ካልጠፋ ነገር ፎቶ አይወጣልኝም፤ በዚህም ምክንያት ፎቶዎቼን ለማየት አልበም ስጠየቅ ወይም «ለማስታወሻ የሚሆን ፎቶ እንነሳ» ሲሉኝ እሸማቀቃለሁ። እዚህ አልበም ውስጥ የምመለከተው ግን ዓይኔን ማመን እስኪያቅተኝ እጅግ የሚያማምሩ ፎቶዎችን ነው።
በቅርቡ ጋብቻቸውን የፈጸሙ ጓደኞቼን «ቤት ለእምቦሳ» ለማለት ከቀለሷት ጎጆ ተገኝቼ ነው። ከተጋቢዎቹ ጋር ከትምህርት ቤት ጀምሮ የምንተዋወቅና ቅርበትም ያለን በመሆኑ ሚዜ የመሆን ወግ ደርሶኛል። እናማ እየተጨዋወትን ሳለ የሰርጋቸውን ፎቶ እንዳይ አልበም ሲያቀብሉኝ መሸማቀቅ የደስታ ስሜቴን ተረከበ።
ፎቶ መነሳት ባልወድም ሚዜ በመሆኔ አብሬያቸው በርካታ ፎቶዎችን መነሳቴን አስታውሳለሁ። የምመለከተው ግን ከጠበቅኩት በተቃራኒ፤ ፎቶ የማይወጣልኝን እኔን ጨምሮ የሁላችንንም ውብ ፎቶ ነው። እውነት ለመናገር የተነሳናቸው ፎቶዎች ሁሉ አስደናቂ ነበሩ። አንዳንዱ ግን ግራ እስኪያጋባኝ ድረስ ባልሄድንባቸውና ባልነበርንባቸው ቦታዎች የተነሱ ነበሩ። ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ባሻገር የሄድንበትን ስፍራ ባላስታውስም የፎቶዎቻችን መገኛ ግን ከወንዝ ዳር፣ ከድልድይ ላይ፣ ከባቡር ሃዲድ ላይ፣ ከአሮጌ ህንጻ ደረጃዎች ላይ፣ በሚያማምሩ የአትክልት ቦታዎች፣ ጸሃይ ስታዘቀዝቅ፣… የሚታዩ ነበሩ።
የማስታወስ ብቃቴን ስላጠራጠረኝ «እዚህ ቦታ ሄደናል እንዴ?» ብዬ ጠየቅኩ። ሙሽራው ከሳቁ ጋር እየታገለ «የትም አልሄድንም፤ በኤዲቲንግ የተጨመረ ነው» አለኝ። በሌለንበት ኖረን ይህንን መሰል ምስል ማስቀረታችን ስላስደነቀኝ ከመምሰጤዬ አልፌ በሃሳብ ጭልጥ አልኩ። ስለተለመደ ብቻ፣ ጊዜ አመጣሽ በመሆኑ ብቻ፣ ስለተፈለገ ብቻ፣ ፎቶውን ለማሳመር ብቻ፣ … ይህንን በማድረጋቸው ምን ያተርፉ ይሆን? ምናልባትም ሰዎች ሲመለከቱት «ሰርጋቸውን በእዚህ ስፍራ ተገኝተው አከናወኑ» ይሉ ይሆናል።
ዓመታት ካለፉም በኋላ ልጆቻቸው ወላጆቻቸው እንዲህ ባለ ሁኔታ መጋባታቸውን እንደ ታሪክ ይመለከቱ ይሆናል። ግን ግን ራስን በዚህ መልኩ ማሳመን ይቻላል? ለነገሩ ምን ይሄ ብቻ፤ በሌለንበት እንዳለን ሆነን አይደል ነገርን ሁሉ ደበላልቀን ግራ የምንጋባው? አብዛኛዎቻችን ያለንበትን፣ የተገኘንበትን፣ የደረስንበትን እና የቆምንበትን አስተውለን ከመኖር ይልቅ፤ ባልተገኘንበት «ነበርን» በሚል አስተሳሰብ ተተብትበናል። ይህንን ከዚያ፤ ያንንም ከዚህ ማጣረስና ማወሳሰብ ስራችን ከሆነ ስለ ሰነባበተም የምናነሳው እያንዳንዱ እርምጃ ጠልፎ እየጣለን ጉዟችን ባሉበት መርገጥ ሆኗል።
አስተውላችሁ ከሆነ አሁን ከማያግባቡን ጉዳዮች መካከል አንዱ ታሪክ ነው። ካለፈው ታሪካችን መልካም መልካሙን የራሳችን፤ ጥሩ ያልሆነውን ደግሞ የሌላው በማድረግ ብሽሽቅ ውስጥ ገብተናል። «ንጉስ እከሌ እንዲህ ነበሩ፣ …የተባለው ብሄር አመጣጥ ከዚህ ነው፣ …የተባለው ስፍራ ቀድሞ የእነ … መኖሪያ ነበር፣…» በሚል መባላታችን ውሎ አድሯል። ከሰሞኑ የሰማሁት አንድ አባባል ነበር «በማበጠሪያ የሚጣሉት መላጦች ናቸው» የሚል።
እውነት እኮ ነው ወገን፤ 100 ዓመትና ከዚያ በላይ ዕድሜ ላስቆጠረ ታሪክ እንዲህ መሆን ጊዜውን ይመጥናል? ዛሬ ላይ የቆምነው እኛ እኮ የዚያኔ አልነበርንም። ታዲያ ባልነበርንበት «አለን» እያልን ለምን እንተላለቃለን? ሌላ ደግሞ አለ፤ «ተምሬያለሁ፣ ሁለት ዲግሪ ጭኛለሁ በ… እና በ… ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች የምስክር ወረቀቶችን በክብር ተረክቤያለሁ» እያለ ራሱን የሚክብ። ነገረ ስራው ግን መስዋዕትነት ከፍሎ ካስተማረው ቤተሰብና ሀገር ጋር በእጅጉ የተጻረረ። ትምህርት አስታሳሰብን የሚያሰፋ እና የተሻለ ነገርን ለማየት የሚያስችል መነጽር ሆኖ ሳለ፤ ዕውቀቱን ለመጥፎ ነገር የሚያውል።
በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዕውቀትን የገበዩት እነዚህ «ምሁር» ተብዬዎች ሲሆን ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ አስተሳሰብና አመለካከት ማራመድ ነበረባቸው። ከራሳቸውም አልፈው እኛን ማስተማር፣ ማሳወቅና ማሰልጠን ይጠበቅባቸዋል። እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፤ ዞረው ምስኪኑን ህዝብ «ተበድለሃል፤ ተጨቁነሃል» እያሉ ከሰፈርና መንደር ያነሰ አስተሳሰባቸውን ያንጸባርቁበታል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች እውቀታቸውን ካልተጠቀሙበት የመማራቸው ትርፍ ከምን ላይ ነው? እኔ ግን ሳይማሩ ዲግሪ የሰበሰቡ ነው የሚመስለኝ (በሌሉበት ኖረው ማለት ነው)።
አንዳንዱ ደግሞ ስለ ደሃው ህዝብ መብት «ያገባኛል» በሚል ልብ አድርቅ ክርክር ይጠመዳል። በአሜሪካ እና አውሮፓ በቅንጦት ተቀምጦ ህዝቡ እንዴት ውሎ እንዳደረ ከወሬ በሚያገኘው ብቻ ተነስቶ ለድሃው ዋስና ጠበቃ ለመሆን ይዳዳዋል። እስኪ አስቡት ይህ ሰው በምን ተዓምር ነው በሌለበት ሊኖር የሚችለው? ዛሬ ዛሬ፤ «እኔ አውቅልሃለሁ፣ እኔ እወክልሃለሁ፣ እኔ የምልህ ብቻ ትክክል ነው» የሚለው አመለካከት የሰረፀባቸው ሰዎች ከየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል። እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ በትምህርት፣ በፖለቲካ፣ አንዳንዴም በሀብት «የእኔ» በሚሉት ማህበረሰብ ዘንድ ተሰሚነትና ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። ታዲያ ይህንን በመጠቀም የግል ሀሳባቸውንና ፍላጎታቸውን በምስኪኑ ህዝብ ላይ ይጭኑታል።
የሚያሳዝነው ግን የነገራቸው መጨረሻ ሀሳብ በመቀበል እና መረጃ በመለዋወጥ የሚቆም ሳይሆን ብዙዎችን ለከፋ ጉዳት፣ ለህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት እንዲሁም ለመፈናቀል የሚዳርግ መሆኑ ነው። እኔ ያለፈውን ታሪክ ስላልደረስኩበት በቅጡ የማላውቀው ቢሆንም በእድሜዬ እንደተገነዘብኩት ብዙ ጊዜ እነዚህ «ተመራጭና ተሰሚ ነን» ባዮች አንዳች መስዋእትነት የሚጠይቅ ጉዳይ ሲፈጠር ጓዛቸውን ጠቅለው ሀገር ይለቃሉ።
ያኔ በገሀዱ መድረክ ከታሪኩም ከነባራዊውም ሁኔታ የሚመጣውን ሁሉ በተግባር የሚወጣው ደሀው ወገን ብቻ ነው (እነርሱማ ቀድሞውንም ሳይኖሩ አይደል «አለን» የሚሉት)። እንዲያም ከሆነ በኋላ «የታሪኩ ባለቤቶች እኛ ነን» የሚል ድርሳን ካሉበት ይደርናል፤ እኛ ምስኪኖቹም ያልነበረውን «አለ» የሚል ተረት ለትውልድ እያስተላለፍን እናልፋለን። ወገን እንደ ጉም የማይጨበጡ፤ እንደ ክረምት ጸሃይም «አሉ» ሲሏቸው የሚጠፉ ሰዎች በዝተዋል።
ታዲያ ከእኛ በእጅጉ ያነሱትን እነዚህን ሰዎች ያሉትን ሁሉ ሰምተን መከተል አለብን? «እንዲህ ነው» ሲሉን፤ «እንዴት፣ መቼ፣ ለምን፣ ከየት፣ በማን፣…» ብለን መጠየቅ የለብንም? ተጨበጠ እና የታመነ መረጃ ሳናገኝስ «ሆነ» ያሉንን ሁሉ «ሆኗል» የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ አለብን? ማስተዋል የሚጠቅመው እዚህ ላይ ነው፤ በሌለንበት እየኖርን ከሆነ እየዋሸን እንጂ እየኖርን አይደለም ማለት ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
ብርሃን ፈይሳ