር ተሸላሚ ሆኗል። ይህ ዜና በመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሽፋን ካገኘ በኋላም የውድድሩ አዘጋጆች በሌሎች ውድድሮች ላይም ተሳታፊ እንዲሆን ግብዣ እንዳቀረቡለትም ነው የገለጸው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
ብርሃን ፈይሳ