የመጋቢት 2010 ዓ.ም ትውስታ
በኢትዮጵያ በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከስተው በነበሩ አለመረጋጋቶችና ሁከቶች በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራዎች ደርሰዋል።መንግሥትም ችግሩን ለመግታት ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።ነገር ግን ሰላምን ማምጣት አዳጋች ነበር። ይህንን ከግንዛቤ በማስገባትም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጥልቅ ግምገማ አድርጎ ትላልቅ ውሳኔዎችን አስተላልፏል። በመጨረሻም የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኃይለማ ርያም ደሳለኝ የመፍትሄው አካል ለመሆን ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸውና ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በገዛ ፈቃዳቸውና ለቀዋል።
ይህንን መነሻ በማድረግም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ አስቸኳይ ጉባኤ በማካሄድ አዳዲስ ለውጦችን አካሂዷል። በዚህም መሰረት ኮሚቴው መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ዶክተር ዐብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር በማድረግ መረጠ። ዶክተር ዐብይ አህመድም መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። በእለቱም ለምክር ቤቱ ያደረጉት ንግግር የብዙዎችን ቀልብ የሳበ እንደነበር በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።በእለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እነዚህን አንኳር ጉዳዮች አንስተው ነበር።
• ትናንት፣ አባቶቻችን በመተማ፣ በአድዋ፣ በማይጨውና በካራማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆዩዋት አገር አለችን።እኛ ዕድለኞች ነን።ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንን እናውቃለን።በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ህዝብ ነን። ህብረታችን ለዓለም ምሳሌ መሆን ይችላል።ጠላቶቻችንን አንበርክኳል። ሉዓላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይ ለሌሎች ህዝቦችም የነጻነት ትግል አርአያ ሆኗል። አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር ፣ ስናልፍ ሀገር እንሆናለን።
የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ።ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን።ኢትዮጵያ የሁላችን አገር ፤የሁላችን ቤት ናት።
• በመጀመሪያ ሥራችን ልናደርገው የሚገባንና ትግላችን ማተኮር ያለበት ራሳችን ላይ ነው። አመለካከታችንን ከጥላቻ፣ ከቂም በቀል ስሜትና ከዘረኝነት ማፅዳት ይገባናል። በብሄር፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በሃይማኖት ወዘተ ያሉንን ልዩነቶች እንደ በረከትነታቸው በፍቅር በማስተናገድ ከልዩነቶቹ የሚነሳ አለመግባባት ቢኖር እንኳ ከፍትህ እንጂ ከበደል ጋር ባለመተባበር ሞራላዊ ዕይታዎቻችንን ልናስተካክል ይገባናል።
• ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነፅር እንደተቃዋሚ ሳይሆን እንደተፎካካሪ፣ እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሃሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው። የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና ሀገራዊ ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገውን ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
• አገራችን፣ ጥሩ የሚባል ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እያስመዘገበች እንደሆነ ቢታወቅም ዕድገቱ በቅርፅና በይዘት ተለዋዋጭ የሆነውን የወጣቱን ትውልድ ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ የሚያረካ አልነበረም። ይህም፣ ሕዝባችንን ለብሶት እንደ ዳረገው እንገነዘባለን። ያለወጣቶች ተሳ ትፎ እና ተጠቃሚነት አገር የትም ልትደርስ እንደማትችልም እንረዳለን። ኢትዮጵያ ለወጣ ቶቿ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ፣ ተስፋ የምታስቆርጥ አገር እንዳትሆን የምንችለውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ።
• እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሥራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል። ኢትዮጵያዊውን ከኢ ትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም።
• ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ቃለ ትውስታ… መሀላ ከፈፀሙ በኋላ መጋቢት 29 ቀን 2010 ዓ.ም በሶማሊያ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የስራ ጉብ ኝት አድርገዋል። በጉብኝታቸውም ወቅት እንዲህ ብለው ነበር።
• የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብ በጫንቃው የተጫነበትን አስከፊ የድህነት ቀንበር ከተቀሩት ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በአብሮነትና በአጋርነት መሰለፍ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ኢትዮጵያዊነቱን በልቡ ይዞ በየጎራው በመሰለፍ ወራሪዎችን የተፋለመበት ገድል በሁሉም የአገራችን ህዝቦች ልብ ውስጥ የታተመ አኩሪ ገድል ነው።
• የኢትዮጵያ ሱማሌ ህዝብ ለኢትዮጵያ ማንነት የዳር ተደርጎ ሊታይ አይችልም ለኢትዮጵያ ማንነት ዳርና መሀል ሳይኖር ሁሉም የኢትዮጵያ አስኳል ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 16/2011