አዲስ አበባ፡- በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የተነሳው የወሰን ጥያቄ ውጥረት ከአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ይልቅ በውይይት መፈታት እንዳለበት የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ አስታወቀ። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ኣብርሃ ደስታ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በክልሎቹ መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ እልባት ማግኘት የሚችለው የሁለቱ ክልል መንግሥታት ታርቀው፣ ተመካክረውና ተቀራርበው መወያየት ሲችሉ ነው።
ሁለቱ ሳይስማሙ ኮሚሽን ቢቋቋም ለውጥ አያመጣም ያሉት ሊቀመንበሩ የትግራይ ክልል መንግሥትም ኮሚሽኑን ባልተቀበለበት ሁኔታ ሥራ ቢጀመር ግጭት ከመፍጠር ውጭ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይሆን ተናግረዋል።በዚህም ዓረና የሚፈልገው ሠላም በሚያሰፍን መልኩ ችግሮች እንዲፈቱ ነው ብለዋል። ዓረና የችግሩን ምንጭ ለማጥራት በራያና በወልቃይት አካባቢዎች በአካል በመገኘት ነዋሪውን ማነጋገሩንም አቶ ኣብርሃ ገልፀዋል።
በውይይታቸውም ዋናው ችግር አካባቢዎቹ በህወሓት ለመተዳደር ያለመፈለግ እንደሆነ ተናግረዋል።በአማራ ክልል አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች የተሻለ አስተዳደርና ፍትሕ እንዲሁም አገልግሎት ያገኛሉ።በትግራይ ክልል ስር ያሉ ወረዳዎች ግን ብዙ በደል ይደርስባቸዋል።ፍትሕ ፈልገው ወደ ተለያዩ ተቋማት ሲያቀኑ ተገቢው አገልግሎት አይሰጣቸውም ሲሉ ተናግረዋል።
ችግሩ እየተነሳ ያለው የራያና የወልቃት ሕዝብ የአማራ ማንነት ስላለውና ትግራዋይነቱን የመካድና የማንነት ጥያቄን ያነገበ ሳይሆን የህወሓትን አስተዳደር ያለመቀበል መሆኑን ማወቅ ይገባል ብለዋል።መፍትሔው መሆን ያለበትም ሕዝብ መጀመሪያ ፍትሕ እንዲያገኝ መታገል እንጂ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል እንዲቀየር በማድረግ እንዳልሆነ ሊቀመንበሩ አመላክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሁለቱም ክልል መንግሥታት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ሲያቅታቸው ወደ ግጭት መግባትና የተለያዩ ጠብ አጫሪ የሆኑ መግለጫዎችን እያወጡ ችግር እየፈጠሩ እንደሆነም ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ህወሓት የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት የትግራይ ሕዝብ ከፌዴራል መንግሥት ጋር እንደተጣላ፣ የፌዴራል መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ለመጨቆን፣ለመደብደብና ለማጥፋት ዕቅድ እንዳለው በማስመሰል ማቅረቡም ትክክል አለመሆኑን አቶ ኣብረሃ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
በፍዮሪ ተወልደ