በ2023 የኮትዲቯር አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታቸውን በገለልተኛ ሜዳ ማላዊ ላይ ከግብጽ አቻቸው ጋር ያደረጉት ዋልያዎቹ ታሪክ የማይዘነጋው ታላቅ ድል አስመዝግበዋል። ባለፉት አስራ አንድ አጋጣሚዎች ፈርኦኖቹን ገጥመው ሽንፈት እንጂ ድልን ቀምሰው የማያውቁት ዋልያዎቹ ዛሬ የፈርኦኖቹን ዘውድ ደምስሰው ታሪክ የማይዘነጋው ታላቅ ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ አበርክተዋል።
ዋልያዎቹ በፍጹም የጨዋታ ብልጫ ፈርኦኖቹን ከዙፋናቸው ለማውረድ ሙሉውን የጨዋታ ጊዜ መጠበቅ አላስፈለጋቸውም። በመጀመሪያው አርባ አምስት በዳዋ ሆጤሳና በሽመልስ በቀለ አማካኝነት ባስቆጠሩት ግቦች ከጨዋታው የሚፈልጉትን ውጤት ይዘው መውጣት ችለዋል። በፍጹም የራስ መተማመንና የአሸናፊነት መንፈስ ጨዋታውን ተቆጣጥረው የጨረሱት የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ልጆች ፈርኦኖቹን መግቢያ መውጫ አሳጥተው የኢትዮጵያን ሕዝብ ምሽት ፍሰሃ ሞልተዋል። ዋልያዎቹ ለውድድር የማይቀርበውን የኢትዮጵያና የግብጽ እግር ኳስ ደረጃን ግምት ውስጥ የከተተ ታሪካዊ ድል አስመዝግበዋል።
ይህ እንደ ማንኛውም ጨዋታ ድል ብቻ አይደለም። ለሁለቱም አገራት ትርጉሙ ብዙ ነው። ኢትዮጵያና ግብጽ የአፍሪካ እግር ኳስ ጠንሳሾች ናቸው። ይህን ታሪክ ይጋሩት እንጂ ዛሬ ላይ የሁለቱ አገራት የእግር ኳስ ደረጃ ልዩነቱ ሰፊ ነው። የደረጃ ልዩነቱ የቱንም ያህል ቢሰፋ ግን በተለያዩ ምክንያቶች የተቀናቃኝነት ስሜታቸው ለአፍታም ደብዝዞ አያውቅም። ሁለቱ አገራት የአለም
ብሎም የአፍሪካ ጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫ ከመሆናቸው ባሻገር በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የገጠሙት ጦርነትና የአባይ ወንዝ ትስስር በእግር ኳሱ መንደር ሲገናኙ ፍልሚያቸውን ይበልጥ ያጦዘዋል። በተለይም ሁለቱ አገራት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ውሀ ሙሌት ጋር በተያያዘ ከቅርብ አመታት ወዲህ የገቡበት ውዝግብ ባላንጣነታቸውን አደባባይ እንዲወጣ ባደረገበት በዚህ ወቅት ድሉ ለኢትዮጵያውያን ያለው ትርጉም ከእግር ኳስም የበለጠ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3 /2014