የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከዳር እስከ ዳር ያነቃቃና ሕዝቦቿንም ያስፈነጠዘው የድል ስሜት አሁንም አልበረደም። ብርቅዬዎቹ ዋልያዎች በሀገራቸው ዓለም አቀፍ ጨዋታን ማድረግ የሚያስችል ስታዲየም በማጣታቸው ወደ ገለልተኛ አገር ማላዊ ተሰደው ጣፋጩን ድል ከባሕርማዶ ለሕዝባቸው ልከዋል። ዋልያዎቹ ከስልሳ ዓመት በኋላ የአፍሪካ እግር ኳስ ኃያሏን አገር ግብጽን ማሸነፋቸው ድል ማድረጋቸው ከስፖርት የበለጠ ብዙ ትርጉም እንዳለው ተደጋግሞ ተነግሯል።
በዚህ ታሪካዊ ድል በተመዘገበበት ጨዋታ ዋልያዎቹ ፈርኦኖቹን አሳምነው ያሸነፉበት መንገድ እንዲሁም ቴክኒካዊ ጉዳዮችን አንስቶ ዛሬ ላይ መተንተንም አንባቢን ማሰልቸት ነው። በአጭሩ ዋልያዎቹ ከተከላካይ እስከ አማካኝ፣ ከአማካኝ እስከ አጥቂ መስመር ድንቅ ነበሩ ብሎ ማለፍ በቂ ነው።
ዋልያዎቹ ለዘመናት ዝቅ ተደርገው ከሚታዩበት ደረጃ ወደ ከፍታው ተመልሰዋል። ከዚህ ከፍታ እንዳይንሸራተቱ ምን ይደረግ የሚለው ጉዳይ የሁሉም የቤት ሥራ መሆን አለበት። ለዚህም ብዙ መስተካከል ካለባቸው አስተዳደራዊ ዝርዝር ነጥቦች ውስጥ አንኳሮቹን መጠቆም ወይም ማስታወስ ተገቢ ነው።
ይህ የዋልያዎቹ ልብን የሚያሞቅና የሁሉም ኩራት የሆነ ድል ነገም እንዲቀጥል ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጀምሮ በፌዴሬሽን በኩል ከወዲሁ ዝርዝር እቅዶችን አውጥቶ መዘጋጀት ቀዳሚ ጉዳይ ነው። አንድ አሰልጣኝ ምን ጊዜም ከትልቅ ድልም ይሁን ሽንፈት በኋላ ቀጣይ ትኩረቱ ከፊቱ ያለው ፍልሚያ ነው። የዋልያዎቹና ፈርኦኖቹ ፍጥጫ አሁንም አላበቃም።
በቀጣይ መስከረም ላይ የመልሱ ጨዋታ በካይሮ ይደረጋል። በሐሙሱ ምሽት ጨዋታ አስደንጋጭ ሽንፈት የገጠማቸው ፈርኦኖቹም ከደረሰባቸው ትችት(ውግዘት ማለት ይቀላል) አገግመው ሕዝባቸውን በተሻለ ድል ለመካስና ዋልያዎቹን ለመበቀል ያንን ቀን እንደሚጠብቁት እርግጥ ነው። ለዚህ ዋልያዎቹም ከወዲሁ በስነልቦናም በአካል ብቃትና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም። የአሁኑ ድል አንዴ ተመዝግቧል፣ታሪክም ያስታውሰዋል።
የበለጠ ትርጉም ያለው ድል እንዲሆን ግን ስለመልሱ ጨዋታም ማሰብ ያስፈልጋል። ዋልያዎቹ ከየትኛውም የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ያነሰ አቅም እንደሌላቸው አሳይተዋል። በእርግጥ ከዚህ ቀደም በተለይም ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እንደ ኮትዲቯር ያሉ ግዙፍ ቡድኖችን በማሸነፍ ብልጭ ብሎ ሳናጣጥመው የሚጠፋ ተስፋ አሳይተውናል። ነገር ግን ቀጣይነት የለውም።
ለምን? ይህን በአግባቡ አጢኖ ዋልያዎቹ ፈርኦኖቹን በረቱበት ጨዋታ የነበራቸውን በውጤት የታጀበ አቅም እንዴት በቀጣይ ጨዋታዎች መድገም ይቻላል የሚለውን ጉዳይ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትና የቴክኒክ ኮሚቴው ጊዜ ወስዶ ሊመለከተው ይገባል። ጎን ለጎንም ፌዴሬሽኑ የተሻሉ ከሚባሉ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ዋልያዎቹ በርካታ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማድረግ አቋማቸውን እየፈተሹ በጎደለው የሚሞሉበትን፣ የተጣመመውን የሚያቀኑበትን እድል መፍጠር ለነገ የሚለው የቤት ሥራ መሆን የለበትም።
ፌዴሬሽኑ ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጪ ጨዋታዎችን ለማድረግ በመገደዳቸው በአንድ ጨዋታ ለሜዳ ኪራይና ለመሳሰሉት ብቻ እስከ ሃምሳ ሺ ዶላር ወጪ እንደሚያደርግ ባለፈው መግለጫው ጠቁሞ ነበር። ይህም ካለው አቅም አንጻር ብዙ እንደማያራምደውና ጨዋታዎችን ከአገር ውጪ ሄዶ ማድረግ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚሳነው ስጋቱን ገልጾ ነበር። ይህ ዋልያዎቹና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በተነቃቃበት በዚህ ወቅት በሕዝብ ስሜት ላይ ውሃ ሊከልስ የሚችል አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
ነገ ዋልያዎቹ በዚህ መነቃቃት ላይ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማምራት እድላቸው እየሰፋ ሲሄድ ይሄ አይነቱ እንቅፋት ሊነሳ አይገባም። መንግሥትም ይሁን የሚመለከተው አካልና ባለሃብቶች ድሎች ሲመዘገቡ ጮቤ ከመርገጥና ጊዜያዊ ሽልማቶችን ከማዥጎድጎድ በዘለለ ስለ ዋልያዎቹ ቀጣይ መንገድ ማሰብ አለባቸው።
ይህን የፋይናንስ ጉዳይ እንቅፋት እንዲሆን ካደረጉ ምክንያቶች ዋነኛው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በሜዳዋ የሚያስተናግድ ስታድየም አለመኖሩ ነው። ከዚህ ቀደም ይህ የስታድየም ችግር ሲነሳ “ለየትኛው እግር ኳስ ነው” የሚሉ ምላሾች ከተለያዩ ወገኖች ሲሰጡ ማየት የተለመደ ነው። የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድም ባለፈው የፓርላማ ንግግራቸው በስታድየሞች ዙሪያ በሰጡት ምላሽ “መጀመሪያ ሠርታችሁ የተሻለ ነገር አሳዩ፣አፍሪካ ዋንጫና ኦሊምፒክ ላይ ደጋግማችሁ በመሳተፍ ውጤት አሳዩን” በማለት መናገራቸው ይታወሳል። እርግጥ ነው መንግሥት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታድየሞች እንዲኖሩ ትኩረት ለመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን ማሳያዎች ይፈልግ ይሆናል። ዋልያዎቹ በፈርኦኖቹ ላይ የተቀዳጁት ድል ለዚህ በቂ ነው ማለት ባይቻልም የመንግሥትን አንጀት ለማራራት አያንስም። ስለዚህም ይህን የተጀመረ መነቃቃት አስቀጥሎ ዋልያዎቹን በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ዳግም ለመመልከት ሌላው ቢቀር አንድ ስታዲየም እንኳን ቢሆን ርብርብ ተደርጎበት የመጨረሻዎቹን የማጣሪያ ጨዋታዎች ለማድረግ ዋልያዎቹ ከስደት ቢድኑ መልካም ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014