በራስ ጥረትና ተነሳሽነት ውጤታማ የሆኑ በርካታ ወጣቶች አሉ። ጫማ ከማሳመርና ትናንሽ ከሚመስል ሥራ ተነስተው ዛሬ ትልቅ በሚባል ደረጃ ላይ የደረሱ፤ በራሳቸው ጥረት ፊደል ገበታን «ሀ» ብለው ጨብጠው ዛሬ ለተሻለ ደረጃ የበቁ ለብዙዎች አርአያ መሆን የሚችሉ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ለተሻለ ደረጃ የደረሱት ከመንግሥት ካዝናና ከወላጆቻቸው ገንዘብ ተሰጥቷቸው፣ ምቹ የሥራ አካባቢ ተፈጥሮላቸው፣ አማካሪና አሠልጣኝ ተመድቦላቸው አይደለም።
በራሳቸው ጥረት ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ነው። ዛሬን ሳይሆን ነገን አስበው፤ ሳይሰለቹ፣ ሳይታክቱና ሥራን ሳያማርጡ ተግተው በመሥራታቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ተደራጁ ተብለው፣ ብድር ተመቻችቶላቸው፣ ሌሎች ድጋፎች አግኝተው ጭምር ውጤት ያላሳዩ ወጣቶችን ማንሳት ይቻላል።
ሁልጊዜም ጥገኝነትን የሚያልሙ፣ የመንግሥትን ሞግዚትነት የሚጠብቁ፤ ሠርተው ለፍተውና ጥረው ሳይሆን በአቋራጭ መክበርን ግብ አድርገው የሚንቀሳቀሱ አሉ። በአንድ ጊዜ ካልከበርን በሚልና ሥራን በመምረጥ «ሥራ አጥ» ከሚለው መጠሪያ መላቀቅ የማይፈልጉ ወጣቶችም ቁጥር ቀላል አይደለም።
አሁን ትልቁ ትግልም እንደነዚህ አይነት ወጣቶችን ካላቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ ተላቀው ወደ መስመር እንዲገቡና ከድህነት ራሳቸውን እንዲያላቅቁ ማድረግ ነው። በመሆኑም መንግሥት ከኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ እንዲሁም ሌሎች ወጣቶችን ጭምር በተለያየ ሙያ በማደራጀት ተጨማሪ ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግና በአዋጭ የሥራ መስክ ተሰማርተው አምራች፣ ሥራ ፈጣሪ ዜጋ እንዲሆኑ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ፣ መመሪያ በማውጣትና አስቻይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ጭምር ወደ ተግባር ተገብቷል።
በዚሁ መሰረት በ2009 ዓ.ም 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የወጣቶች ፈንድ መድቧል። ከዚህም ውስጥ 91ነጥብ3 በመቶው ወይም 9 ቢሊዮን 125 ሚሊዮን 757 ሺ 385 ብር መለቀቁን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። ይሁን እንጂ ዛሬም ውጤቱ ከሪፖርት ማድመቂያነት ያለፈ ውጤት እያሳየና የታሰበውን ዓላማ ከግብ እያደረሰ አይደለም። የተዘዋዋሪ ፈንዱን ገንዘብ የወሰዱ ወጣቶች በሁለትና ሦስት ዓመታት ሠርተውና ተለውጠው የተበደሩትን ገንዘብ እየመለሱ አይደለም።
የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴርበሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች አለመፈጠራቸውን አስታውቋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተናበውና ተቀናጅተው የክትትልና የቁጥጥር ሥራውን ባለመሥራታቸው የተፈጠረው ክፍተት ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ በሚል የተያዘውን ዕቅድም አጨናግፏል። ለወጣቶቹ ስኬታማ አለመሆን የመጀመሪያውን ድርሻ መያዝ ያለባቸው ወጣቶቹ ራሳቸው ቢሆኑም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማትም ሥራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ተጠያቂዎች ናቸው።
በተለይም ክልሎች ከተሰጣቸው ኃላፊነት ጭምር የወጣቶችን ተዘዋዋሪ ፈንድ ወጣቱ ተከፋፍሎ የሚበላው ሳይሆን ሠርቶ፣ ነገዶና ለውጦ የሚመልሰው ገንዘብ መሆኑን በማስረዳት ገንዘቡ ለታለመለት አላማ እንዲውል የማድረግ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም። ተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ሥራ ላይ ውሎና ተመልሶ ሌሎች ወጣቶች ወደ ሥራ እንዳይሰማሩ በር ዘግቷል። ይሄም በመሆኑ ዕቅዱ ዓላማውን ስቷል። በዚህም ላይ የነበረው ክፍተት ሳይደፈንና በአሰራር ሳይመለስ በቅርቡ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቧል።
ይሄ ገንዘብ አሁንም «ውሃ ውስጥ የገባች አይጥ» ሆኖ እንዳይቀር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በወጣቶቹ ዘንድ የሚታየውና የተለመደውም ነገር ብድር ለመውሰድ ደፋር መሆንና ሠርቶ ለመመለስ ማፈግፈግ ነው። ለዚህ የተዘዋዋሪ ፈንዱ በወቅቱ አለመመለስ አንዱ ማሳያ ነው። ይሄ የወጣቶች የተሳሳተ አመለካከት ሳይስተካከል፤ ከዚህ ቀደም የወጣውም ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ውሎ ሳይመለስ ተጨማሪ በጀት መመደብ የተገቢነት ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ዛሬም በማህበረሰቡ አካባቢ ያለው «ወይ አበዳሪ ወይ ተበዳሪ ይሞታል» የሚለው አመለካከት አልተስተካከለም።
ስለዚህ በጀቱን መመደብ ብቻ ሳይሆን የወጣቱን አመለካከት ማስተካከል፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን በኃላፊነት ስሜት መሥራት ይገባል። ስለዚህ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በአግባቡ ሥራ ላይ ያልዋለበትንና ለመመለስ ያልተቻለበት ምክንያት ተለይቶ መታወቅ አለበት። ይሄ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይህንንም ሊሠሩ የሚገባቸውና ያልሠሩ አካላትም መጠየቅ አለባቸው፡፡ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የሀገር ሀብት ነው። ሁሉም ሥራ አጥ ወጣት በዙር ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ ‹‹እንደፈነዳ ኳስ›› አንዱ ሜዳ ላይ ከጥቅም ውጪ እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011