የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ በሐዋሳ መካሄድ ከጀመረ ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን አስቆጥሯል። በተለያዩ የውድድር ቦታዎች የሚካሄዱ በርካታ የስፖርት አይነቶች በጠንካራ ፉክክር ታጅበው የቀጠሉ ሲሆን ብዙዎቹ ፍጻሜ እያገኙም ነው። በውድድሩ አንድ ሳምንት ቆይታ ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ የፍጻሜ ፉክክር በተደረገባቸው ውድድሮች ተሳታፊ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሜዳሊያዎችን ለመሰብሰብ የሚያደርጉት ፉክክር ተጠባቂ ነው። ከዚህ ቀደም በሚካሄዱ የተለያዩ አገር አቀፍ ውድድሮች የበርካታ ስፖርተኞች መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ከተፎካካሪነት ባሻገር በውጤታማነት ጎልታ ስትወጣ አለመታየቷ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ያስነሳ እንደነበር ይታወቃል። ይህ የመጀመሪያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ውድድሩ ገና አንድ ሳምንት በሚቀረው በዚህ ወቅት በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አጠቃላይ አሸናፊ የሚሆነውን መገመት ቢከብድም ባለፈው አንድ ሳምንት በተካሄዱ የተለያዩ የፍጻሜ ፉክክሮች አዲስ አበባ ከተማ ከወትሮው ጎልታ የታየችበትን ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች። በቀሪው አንድ ሳምንት በዚሁ ውጤታማነት ከቀጠለችም አጠቃላይ አሸናፊ የምትሆንበት እድል መኖሩን እስካሁን የሰበሰበችው በርካታ ሜዳሊያ ፍንጭ ይሰጣል።
ከትናንት በስቲያ ከተጠናቀቁ ውድድሮች ስንጀምር በ3ለ3 የግማሽ ሜዳ ቅርጫት ኳስ ውድድር በሴቶች አዲስ አበባ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ስትሆን ደቡብና ሲዳማ ክልሎች የብርና የነሐስ ሜዳሊያውን ወስደዋል። በተመሳሳይ ውድድር በወንዶች ሲዳማ ክልል ወርቁን ሲወስድ አዲስ አበባ የብርና ደቡብ ክልል የነሐስ ሜዳሊያውን የግላቸው አድርገዋል።
አዲስ አበባ የወርቅና የብር ሜዳሊያ የወሰደችበት ሌላኛው ውድድር በአትሌቲክስ 8 መቶ ሜትር ወንዶች ተጠቃሽ ሲሆን የነሐሱን ሜዳሊያ ደቡብ ክልል ወስዷል። በተመሳሳይ በሴቶች ኦሮሚያ ክልል የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን አዲስ አበባና ደቡብ የብርና የነሐስ ሜዳሊያውን ወስደዋል። ከኦሊምፒክ ስፖርቶች ውጪ ፉክክር የተደረገበት የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ውድድር ፍጻሜውን ሲያገኝ አዲስ አበባ የሜዳሊያ ስብስቧን ያደመቀችበት ወርቅ የግሏ አድርጋለች። ሐረሪና ድሬዳዋም በዚህ ውድድር ብርና ነሐስ አጥልቀዋል። በሌላ የአትሌቲክስ 100 ሜትር መሠናክል ውድድር አዲስ አበባ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት ወርቅ፣ ብርና ነሐስ ያገኘችበት ውጤት በጉልህ የሚጠቀስ ነው። በሜዳ ተግባር በሴቶች የርዝመት ዝላይ ወርቅ፣ በሴቶች 400 ሜትር ብር ማስመዝገቧ ይታወቃል። በዲስከስ ውርወራ በሴቶች ወርቅ፣ በወንዶች ሱልስ ዝላይ የነሐስ ሜዳሊያ ከማስመዝገቧ ባሻገር በብስክሌት የቡድን ክሮኖ ሜትር በሴቶች 20 ኪሎ ሜትር በሸፈነና፣ በወንዶች 30 ኪሎ ሜትር በሸፈነ ውድድር በሁለቱም ጾታ ሁለት የወርቅ ሜዳልያ ማስመዝገብ ችላለች። ትናንት የተካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮችን ውጤት ሳይጨምር አዲስ አበባ አስራ አንድ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኖ ለማጠናቀቅ በተሻለ መንገድ ላይ እየተጓዘች ትገኛለች።
ተሳታፊዎች በርካታ ሜዳሊያዎችን ለመሰብሰብ ከተዘጋጁባቸው ስፖርቶች መካከል የኦሊምፒክ ስፖርት የሆነው የወርልድ ቴኳንዶ ውድድር ትናንት በሐዋሳ መምህራን ኮሌጅ በይፋ የተጀመረ ሲሆን በውድድሩ አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ጨምሮ 8 ክልሎች በአስር የተለያዩ ካታጎሪዎች፣ በወንድና በሴት ከ15 እስከ 18 ዕድሜ ክልል ያሉ መቶ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት ይሆናሉ። በሌላኛው የኦሊምፒክ ስፖርት የቦክስ ውድድር ትናንት ከሰአት ጀምሮ የተለያዩ የፍጻሜ ፍልሚያዎች እየተከናወኑ ይገኛል። አዲስ አበባም በነዚህ ስፖርቶች ተጨማሪ ወርቆችን ለመሰብሰብ ተዘጋጅተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ “የአዲስ አበባ ልዑክ በቆይታው በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል፣ እስካሁን ያደረግናቸው ውድድሮች በአንፃሩ ጥሩ ቢሆኑም ቀን በቀን በሚካሄዱ ውድድሮችና የሜዳሊያ ፍፃሜዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መወዳደር ይገባል” በማለት አዲስ አበባ በኦሊምፒኩ እያስመዘገበች ስለሚገኘው ስኬት አስተያየት ሰጥተዋል።
የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ “ እውነተኛ ዕድሜ ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ከኦሊምፒክ ስፖርቶች በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ ጅምናስቲክና ወርልድ ቴኳንዶ ፉክክሮችን እያስተናገደ ይገኛል። ከኦሊምፒከ ስፖርቶች ውጪም ቼዝ፣ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶና ውሹ ስፖርቶች ፉክክር የሚደረግባቸው ሆነዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014