በአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ዴሞክራሲያዊ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፤ የአገር ውስጥ ሰላምና ፀጥታ ሥራው ግን በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተጓዘ ምሑራን ይናገራሉ። ችግሩ ወደባሰ አደጋ እንዳይሸጋገርም ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድና የሕግ ማስከበር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባም መክረዋል። አቶ መላኩ ሙሉዓለም፣ በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት፤ የለውጥ ጅምሩ ብዙ ለውጦችን አምጥቷል።
ሆኖም አንደኛ፣ ለውጡን እንደ ስጋት ከማየት ከለውጡ ተቃዋሚዎች በሚፈጠር ጥቅምን የማጣት ስጋት፤ ሁለተኛም፣ ከለውጡ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ከመሻት ከለውጡ ደጋፊዎች የላቀ ተጠቃሚነትን ለማሳካት ሲባል የመንግሥትን ስልጣን ከመግፋት ሰላምና ፀጥታን እስከማደፍረስ በሚሄድ ሽኩቻ በሰላምና ፀጥታው ላይ ችግሮች ታይተዋል። አቶ ዳደ ደስታ፣ የጋዜጠኝነትና ፐብሊክ ፖሊሲ ባለሙያ ሲሆኑ፤ በአፍሪካ ታላላቅ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ውይይትና ክርክር የሚደረግበት ዲስኮርስ የተሰኘ ጆርናልም ኤዲተር ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ሰላምና ፀጥታ ከሜዳ ሳይሆን ተሰርቶ የሚገኝ እንደመሆኑ፤ የሰላምና ፀጥታ መዋቅሩና ይሄን እንዲሰሩ የተደራጁ አካላት፣ የህብረተሰቡ አስተሳሰብና ባህል እንዲሁም ስሜት ምን ይመስላል የሚሉ ጉዳዮች ለዚህ ወሳኝ ናቸው። በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውና በየቀኑ የሚሰሙ ነገሮችም የዚህ መገለጫ እንደመሆናቸውም፤ አሁን ያለው የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ የሚያሳስብ ነው። ምክንያቱም ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በፀጥታው ላይ አጥልቶ የነበረውን ችግር ለመፍታት የአመራር ለውጦች ከተደረጉ በኋላም በተለያየ መንገድ (በአንዳንድ ቦታም በከፋና በሰፋ መልኩ) መቀጠሉ ትልቅ ችግር ሆኗል። ሆኖም ችግሩ መነሻም መፍትሄም አለው።
አንዳንዶቹ በፖለቲካ መፍትሄ፤ አንዳንዶቹም በሕግ የሚፈቱ ናቸው። ይሄን ለማድረግ እንደ መንግሥትና አገር ያለው ዝግጁነት የደከመ መሆኑም፤ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ተፈጥሯዊና ሌሎች አስገዳጅ የሆኑ ነገሮች በሌሉበት የብዙ ህዝብ መፈናቀል (ያውም በሚሊዮኖች የሚቆጠር) በኢትዮጵያ ተከስቷል፣ መፍትሄ ሳያገኝም ዘለግ ያለ ጊዜ ወስዷል። አቶ መላኩ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የሰላም እጦቱ የህዝብ መፈናቀል እንዲያሻቅብ አድርጓል። የሰዎችን አመለካከትም እየቀየረ ለውጡን ሊቀለብስ፣ አገርንም ሊያፈርስ የሚችል ስጋት ተደቅኗል።
ህዝቡም ሰላምና ደህንነት እንዳይሰማው ሆኗል። ችግሩን ከመፍታት አንጻርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሆደ ሰፊነት በንግግራቸው ማስተማር ላይ አተኩረው እየሰሩ ነው። ሆኖም በማስተማር ለመቀየር የሚያደርጉት ጥረት ረጅም ጊዜ የሚወስድ እንደመሆኑ ከማስተማር ጎን ለጎን አስፈላጊ በሚሆንበት ቦታ ላይ መንግሥት የግድ የህግ የበላይነትን ወደ ማስከበር መሄድ ይኖርበታል። ጊዜ በሄደ ቁጥር ህዝብ እየተጎዳ ስለሚሄድና ህዝብም መንግሥት እርምጃ እንዲወስድለት ስለሚጠብቅ ሆደ ሰፊነቱ ገደብ ሊኖረውና ሕግ የማስከበር እርምጃ ሊወሰድ ይገባል የሚሉት አቶ መላኩ፤ ከዚህ ባለፈም በተለያየ ምክንያት ህዝቡ ውስጥ ብዥታን የሚፈጥሩና የሚያጨቃጭቁ ነገሮች ሲመጡ ህዝቡን ለግጭት እንዳይዳርጉ ወጥቶ መረጃ መስጠትም ይጠበቃል ይላሉ።
ፓርላማውም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን እየጠራ በዚህን ዓይነት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ማድረግ፤ ሕገ መንግሥታዊ አሰራሮች ስር እንዲሰዱ ከማድረግ አኳያም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማገዝ አለበት። የፍትህ አካላቱም ሕግን የማስከበር ሥራቸውን ማከናወን ይኖርባቸዋል። አቶ ዳደ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የችግሩ ጎልቶ መውጣት ለአገር ውስጥ ሰላምና ፀጥታ ትኩረት ስላልተሰጠው አይደለም። ይልቁንም አንደኛ፣ ለመፍትሄው የሚሰራው ሥራ በተገቢው ጉዳይ ላይ ያለማተኩር፤ ሁለተኛም፣ ለመፍትሄ ተብሎ የተሰሩ ሥራዎች ለችግሩ ተገቢ መፍትሄ ያለማስገኘታቸው የፈጠሩት ነው።
ምክንያቱም ለውጡን ተከትሎ የፖለቲካም ሆነ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰዱ እርምጃዎች በአገሪቱ ያለውን ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን ቢሆንም፤ እርምጃው ግን ተገቢውን ውጤት በሚፈለገው ደረጃ ማምጣት አልቻለም። ይህ ደግሞ ሁለት ነገሮችን በሚዛናቸው ያለማስኬድ ውጤት ሲሆን፤ የዴሞክራሲና ፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት በተጓዳኝ፣ የተገኘውን ሰፊ ምህዳር በመጠቀም ሂደት ለሚታዩ ግድፈቶች የህግ ማስከበር ሥራዎች አለመከናወናቸው ነው። ከዚህ ባለፈም የሕግ አስከባሪው መዋቅር ከላይ ያለ ቢመስልም ከታች ግን የተዳከመና በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዳ መሆኑ ለችግሩ መጉላት ተደማሪ ምክንያት እንደሆነ አቶ ዳደ ይገልጻሉ።
ለጥፋቶች ባለቤት ከመስጠት ይልቅ በጅምላ መፈረጅ፤ ለውጡን ተከትሎ ሙገሳውንም ሆነ ወቀሳውን ከድርጅት ይልቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ መስጠት፤ እንዲሁም የታችኛው የመንግሥት መዋቅር ያለ መስሎ የፈረሰ መሆን ለችግሩ መባባስ የድርሻቸውን አበርክተዋልም ይላሉ። እንደ አቶ መላኩ ገለጻ ደግሞ፤ ለውጡ ከመምጣቱ በፊት ብዙ አደጋ ነበር። ሕዝቡ ጭንቀት ውስጥ፤ አገሪቱም ብዙ ችግር ውስጥ ነበረች። ለውጡ ደግሞ ትልቅ ተስፋ ይዞ ነው የመጣው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሥራቸውን ሲጀምሩ በየክልሉ እየዞሩ ህዝቡን በማነጋገር ያለበትን ችግር ተረድተዋል።
በዚህም በርከት ያሉ ችግሮችን ለመረዳት ሞክረዋል። በለውጡም በርካታ የለውጥ ቱሩፋቶች በመምጣታቸውም ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ተገኝቷል። ሆኖም ችግሮች ተቀያያሪ እንደመሆናቸው አሁንም ተመልሰው ችግሮች እያቆጠቆጡ፤ አፍጥጠውም እየወጡ ናቸው። ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀመሩት መልክ ዳግም ማነጋገር ወይም አጋዥ የሚሆን ጥናት እንዲከናወን ማድረግ ይጠበቅ ባቸዋል። ካልሆነ አሁንም ተመልሶ አስቸጋሪ ነገር ይፈጠራል። ተስፋው ወደ ስጋት፤ ስጋቱም ወደ ጥፋት ይለወጣል።
እንደ አቶ መላኩ ገለፃ ይህ እንዳይሆን በገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መካከል፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ በገዢውና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ልዩነትን አጥብቦ ለሰላምና ደህንነት በጋራ መስራት ይገባል። ከሰንደቅ ዓላማና ከሕገ መንግስቱ መሰረታዊ ድንጋጌዎች ጀምሮም የጋራ መግባባት የማይታይባቸው ጉዳዮችን በመለየት እልባት መስጠት ያስፈልጋል።
ሕጎችም ከወቅቱ ጋር እየተከለሱ መሄድና ችግር የሚፈጥሩትን ፈትሾ ማረም፤ የሃይማኖት አባቶችም ወደ ህዝቡ ቀርበው ማስተማር፤ በሰላም ዙሪያ የሚሰሩ አካላትን ማበረታታት፤ በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያለውን ክፍተትም መሙላት፤ የፌዴራል መንግሥቱም ሕገ መንግሥታዊ ስልጣኑን በመጠቀም ለሰላም መስራት ይጠበቅበታል። አቶ ዳደ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ችግሩ ቶሎ መፍትሄ ካልተሰጠውና እንዳለ ከቀጠለ እየባሰ ይሄዳል። የአገሪቱንም ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። እናም አስቸኳይ እርምት ያስፈልገዋል።
ለዚህ ደግሞ፣ ኢህአዴግ አንድ መሆን ባቃተው ቁጥር ከትግልም ሆነ ከስደት የተመለሱ ፓርቲዎች ላይም መከፋፈልን ስለሚፈጥር በኢህአዴግ ደረጃ ወደ አንድ አቅጣጫ መምጣት አለባቸው። ኢትዮጵያ የምትወለድም፣ ያረጀችም ሆና የምትታይበትን የእስካሁን የለውጥ ጉዞ በሚቀይር መልኩ ለውጡ የነበረውን ወደ ዜሮ ሳይመልስ የአገርና ህዝብን ቀጣይነት ሳይረብሽ መካሄድ ይኖርበታል። ተቋማትንም ከተልዕኳቸው እንጂ ከፖለቲካ ፍላጎት አንጻር አለመመልከት፤ እንደ አዲስ አበባ አይነት ያልተገቡ ውዝግቦችን በተመለከተም የፖለቲከኞችና የሚዲያዎች ሃቲት መልክ ሊበጅለት ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011
ወንድወሰን ሽመልስ