”አገርኛ” ምንጫቸው፣ መነሻቸው፣ መገኛቸውም ሆነ ሙሉ አድራሻቸው አገር ውስጥ የሆኑ፤ ባለቤታቸውም ሆነ ፈጣሪ ተጠቃሚያቸው ኢትዮጵያዊ(ያን) የሆኑ ተቋማትም ሆኑ ሌሎች አገር በቀል ሀብቶች ናቸውና ሲያስተናግድ ቆይቷል።
አገር በቀል የሆኑ ድርጅቶች፣ ባህላዊ አልባሳት፣ ኢትዮጵያዊ የሆኑ በጎ አድራጊ ግለሰቦች፣ ለኢትዮጵያ ችግር ኢትዮጵያዊ መፍትሄ አፈላላጊ አካላት፣ ቡድኖች፣ ተቋማት ወዘተ ሁሉ አገራዊ ናቸውና አምዱ በሚገባ ሲያስተናግዳቸው ቆይቷል። ”ቡሳ ጎኖፋ”ም የዛሬው ትኩረታችን ነው። ከሁሉም በፊት ለአጠቃላይ ግንዛቤ ያግዘን ዘንድ ”አገር በቀል እውቀት”ን እንመልከት።
ሰሞኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ”አገር በቀል እውቀቶች – በእጅ [እንደ] ያዙት ወርቅ … ይቆጠራል!” በሚል ርእስ የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሶ ለንባብ ባበቃው ጽሑፍ ”አገር በቀል እውቀት ማለት በውስን አካባቢዎች ላይ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ገጽታዎች ዙሪያ ላሉ ክፍተቶች መፍትሄ ይሆኑ ዘንድ ባህላዊ በሆነ መንገድ በአንድ ወይም በተወሰኑ ሰዎች የሚመነጭና የሚተገበር እውቀት ነው።” በማለት አስፍሯል። ”የማህበረሰብ እውቀት”ን ደግሞ ”ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ የሕይወት ገፅታዎች የሚዳሰሱበትና መፍትሄ የሚሰጥበት የተገለፀና ያልተገለፀ እውቀትና ልምድን ያጠቃለለ ነው።” ሲል ይበይነዋል። እነዚህን በአግባቡ አልምቶ ከመጠቀም አኳያ ያለንበትንም ሁኔታም ”ነገር ግን በአገሪቱ የሚስተዋሉ ፈርጀ ብዙ ችግሮቻችን አገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅሞ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ፤ ከሌሎች አገሮች (ከምዕራባውያን) ተሞክሮ ተቀድ[ተው] የሚወሰዱ እርምጃዎች ችግሮቻችንን ’በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” አድርገውታል። ይህም አሁን አገሪቱ ለገባችበት ምስቅልቅል አንዱ ምክንያት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።” ሲል ከማሳሰቢያ ጋር ከገለፀ በኋላ ”ሆኖም እንደ ገዳ፣ አባጋር ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ለአገር ዕድገት እና ለሰላም ግንባታ መሠረት የሆኑ አገር በቀል እውቀቶች ባለቤት ብንሆንም፤ “በእጅ የያዙት ወርቅ … ይቆጠራል” እንዲሉ አበው እነዚህን እውቀቶች በቅጡ እንዳላለማናቸውና እንዳልተጠቀምንባቸው” ይገልፃል። ተጠቅመን ቢሆን ኖሮ የት እንደምንደርስና ወደ ፊት አልምተን ልንጠቀም እንደሚገባም በዝርዝር ያስረዳል። ይህ ቀጥለን ለምንቃኘው ”ቡሳ ጎኖፋ” ተቋም መሰረት ይሆነን ዘንድ ይዘነው ወደ ተነሳንበት እንዝለቅ።
የዛሬው ”አገርኛ” የሚቃኘው አገር በቀል እውቀት የሆነውን፣ ”ቡሳ ጎኖፋ” ማህበረ-ባህላዊ እሴትን ሲሆን፤ ይህ እሴት አስፈላጊውን ሁሉ አሟልቶ በመገኘቱ እራሱን ችሎ፤ እራሱንም ሆኖ፤ ቀድሞ የነበረውን የክልሉን አደጋ ስጋት ቢሮ ወደ ራሱ አምጥቶና በስሩ አድርጎ ወደ ዘመናዊ ተቋምነት ስለመሸጋገሩ ጉዳይ ነው።
ጨፌ ኦሮሚያ እያካሄደ በነበረው 1ኛ ዓመት 6ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የገዳ ስርአት አካል በሆነው ስርአት ”ቡሳ ጎኖፋ” የተሰኘ አዲስ አዋጅ መጽደቁ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተሰማ። የመረጃው ምንጭም ስለ አዋጁ ያስረዱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ መሆናቸው፤ ስለ አዋጁ አስፈላጊነትም የኦሮሞን ሕዝብ አቃፊነቱንና የመረዳዳት ባህሉን ማንሳታቸው፤ አዋጁ ቀደም ሲል በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያለና የቆየ ሥርዓት ሲሆን፤ (በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተስተዋለው ድርቅ እና ጦርነት ወቅት ያሳየውን መደጋገፍ በምሳሌነት በማንሳት) የሕዝቦች የመረዳዳት እና መደጋገፍ ባህልን የሚያሳድግ፤ እንዲሁም፣ የመስጠት ባህልን የሚያጎለብት መሆኑን መግለፃቸው ከእነዚሁ ምንጮች ታወቀ። ”ገዳ የሰው ልጅ መተዳደሪያ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም፤ ይህን የመረዳዳት እና የመስጠት ባህልን ለማጠናከር አዋጁ እንዳስፈለገ” መግለፃቸውም ተነገረ። የእኛም የዛሬው ጽሑፋችን ከዚህ (ከአዋጁ በ441 አብላጫ ድምፅ መፅደቅ በኋላ) ወቅት ጀምሮ ያለውን ይመለከታል።
የገዳ ስርዓት (Gada system) አካልና የኦሮሞ ሕዝብ ጥንታዊ የመረዳጃ ስርዓት የሆነው ቡሳ ጎኖፋ ሥርአት የኦሮሞ ህዝብ ሰው ሰራሽም ይሁን ተፈጥሯዊ ችግር ሲያጋጥመው ችግሩን በትእግስት፣ በዘዴና በተረጋጋ ሁኔታ ለማለፍ የሚታገዝበትና እርስ በእርሱም የሚተጋገዝበት ጥንታዊ ባህል መሆኑ፤ ንቅናቄውን ማስጀመር ያስፈለገበትም ምክንያት የሕዝቡን የመረዳዳት ባህል ለማጎልበት እንደሆነ፤ ሥርአቱ ተቋማዊ መልክ እንዲኖረው ታስቦ በቢሮ ደረጃ እንደ ተቋቋመ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ገረመው ኦሊቃ ያስረዳሉ።
ስለ ”ገዳ ሥርአት” ከጥናቶችም እናንሳ፤
በገዳ ስርአት ቀዳሚ ተጠቃሽ የሆኑት ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሠ (ከቢቢሲ ጋር አድርገውት በነበረ ቆይታ) ኢትዮጵያ ያላትን አገር በቀል የአስተዳደር ሁኔታ ከ45 ዓመታት በፊት “ኦሮሞ ዴሞክራሲ፤ አን ኢንዲጂኒየስ አፍሪካን ፖለቲካል ሲስተም” (OROMO DEMOCRACY: An Indigenous African Political System) በሚል ርእስ ስለ ሰሩት ጥናታቸው (መጽሐፍ) ”ምን ያስደነቀዎት ነገር አገኙ?” ሲባሉ ”በምስራቃዊ አፍሪካ በሙሉ የዕድሜ አደረጃጀት ስርዓት አላቸው። ይህ ፖለቲካዊ ሳይሆን ማህበራዊ ስርዓት ነው። ስርዓቱም የተዘረጋው አንድ ሰው ወደ ሌላኛው በእድሜ የሚሸጋገርበትን ለመቀየስ ነው።” ነበር ያሉት። ”የገዳ ስርዓት አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን ለምሳሌ ስድስት አባላት ያሉትን ጉሚን ብንወስድ የመላው ቦረና ጉባኤ ማለት ሲሆን ሕግ ወሳኝና ከሁሉም በላይ የሆነ አካል ማለት ነው፤ ከባለሥልጣናቶቹም ጭምር። በጣም የሚያስገርመው፤ ውሳኔ ላይ የሚደረሰው በስምምነት ነው።” በማለትም ሀሳባቸውን ያዳብሩታል። ”ስርዓት ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ቋንቋ አላቸው። የኢትዮጵያ ቋንቋ ተመራማሪዎች የዴሞክራሲ ቋንቋን ለማጥናት [ወደ’ዛ] መሄድ አለባቸው። እኔ ቋንቋውን ስለማልችል ማድረግ አልችልም። ይህ ትልቅ ሳይንሳዊ ስርዓት መሆኑን ለማስረዳት ችያለሁም ይላሉ።
”የገዳ ስርዓት ዘመናዊ አስተዳደር ሊሆን ይችላል?” ለሚለው የቢቢሲ ጥያቄም ”በደንብ፤ በአሁኑ መጽሐፌ የመጨረሻ ምዕራፍ ‘ገዳ ኢን ዘ ፊውቸር ኦፍ ኦሮሞ ዴሞክራሲ’ የምጠቅሰው ይህንኑ ነው።” የሚል መልስን ነበር የሰጡት። ይህም ይሄው በ”ቡሳ ጎኖፋ” እውን ሆነ። ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ካገኘነው መረጃ ደግሞ ጥቂት እናክል፤
የኦሮሞ ሕዝብ እንደሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ለህልውናው ሲል በሚያከናውነው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችና ማኅበራዊ ግንኙነቶች እንዲሁም ከአካባቢውና ከተፈጥሮ ጋር በሚያደርጋቸው መስተጋብሮች የፈጠራቸው፣ አሁንም እየፈጠራቸው የሚገኙና የማንነቱ መገለጫ የሆኑ አያሌ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ነው። […] የገዳ ሥርዓት ከኦሮሞ ብሔር ሁለንተናዊ ሕይወትና ዕድገት ጋር በእጅጉ ተያያዥነት ያለው ሲሆን ሥርዓቱ ከቀላል የዕድገት እርከን ላይ ተነስቶ ቀስ በቀስ ውስብስብ ወደሆነ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት እያደገ የመጣ ነው። የኦሮሞ ብሔር የገዳን ሥርዓት ለረጅም ዘመናት ሲተገብረው ከመቆየቱም በላይ በሂደትም እያዳበረውና እያሳደገው ይገኛል። የገዳ ሥርዓት የኦሮሞ ብሔር ዓባላት የማንነት መገለጫ የሆኑ አንኳር ባህላዊ ገጽታዎች፣ ታሪክና እምነት እንዲሁም አገር በቀል የሆነ እውቀትን አካቶ የያዘ ጥንታዊ የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት ነው። (”ቅርስ” መጽሔት፣ 2009 ዓ.ም)
ከስምንት መቶ አመታት በላይ (የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ 2009 ጥናት ”ከ1522 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሞዎች ሲተገበር የኖረ” ካለ በኋላ ”በቃል ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሥርአቱ ከዛ በፊት ለበርካታ አመታት ሲሰራበት የነበረ ስለመሆኑ” ያስረዳል) የኦሮሞ ብሔር ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርአት በመሆን ሲያገለግል የቆየው ”የገዳ ሥርዓት ሰፊና ውስብስብ፣ በውስጡ አያሌ ንዑሳን ተቋማትንና አደረጃጀትን ያካተተ ነው። ለምሳሌ ያህል የገዳ ሥርዓት በግጭቶች ሳቢያ የተከሰቱ ችግሮችን በሂደት ለመፍታትና የተጎዳ የኅብረተሰብ ክፍልን ወይም ግለሰብን መልሶ ወደ ሰላማዊና የተረጋጋ ሕይወት ለማምጣት የሚሰሩ ተቋማት አሉት።” የሚለው የባለሥልጣኑ መጽሔት ስንቄን፣ ጉማን፣ ሞጋሳንና ሌሎችንም በማስረጃነት ያቀርባል። ለዋልታ (ዲሴምበር 2፣ 2016) ሀሳባቸውን ያካፈሉ እንግዳም “ከገዳ ስርዓት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚነሱት የሞጋሣና ሜደቻ፣ የሲንቄና የሽምግልና የጉማ፣ የከለቻና ጫጩ፣ የቦኩና የቃሉ እንዲሁም የአያንቱ ተቋማትን መጥቀስ ይቻላል።” በማለት መግለፃቸው ይታወሳል። ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት፣ የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገረመው ኦሊቃም ይህንኑ ነው ያረጋገጡልን።
መጽሔቱ ”የኦሮሞ ብሔር ባህላዊ የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሆነውን የገዳን ሥርዓት ከኅዳር 19 እስከ ኅዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደው አስራ አንደኛው የማይዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶች ጥበቃ የበይነ መንግስታት (intergovernmental) ኮሚቴ ጉባዔ ላይ በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገቡ ከቀረቡት 37 የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነበር። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እ.ኤ.አ. በ2003 በጸደቀው የማይዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶች ጥበቃ ዓለም አቀፍ ሥምምነት መሠረት የገዳን ሥርዓት ለማስመዝገብ የተዘጋጀው የማስመረጫ ሰነድ አምስቱን የመመዘኛ መስፈርቶች አሟልቶ ስለመገኘቱ ዓባል አገራት ውይይት ካደረጉበት በኋላ አዎንታዊ አስተያየታቸውን በመስጠታቸው ሕዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም (November 30, 2016) በፋይል ቁጥር 01164 በውሳኔ ቁጥር 11.com.10. b.11 የገዳ ሥርዓት በሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስነት ተመዝግቧል። የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ የተመዘገበ ሦስተኛው የኢትዮጵያ የማይዳሰስ ቅርስ ነው።” በማለት የተሟላ መረጃን ያቀርባል። የዋልታው እንግዳም ”እኛ ኢትዮጵያዊያኖች የሰው ልጆች መገኛ፣ የጥንት ስልጣኔ ባለቤቶች ብቻ ሳንሆን የዘመናዊው የዴሞክራሲ ስርዓት መስራችም እንደሆንን አለም ለገዳ ስርዓት በሰጠው እውቅና አረጋግጦልናል።” በማለት እውቅናውን ያፀኑታል።
የኦሮሞ ህዝብ ወደ ነበረበት ቱባ ባህልና እሴቱን ጠብቆ ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንዲረዳዳና እንዲደጋገፉ ያግዛል በሚል ”ቡሳ ጎኖፋ” በአዋጅ መቋቋሙን፤ በዚሁ ስያሜም ንቅናቄ መጀመሩን፤ ድሮ የነበረውን የአደጋ ስጋት ቢሮ ተግባርና ኃላፊነትን ደርቦ ወደ ስራ መግባቱን፤ የነበረውን መዋቅር ተጠቅሞም ህዝቡ ጋር ተደራሽ መሆኑን አቶ ገረመው ይናገራሉ።
ሥርዓቱ በተጠናከረ መልኩ ሲተገበር ሕዝቡ ሌሎችን ሳይጠብቅ በራሱ መንገድ ከችግሩ እንዲወጣ የሚያደርግ ሁኔታ ይፈጥራል። ‘ቡሳ ጎኖፋ’ በዋናነት ከመንግስት ከሚመደብለት በጀት በተጨማሪ ከአባላት መዋጮና ከሌሎች አካላት ድጋፍ የሚደጎም መሆኑንም ያነሱ ሲሆን፤ ‘ቡሳ ጎኖፋ’ የተሰኘው ጥንታዊ የሕዝቡ መረዳጃና ማቋቋሚያ ሥርዓትም ሕጋዊነት ባለው መልኩ እንደሚተገበርም የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ ያለው ሁኔታ ያስረዳል።
አቶ ገረመው እንደሚሉትም ማንኛውም ሰው አባል መሆን እንደሚችልና ለዚህም መመሪያ የተዘጋጀ መሆኑን፤ ህብረተሰቡም ባለው አቅም ሁሉ የሚሳተፍበት ንቅናቄና ተቋም እንደሆነ ገልፀዋል።
ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፣ በኤፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የተለያዩ እርዳታዎችን ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በተለያዩ ክልሎች ባጋጠመው ድርቅና በጦርነት ምክንያት ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ በማስተባበር ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በዓይነት መሰብሰብ መቻሉን እና ለአማራ፣ አፋር እና ዛሬ ደግሞ ለኦሮሚያ ክልል ማስረከባቸውን ገልጸዋል። አቶ ሽመልስ አብዲሳ በኦሮሞ ህዝብና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስም የተሰጠውን ድጋፍ በማመስገን በህዝቡ ውስጥ የሚገኘውን የድጋፍ ባህልን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦችም እርስ በዕርስ መደጋገፍ እንዳለባቸው ተናግረዋል። በገዳ ስርዓት ባህል ቡሳ ጎኖፋ የተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የተቋቋመ መሆኑን በመግለፅ ይህም ተቋም የሰው ልጆችን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ ወጣቶች ስለሥርዓቱ ታሪካዊ አመጣጥና ለማኅበረሰቡ የሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በተመለከተ ከአባ ገዳዎች፣ አርጋደጌቲ (ካዩት፣ ከሰሙትና በሥርዓቱ ውስጥ በማለፋቸው ስለ ገዳ ሥርዓት ታሪክና ምንነት ጠንቅቀው የሚያውቁ) እና የአገር ሽማግሌዎች የሚሰጠውን የቃል ትምህርት በአንክሮ መከታተልና መተግበር ይኖርባቸዋል፡ የሚለውን ሃሳብ እኛም እንጋራለን። የገዳ ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ እንዲታወቅና በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት የተመዘገበ ሦስተኛው የኢትዮጵያ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ እንዲሆን በመንግስትና በሕዝቡ የተደረገው እልህ አስጨራሽ ጥረት ቅርሱን ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፉ ሂደትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል የሚለውንም ሆነ፤ መንግስት ከሥርዓቱ ጋር በተያያዘ ሕጋዊ ማዕቀፎችን ከማውጣት በተጓዳኝ በጀት በመመደብና የቅርሱ ማከናወኛ ሥፍራዎችን የመጠበቅና መሰረተ ልማት የመገንባት፤ እንዲሁም፣ ገልማዎችን (የአባ ገዳ አዳራሽ ወይም አስተዳደራዊ ማዕከሎችን) በመስራት በቅርሱ ጥበቃ ያሳየውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል በሚለውም እንስማማለን። በቀጣይም አገራችን የበርካታ አኩሪ ባህሎችና መስህቦች መገኛ በመሆኗ ጠንክረን በመስራት ባህል ወጋችንን ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቃቸው በማድረግ የቱሪዝም ኢንዱስትሪያችንን ልናሳድግ ይገባናል የሚለውን ጥሪና ማሳሰቢያም ሆነ፤ ገዳ ”… ለምን ኦሮሚያ ብቻ? በመላ አገሪቱስ ለምን ስርአተ ትምህርቱ ውስጥ ተካትቶ አይሰጥም?” የሚለውን ጥያቄ እንጋራለን። ”የገዳ ሥርዓታችንም ሆነ ከእሱው አብራክ የወጣውና የ”ቡሳ ጎኖፋ” ስርአት የመቻቻልና የመከባበር፤ የመደጋገፍና የመተጋገዝ፤ የአብሮነትና አቃፊነት ባሕላችን ከመሆኑም በላይ ለህዳሴ ጉዟችንም መሠረት ነው!!” የሚለውን እናጸናለን። ስንብታችንም ”ቡሳ ጎኖፋ ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ በስፋት ይሰራል” በሚለው የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ምክትል ኃላፊ አቶ ገረመው ኦሊቃ አስተያየት ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2014