ግሎባል ዊትነስ የተባለው ድርጅት በናይጄሪያ እየተካሄደ ነው የሚለውን የተጭበረበረ ስምምነት እግር በእግር እየተከታተለ ዘመቻ የሚያካሂድ ድርጅት ሲሆን፤ በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ ኤኒ እና ሼል የተባሉ ኩባንያዎች ከናይጄሪያ ጋር ባደረጉት የተጭበረበረ የነዳጅ ስምምነት ምክንያት ሀገሪቷ 6 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን አስታውቋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ኦ ፒ ኤል-245 የተባለው እ አ አ በ2011 የተደረገው የነዳጅ ስምምነት ናይጄሪያ ለትምህርትና ለጤና ማዋል የሚስችላትን የአንድ ዓመት በጀቷን እጥፍ እንድታጣ አድርጓታል፡፡ በዚህም ግሎባል ዊትነስ ኤኒ እና ሼል የተባሉት ነዳጅ ዘይት አምራች ኩባንያዎች በስምምነቱ ወቅት ለናይጄሪያ በሰጡት መደለያ ወይም ጉቦ የተነሳ በኢጣሊያ ሚላን በሚገኝ ፍርድ ቤት ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱን አመልክቷል፡፡
የኢጣሊያን ኤኒ እና የእንግሊዝና ሆላንድ ንብረት የሆነው ሼል ኩባንያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ግን ክሱን ጉዳይ አስተባብለዋል፡፡ ጉዳዩን የሚያቀናብሩት የእንግሊዙ የደህንነት ድርጅት ኤም 16 የቀድሞ አባላት፣ ኤፍ ቢ አይ፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የሁለቱ የነዳጅ ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚዎች ናቸው ብለዋል።
የቀድሞው የናይጄሪያ የነዳጅ ዘይት ሚኒስትር ዳኒ ኤቴት በፈረንሳይ ፍርድቤት በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በሙስና ያጋበሱትን በውጭ ሀገር ባንኮች በማስቀመጣቸውና እጅግ በጣም ውድና የተከለከሉ ፈጣን ጀልባዎችን በመግዛታቸው እንዲሁም እስከ 5 ቶን የሚገመት ብር እንዳላቸው በመረጋገጡ ተከሰው ተፈርዶባቸው እንደነበር ዘገባው ይጠቁማል፡፡
ግሎባል ዊትነስ ለዓመታት ባደረገው ጥናት ሼል እና ኤኒ የተባሉት የነዳጅ ዘይት አሳሽ ካምፓኒዎች በኦፒ ኤል 245 ስምምነት መሰረት በኒጀር ጠረፋማ እና ዳርቻዎች ላይ የነዳጅ ዘይት በመፈለግ ሥራ ላይ ያሉ እንደነበሩ አረጋግጧል፡፡
ከካምፓኒዎቹ ጋር የተደረገው ውል ማሻሻያ የተደረገበትና የጥቅም ተጋሪነትን በሚያረጋግጥ መንገድ የእከክልኝ ልከክልህ ሥምምነት የታየበት መሆኑን ግሎባል ዊትነስ ትንታኔውን አስቀምጧል በዚህም እአአ ከ2011በፊት ከነበረው አሰራር አንጻር እነዚህ ፐሮጀክቶች ውል ፈጽመው በነዳጅ ዘይት ቁፋሮ ከተሰማሩ በኋላ ናይጄሪያ 5.86 ቢሊዮን ዶላር አጥታለች፡፡
የኪሳራውን ግምታዊ አሀዝ በገንዘብ ለመተመን መነሻ የሆነውም የአንድ በርሜል ነዳጅ ዘይት ዋጋ 70 ዶላር በማብዛት ነው፡፡ ጥናቱና ትንተናው የተከናወነውም የግሎባል ዊትነስ አጋር በሆነው የተፈጥሮ ሀብት እድገት አማካሪ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ነው፡፡ ኤኒ የተባለው ኩባንያ ሂሳቡ የተሰራበትን መንገድ የተቸ ሲሆን፤ ናይጄሪያ ስምምነቱን የመከለስ መብት እንዲሁም ከነዳጅ ገቢው 50 በመቶ መጠየቋን ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ተገልጿል።
እንደ ግሎባል ዊትነስ ተሟጋቾች አቋም ስምምነቱ ተገቢነት ያለው ባለመሆኑ መሰረዝ የሚገባው ነው፡፡ አቫ ሊ የተባሉት የቡድኑ አባል ለቢቢሲ ቢዝነስ ሪፖርት እንዳስረዱት ‹‹ በጥናታችን ውጤት እኛ ያረጋገጥነው የሼል ካምፓኒ ስምምነቱን ለምዝበራ ምቹ በማድረግ ናይጄሪያ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አሳጥቷል፡፡ ይህ ያለ አግባብ የተመዘበረው የሀገሪቱ ገንዘብ 6 ሚሊዮን የናይጄሪያ መምህራንን ለማሰልጠን እንደሚያስችል ተገምቷል፡፡ ሕዝቦቿ በድህነት ወለል ላይ ለሚገኙ እንዲህ ላለች ሀገር ይህ አይነቱ ዓይን ያወጣ ምዝበራ ችላ ተብሎ የሚታለፍ መሆን የለበትም፡፡ ምንም እንኳን ናይጄሪያ በነዳጅ ዘይትና ጋዝ የበለጸገችና ኢኮኖሚዋ አድጓል ከሚባሉ የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ ብትሆንም ዛሬም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆች ይገኙባታል፡፡››
ለምንድነው ኤኒ እና ሼል ኦፒ ኤል – 245 ስምምነትን መሰረት አድርገው መስፋፋት የፈለጉት ብለን ብንጠይቅ መልሱ አንድና አንድ ነው፡፡ እንዳልነው ሕገ- ወጥ መንገድን በመከተል ኃላፊነት ከማይሰማቸው አመራሮች ጋር በመመሳጠር ያለ አግባብ ለመመዝበር ነው፡፡ የሙስናውም ሂደት በቀላሉ ሊደረስበት የሚችል አይደለም፡፡
የሚላኑ ፍርድ ቤት የቀድሞው የናይጄሪያ የነዳጅ ዘይት ሚኒስትር ዳን ኢቴት ከተለያየ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር በጥቅም የተሳሰረ ግንኙነት እንዳላቸውና በሙስና ምክንያትም ተከሰው እንደነበር ያትታል፡፡ በዚህም የቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ጉድ ላክ ጆናታንን የጥቅም ተጋሪያቸው በማድረግ የክሱ ሂደት እንዲረግብ አድርገዋል፡፡
ሁለቱ የነዳጅ ኩባንያዎች 1 ነጥብ 1 ቢልዮን ዶላር ለናይጄሪያ መንግሥት መሥጠታቸውን በኢሜል ከተጻጻፉት መረጃ ማወቅ ተችሏል፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተው ቀደም ሲል ከሼል ኩባንያ ጋር የተደረገው ውል እርምት የተደረገበት በሚመስል መልክ ተቀምጧል፡፡ ይህ አሳፋሪና ተአማኒነት የጎደለው ስምምነት በወቅቱ በናይጄሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድም መነጋገሪያ እንደ ነበር የግሎባል ዊትነሱ የሥራ ባልደረባ ኦቫ ሊ ያስረዳሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የየኢጣሊያን ኤኒ እና የእንግሊዝና ሆላንድ ንብረት የሆነው ሼል ኩባንያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምንም አይነት ሥህተት አልተፈጠረም ይላሉ፡፡ እንደነዚህ አካላት እምነት ገንዘቡ የተከፈለው በቀጥታ የናይጄሪያን ጥቅም ለማስጠበቅ የህግ አግባብን በተከተለ መንገድ ነው፡፡
ቢቢሲ በዝነስ ሪፖርት ጉዳዩን አስመልክቶ ሼል ኩባንያን ሊያነጋግር ቢሞክርም የሚላን ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ጣልቃ ገበቶ መናገር እደማይፈልግ አስረድቷል፡፡ በተያያዘም ሼል ውሉን ያደሰው በሕጋዊ መንገድ ነው ፡፡ የሚላን ፍርድ ቤትም የሼል ኩባንያም ሆነ የቀድሞ የሥራ ኃላፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርግበት አግባብ እንደሌለ እናምናለን በማለት ዝርዝር ነገሮችን ከማውራት ተቆጥበዋል፡፡
የኤኒ ኩባንያ በበኩሉ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ በግሎባል ዊትነስ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል፡፡ እንደውም ቡድኑ ሥም የማጥፋት ዘመቻ እንዳደረገበት በመግለጽ የንግድ ውሉን በመኮነን የቀረበውን ክስ መሰረተቢስ ሲል ይተቻል፡፡ የኢጣሊያ የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ኩባንያም እንዲሁም ይህ ጉዳይ በሚላን ፍርድ ቤት እየታየ በመሆኑ ዝርዝር አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡ መርማሪው ግብረሃይልና አጋሮቹ እንዳስቀመጡት ጉዳዩ ውሳኔ እንዲያገኝ ከአንድም ሁለት ጊዜ ለሚላን ፍርድ ቤት አቤቱታወን አቅርቧል፡፡ ተሟጋቾቹ እንደሚስማሙበት ይህ ሁኔታ ወሰን ተሸጋሪና ትልቅ ጉዳይ እንደመሆኑ የሚላን ፍርድ ቤት የሚያስተላልፈውን ውሳኔ በነዳጅ ዘይትና ጋዝ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘንድ ልክ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ሊያናውጥ የሚችል ስሜትን እንደሚያስተጋባ ይታመናል፡፡
ታዘቢዎች እንደሚሉት አሁን ላይ ያሉት የናይጄሪያ አመራሮች ቀደም ሲል የነበሩትን ስምምነቶች በውል እያጤኗቸው ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ብዙ ውሎችን ሊሰርዙ እንደሚችሉም ይገመታል፡፡ የኢጣሊያ መንግሥት ህግን የማስከበር ክፍተት እንዳለበት የሚተቹም አልጠፉም፡፡ እንደውም የሀገሪቱ ዜጋ የሆኑት አንቶኒዮ ትሪካሪኮ ኢጣሊያ ሰደተኞችን አስመልክቶ የተስማማችውን ዓለም አቀፍ ህግ በገባችው ቃል መሰረት እየተገበረችው እንዳልሆነ ይተቻሉ፡፡ ኢጣሊያ የናይጄሪያ ስደተኞች ወደ ሀገሯ እንዲገቡ ከመፍቀድ ይልቅ በሀገራቸው ሆነው እርዳታ እንዲደረግላቸው ትፈልጋለች፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ትልቅ ስም ያለውና የሀገሪቱ አንድ አካል የሆነው ኩባንያዋ ከናይጄሪያውያኑ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ሲመዘብር ጉዳዩን ችላ ማለት ትፈልጋለች በሚል ትብጠለጠላለች፡፡
የሆነው ሆኖ የሚላኑ ውሳኔ የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪዎች በተለይም ሙስና የተንሰራፋባቸው ነዳጅ አምራች አገሮች የንግድ አሰራራቸውን በመለወጥ እንዴት መመራት እንዳለባቸው ጫና ሊያሳድርባቸው ይገባል፡፡ በስምምነቶችና በክፍያ ላይም ግልጽነት ያለውን አሠራር በመከተል ሀገራትን ከመጭበርበር መታደግ ያስፈልጋል፡፡