የቱሪዝም ዘርፉን የሰው ኃይል ፍላጎት ለመመለስ ከሚከናወኑ ተግባሮች አንዱ የዘርፉን ባለሙያ ማፍራት ነው። ዛሬ የአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የግል ማሰልጠኛ ተቋማት የዘርፉን ባለሙያዎች በማሰልጠን ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜያት ይህን ሃላፊነት ወስዶ ሲሰራ የቆየው የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ነው። ተቋሙ አሁንም በዚሁ ላይ እየሰራ ይገኛል።
ከኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ተቋሙ የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል (ሆ.ቴ.ሥ.ማ.ማ.) በሚል ነበር የሚታወቀው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከእስራኤል መንግስት ባገኘው ድጋፍ የተቋቋመው በ1961 ዓ.ም ነበር። የተቋቋመበትም ዋና አላማ በወቅቱ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ያስፈልግ የነበረውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ማሟላት ነው።
ይህ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ስልጠና በመስጠት ፈር ቀዳጅ የሆነ ተቋም ከራስ ሆቴል ጥቂት ክፍሎችን በመከራየት ስራውን የጀመረ ሲሆን፣ ላለፉት 47 ዓመታት ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ ለአገራችን የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዕድገት የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከተና እያበረከተ ያለ አንጋፋ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከ2008 ጀምሮ ደግሞ ለአሥር ዓመታት እስከ 2017 ዓ.ም የጉዞ አቅጣጫውን የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀትም ሲሰራ ቆይቷል። በፍኖተ ካርታው ላይ የተቀመጡትን ስትራቴጂዎች በመጠቀም ማዕከሉ በቀጣይ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ሙያተኞችን በማሰልጠን ሃያ ሶስት በመቶ ብቻ የነበረውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ክፍተትን ለመሙላት ይሰራል። በዚህ አግባብ በአስር ዓመታት ያለውን ክፍተት የሰለጠነ የሰው ኃይል ከሰማንያ በመቶ በላይ ከፍ ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተሳሰር ስራዎችን በቅንጅት መስራትና ኢንዱስትሪው ላይ ያሉትን ሙያተኞች የማብቃት፤ ጥናትና ምርምር ማካሄድና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራትን ያከናውናል።
ላለፉት ስምንት ዓመታትም “የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንትን” በተለያዩ ንቅናቄዎች ሲያከብር ቆይቷል። ዘንድሮም ለዘጠነኛ ጊዜ “ቱሪዝም ለአብሮነት በሚል” መሪ ሃሳብ ሳምንቱን ልዩ ልዩ ዘርፉን የሚያጎለብቱ ዝግጅቶችን በማከናወን አክብሯል።
ከኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ባለፉት ቀናት ሳምንቱን በማስመልከት ዘርፉን የሚወክሉ ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ተካሂደዋል። ከእነዚህ ውስጥ የማሰልጠኛው የመጨረሻ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎች በሆቴል ዘርፍ፣ በአስጎብኚነትና በሌሎች መስኮች የስራ እድል የሚያገኙበትና ቀጣሪዎች በተመሳሳይ ብቁ የሰው ኃይል መመልመል የሚችሉበት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህም ስራና ሰራተኛን በማገናኘት ትስስር የሚፈጠርበትን ልዩ እድል በቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት ዝግጅቶች ላይ መፍጠር ተችሏል። በዝግጅቱም ከ40 በላይ ሆቴሎች በስፍራው በመገኘት ባለሙያዎችን ለመቅጠር መረጃዎችን ተሰብስበዋል።
በቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንቱ ሁለተኛ ቀን መርሃ ግብር ሲምፖዚየም ተካሂዷል። በዚህም ሶስት ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርሷል።
በመጀመሪያው ፅሁፍ ላይ ቱሪዝም ለአብሮነት ያለውን ፋይዳ የሚዳስስ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን፣ ዘርፉ ሰላምን አንድነትንና መሰል የጋራ ማንነቶችን የሚያጠናክር አቅም ያለው ከመሆኑ አንፃር በዚያ አግባብ መቃኘት እንደሚኖርበት በዘርፉ ከፍተኛ ኤክስፐርት በሆኑት አቶ ይስፋልኝ ሃብቴ ጥናታዊ ፅሁፉ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። አቶ ይስፋልኝ ባቀረቡት ጽሑፍ ቱሪዝም ከሰላም ጋር፣ ቱሪዝም ከአብሮነት ጋር ያለውን የተሳሰረ ግንኙነት ያነሱ ሲሆን አብሮነትን ለማሳደግ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
ሁለተኛውን ፅሁፍ ያቀረቡት በአማራ ክልል ምእራብ ጎጃም ዞን የጮቄ ተራራን ተከትሎ ደጋ ዳሞት በሚባል ቦታ ላይ የሚገኘው የሙሉ ኢኮ ሎጅ ባለቤት ናቸው። እሳቸውም የዚህን የማህበረሰብ ሎጅ መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብና የሚገኝበትን ደረጃ እንዲሁም ማስመዝገብ የቻለውን ስኬት አስመልክተው ልምዳቸውን በዳሰሳዊ ፅሁፍ አቅርበዋል። ኢኮ ሎጁ በዓይነቱ ለየት ያለ መሆኑን በመግለጽ፣ የእሱን ተሞክሮ ወደሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ማዳረስ የሚቻልበትን ተሞክሮ ጠቁመዋል።
ሌላውና በመጨረሻ የቀረበው ፅሁፍ ቱሪዝምና የመገናኛ ብዙሃን ስላላቸው መሰተጋብር የተመለከተው ፅሁፍ ነው። በባህልና ቱሪዝም የጋዜጠኞች ማህበር ስራ አስፈፃሚ አቶ አስናቀ ብርሃኑ ለውይይት መነሻ እንዲሆን የቀረበው ይህ ጽሁፍ መገናኛ ብዙሃን ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ወሳኝ ድርሻ እንደሚጫወቱ ተመላክቶበታል። በሲምፖዚየሙ ላይ በተደረገ ውይይት ላይ የጋራ ስምምነት ተደርሶበት ትስስሩ መጠናከር እንዳለበት ግንዛቤ ተይዟል።
ጋዜጠኛ አስናቀ ብርሃኑ የሚዲያ ሚና ከቱሪዝም አንፃር ያለውን ፋይዳ ከማንሳታቸውም ባሻገር አገሪቱ ያላትን የቱሪዝም ሃብት በበቂ ከማስተዋወቅ እና ዘርፉ በገጽታ ግንባታ ላይ ያለውን ጉልህ ሚና በመወጣት በኩል ሚዲያው ውስንነት እንዳለበት ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ጥናት ኮሌጅ የምርምርና ስርፀት ተባባሪ ዲን ዶክተር ተስፋዬ ዘለቀ፣ በዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም ትምህርት ክፍል በመምህርነት ያገለግላሉ። እርሳቸው ከሙያና ከሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር ያለውን ተግዳሮትና መልካም ጎን በሰሩት ጥናት ላይ ተመስርተው የ“ፕሮፌሽናሊዝም” ፅንሰ ሃሳብ ላይ በማተኮር በዘርፉና ከሙያው ጋር በቀጥታ በሚገናኙ ባለሙያዎች በኩል የሚነሱ አከራካሪ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ሞክረዋል።
“የተማሩና አስጎብኚና መሰል ለቱሪዝሙ እድገት እርሾ የሆኑ ሙያዎች ላይ እውቀትና እውቅና ያላቸውን ከማሳተፍ ይልቅ በዘመድ ዘርፉ ላይ የሚገቡ ይበዛሉ” የሚል ትችት መኖሩን አንስተዋል። ይህ አሰራር በግሉም ሆነ በመንግስት የቱሪዝም መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚታይ መሆኑን ይናገራሉ።
የቱሪዝምን ፅንሰ ሃሳብ የሚያስጨብጡ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሃብቶች ለማልማትና ከዚያ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል እውቀትን የሚያደረጁ የትምህርት ተቋማት እየበዙና በየደረጃው እየተከፈቱ ሲመጡ ከፍተኛ የሰው ሀብት ፍሰት እንደሚመጣ ይጠቅሳሉ። ይህን ተከትሎ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ ዘርፉ በሙያተኛ የሚታገዝ እንዲሆን ውይይት በየጊዜው ሲካሄድ የሚነሳው “የሙያና ፕሮፌሽናሊዝም” ችግር እየተቀረፈ እንደሚመጣ አስታውቀዋል። ዶክተር ተስፋዬ ይህን ችግር በአንድ ሌሊት መፍታትና ዘርፉን በበቂና በቀልጣፋ ባለሙያ መምራት እንደማይቻልም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ መንገድ በተለያየ የትምህርት መስክ የተመረቁ (የታሪክ፣ የመልክአ ምድር፣ የተፈጥሮ ሳይንስና፣ ባዮሎጂ) ባለሙያዎች በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ያሉት ዶክተር ተስፋዬ፣ እነዚህ ባለሙያዎች በቀጥታ ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር የተገናኘ ትምህርት ባይወስዱም ለዘርፉ በተዘዋዋሪ አስፈላጊ የሙያ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። ስለዚህ በዚህ በኩል ከሙያው ውጭ ናቸው በሚል የሚነሳው ትችት አግባብነት የሌለውና እንዲያውም ለዘርፉ ሁለንተናዊ እድገት አስፈላጊ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በቱሪዝም ሳምንቱ የኤግዚብሽን ዝግጅት በተማሪዎች ቀርቧል፣ ባለድርሻ አካላት ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት፤ ለአቅመ ደካማ አረጋውያን የ3ወር ቀለብ ድጋፍ ያደረጉባቸው የተለያዩ መርሀ ግብሮችም በኢንስቲትዩቱ አማካኝነት ተደርገዋል። በእለተ ማክሰኞ ቀንም በገነት ሆቴል ሲፖዚየም የተካሄደ ሲሆን፣ የምግብ ዝግጅት፣ የቋንቋ እና የአስጎብኝነት የክህሎት ውድድር ተማሪዎችን ባካተተ መልኩ ውድድሮችም ተካሂደዋል። ስፖርትና ቱሪዝም ያላቸውን ትስስር ለማሳየት ባለመ መልኩ የስፖርት ውድድር በአስተዳደር ሰራተኞች እና በመምህራን መካከል እንዲሁም በኢንስቲትዩቱ ተማሪዎች መካከል ተካሂዷል።
ሲፖዚየሙን በንግግር የከፈቱት የሆቴልና ቱሪዝም ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት ቱሪዝም በባህሪው ድንበርና ወሰን የሌለው መሆኑን ጠቅሰው፣ ዘርፉን ከፍ የሚያደርገው አብሮነት በመሆኑ አሁን ዓለማችንም፤ አገራችንም ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ይህን አብሮነትን፣ አንድነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነገር ላይ ማተኮር ወቅቱ ያስገድዳል ብለዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል 33በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ወደ 66 በመቶ ከፍ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በቱሪዝም ሳምንቱ ቀጣሪና ተቀጣሪ የሚገናኝባቸው መድረኮች፣ ዓውደ ርዕዮች፣ የምክክር መድረኮች፣ የሰልጣኞች ውድድር እና ሌሎችም ስነስርዓቶች መካሄዳቸው ስላለው ጉልህ አበርክቶም አንስተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አማካኝነት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች የማዕድ ማጋራት በማከናወን የቀለብ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህ ወቅት መልእክታቸውን ያስተላለፉት የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ “የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በቱሪዝም ዘርፍ የትምህርት ደረጃውን በማሳደግ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልከተው፣ ብቁ ባለሙያ ለማፍራት 15 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሀብት መመደቡንም ጠቅሰዋል። በዚህም መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ጠቅሰዋል።
ቱሪዝም ለአብሮነት በሚል መሪ ቃል ይህ ፕሮግራም መዘጋጀቱ አብሮነትን የሚጠናክርና መጠናከር ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በዘርፉ የተሰማሩ የግል ባለሃብቶች ሰልጣኞች በስልጠና ያገኙት ሙያ ይዘው እጃቸው እንዲፍታታ በማድረግ በኩል የእናንተ ተሳትፎ እጅጉን ያስፈልገናል ብለዋል።
ቱሪዝም በፍኖተ ብልጽግናው ቅድሚያ ከተሰጣቸው አምስት ዘርፎች አንዱ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መፍታት ግድ መሆኑን ተናግረዋል። ከሚያከናውናቸው የለውጥ ስራዎች መካከል የትምህርት ደረጃውን እስከ ደረጃ 8 ከፍ ማድረግ አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
መሰረተ ልማቱን ለማሟላትም 15ሚሊዮን ዶላር ሀብት መድቦ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቀሰው፣ ይህም ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠት ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል። አገርን ለማሳደግ በመንግስት የሚደረጉ ጥረቶች ብቻ በቂ እንዳልሆኑም አስታውቀው፣ የግሉ ዘርፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማገዝ ተቋማት ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ ሲሄዱ በራቸውን ክፍት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2014