አንድ አብሮ አደግ ጓደኛ አለኝ፤ ከዚህ ጓደኛዬ ጋር ብዙ ጊዜ ነው የምንጨቃጨቅ። የምንጨቃጨቅበትን ምክንያት ልንገራችሁና ማን ትክክል እንደሆነ ፍረዱ።
ምግብ ለመብላት ወይም አንድ ሁለት ለማለት ስንገባ፤ አዲስ ቤት ከሆነ ዋጋ ይጠይቃል። እኔ ደግሞ በመጠየቁ እናደዳለሁ። ‹‹ፋራ ነህ እኮ! ቢያንስ ‹ሜኑ አምጡልኝ› ይባላል እንጂ እንዴት የእያንዳንዱን ምግብ ዝርዝር እየጠራህ ዋጋ ትጠይቃለህ?›› እያልኩ እናደድበታለሁ።
እሱም በበኩሉ ፋራው እኔ እንደሆንኩ በቁጣ ይወርድብኛል። ዋጋ መጠየቅን የመሰልጠን ምልክት ነው የሚያደርገው፤ የምግብና መጠጥ ዋጋ ዝርዝሩን አያምነውም፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዕለቱ ዋጋ ስለሚጨምር ወቅታዊ መረጃ አይኖረውም ብሎ ነው የሚያምን። በዚያ ላይ የምግብ ዝርዝሩ ላይ ያሉት ምግቦች ስለማይኖሩ፤ በቀጥታ ያለውን ጠይቆ አስተናጋጇ ስትነግረው እዚያው ላይ እያከታተለ ዋጋውን ይጠይቃል። እኔ ደግሞ ‹‹አስፎገረኝ›› በሚል ስሜት እንደማፈር ብየ ትኩረቴን ወደሌላ አደርጋለሁ።
በነገራችን ላይ ይህን የሚያደርገው ሲጋብዝ ብቻ አይደለም፤ ሲጋበዝም ጭምር ነው። ‹‹የትኛውም ሀብታም ይጋብዘኝ፤ አይገባውም የምለው ቤት ውስጥ የተጋነነ ዋጋ መክፈል የለበትም›› ነው የሚል። ዋጋውን ካላመነበት ካልወጣን ይላል።
ለዚህ ትዝብት መነሻ የሆነኝ ባለፈው ቅዳሜ (ግንቦት 20) ይህ ጓደኛዬ እራት እንብላ ብሎኝ ካራ አካባቢ ከአንድ ቤት ገብተን ነው። በእውነቱ የገባንበት ቤት ያን ያህል ትልቅ የሚባል ቤት አይደለም፤ በየመንገዱ ከሚገኙት አነስተኛ ሆቴሎች አንዱ ነው።
ከአንድ ውጪም ውስጡም ሰው የበዛበት ሆቴል ገብተን እንደተቀመጥን አስተናጋጇ መጥታ በትህትና ‹‹ምን ልታዘዝ›› አለችን። የሚበላ ጠይቅናት ያሉትን ምግቦች ነገረችን። ይሄው ልማደኛ ጓደኛዬ እንደልማዱ ዋጋ ጠየቀ። ለአንድ ምግብ ዝቅተኛ የሚባለው ዋጋ 170 ብር ነው። በፍጹም እዚህ ቤት ውስጥ በዚህ ዋጋ አንበላም ካልወጣን አለ፤ እኔም እንደተለመደው በ‹‹እንፎገራለን›› ስሜት ብለማመጥ ሊሰማኝ አልቻለም፤ ትቶኝ ተነሳ። እኔም ተነሳሁ። በዙሪያችን የነበሩ ሰዎች አተያይ የግርምትና የትዝብት ነበር። ‹‹ምን አይነት ፋራዎች ናቸው›› እያሉ ይሆናል።
እዚያ ቤት ውስጥ ዝቅተኛ ዋጋ 170 ብር መሆኑን ካየሁ ወዲህ ግን ያ ጓደኛዬ ትክክል መሆኑን አመንኩ። እውነትም እኔ ነበርኩ ፋራ። እንደዚህ አይነት መረን የለቀቀና ይሉኝታ የለሽ ቤት ውስጥ ይሉኝታ አያስፈልግም። የፈለጋቸውን ይበሉ ጥሎ መሄድ መብት ነው። የውሃ መድፊያ የሌለው መጸዳጃ ቤት ይዘው እኮ ነው በዋጋ መቆለል ብቻ የቤታቸውን ደረጃ ከፍ ያደረጉ የሚመስላቸው።
አዲስ አበባ ውስጥ አንድ የሚገርመኝ ነገር፤ አንድ አካባቢ ባሉ ቤቶች በተመሳሳይ ደረጃና በተመሳሳይ የምግብ ጥራት ላይ ሆነው የዋጋ ልዩነታቸው ግን በተለምዶ ‹‹ማዘር ቤቶች›› የሚባሉት ውስጥ ምሳ ያበላል።
ብዙ ጊዜ እንደምናስተውለው የዋጋ ልዩነት የሚታየው በቤቶች ደረጃ እንጂ በምግብ ይዘት ልዩነት አይደለም። እርግጥ ነው ትልቅ ደረጃ ያለው ቤት ሲገነባ ብዙ ወጪ አስወጥቷል፤ የኪራይ ከሆነም ኪራዩ ውድ ነው የሚሆን። ይህ ስለሚታወቅ መሰለኝ ትልቅ ደረጃ ያለው ቤቶች ውስጥ የዋጋ መወደድ ብዙም አይገርምም።
ግን የቤቱ ማሸብረቅ ለተመጋቢው ምን ጥቅም አለው? ወደ ሰውነቴ የሚሄደው የቤቱ ቀለም ነው ወይስ ምግቡ ነው? ይህን ያልኩበት ምክንያት በትልልቅ ቤቶች ውስጥ የምግቡ መጠን አነስተኛ ስለሚሆን ነው። ጥብስ አዘህ፤ በትንሽ ሳህን መረቅ ይሞላና በዚያ መረቅ ውስጥ የሚዋኙ ቲማቲምና ሽንኩርት እና አንዳንድ ሥጋዎች ናቸው። እነዚህ ቤቶች ግን በደረጃቸው ልክ የሚመጥን ምግብ ቢያቀርቡ ለቤታቸው ክብር አይሻልም ነበር ወይ?
በነገራችን ላይ ይሄ ነገር የአገልግሎት ሰጪዎች ብቻ ሳይሆን የተጠቃሚውም ችግር ነው። የተወደደ ነገር እንወዳለን። ‹‹ሐበሻ የረከሰ አይገዛም›› የሚባል አባባል አለ። ደረጃው ከርካሽ ዕቃዎች በታች ቢሆን እንኳን የተወደደ ነገር ነው የምንወድ። ‹‹ክብር›› የምንለው ነገር አለ። በምንጠቀመው ዕቃ ወይም በምንመገበው ምግብ መጠንና ጥራት ሳይሆን በቤቱ ደረጃና በዋጋው ውድነት ነው ክብራችንን የምንገልጸው።
ከአራት ይሁን አምስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ‹‹እሁድ መዝናኛ›› ፕሮግራም ላይ ያየሁት ትዝ አለኝ። ‹‹ታዋቂነት እና መዘዙ›› በሚል ርዕስ የቀረበ ነበር። ታዋቂ ሰዎች ታዋቂ በመሆናቸው የሚገደቡትን ገደብ እየተናገረ ነበር።
አርቲስት ሥዩም ተፈራ መንገድ ዳር የሚሸጥ ፓስቲ በጣም እወዳለሁ አለ። ይህን ፓስቲ ግን በነፃነት መብላት አይችልም ነበር። ሲበላ ያየው አላፊ አግዳሚ ሁሉ በግርምት ይመለከተዋል። በእነዚህ ሰዎች አስተሳሰብ ፓስቲ የሚበላው በምርጫና በፍላጎት ሳይሆን በድህነት ነው። አርቲስት ሥዩም ምን ቸገረኝ ብሎ ነው ፓስቲ የሚበላ እያሉ ነው። እነዚህ ሰዎች ከባባድ የሥጋ ምግቦች መዘወተር እንደሌለባቸው ሐኪሞች የሚሉትን እንኳን ሰምተው አያውቁም ማለት ነው። አርቲስት ሥዩም አርቲስት ስለሆነ ብቻ ከሳምንት ሳምንት ከዕለት ዕለት ቁርጥ፣ ፒዛ፣ በርገር…. ሊበላ አይችልም። ለጤናም የሚመከረው ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ያሉ ምግቦችን መቀያየር ነው።
በተመሳሳይ ሌሎች ታዋቂ ሰዎችም በዚያ ፕሮግራም ላይ ሲናገሩ የነበረው አነስተኛ ቤቶች ውስጥ ሲገኙ ብዙ ሰው በግርምት ይመለከታቸው እንደነበር ነው። በእውነቱ ይሄ ኋላቀር አስተሳሰብ ነው ሊባል የሚችል። አንድ ሰው ሀብታም ስለሆነ ብቻ ባለኮከብ ሆቴል ብቻ እየመረጠ ሊሄድ አይችልም። በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጁና በአነስተኛ ቤቶች ውስጥ ያሉ ምግቦችም ያስፈልጉታል።
በተለምዶ ‹‹ማዘር ቤቶች›› የሚባሉ ምግብ ቤቶች አሉ። በአዲስ አበባ በአንዳንድ ጎዳናዎች ዳርቻ የምናያቸው የኮንቴነር ቤቶች ማለት ነው። ለምሳሌ አምስት ኪሎ ከየካቲት 12 ሆስፒታል ጀርባ ያሉት። እነዚህ ቤቶች ውስጥ የሚሰራ ፍርፍር እና ሽሮ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ከሚሰራ ሽሮ የበለጠ ይጣፍጣሉ። ምክንያቱም አሰራራቸው ለአብዛኛው ሀበሻ ቅርብ ነው።
ዳሩ ግን እነዚህ ቤቶች ውስጥ መታየት የችግር ማሳያ ስለሚመስላቸው ብዙ የማይገቡ ሰዎች ይኖራሉ። ስነ ልቦናም ጭምር ነው። ለምሳሌ፤ ከአንድ አይነት ግብዓት፣ በአንድ የምግብ አዘጋጅ፣ አንድ ቦታ ተዘጋጅቶ፤ አንደኛው ወደ ትልቅ ሆቴል፣ አንደኛው ደግሞ መንገድ ዳር ወዳለች ትንሽ ቤት ተወሰደ እንበል። ለአንድ ቀብራራ ነኝ ባይ ሁለቱንም አቅምሶ ‹‹የትኛው ይሻላል›› ቢሉት ትልቅ ሆቴል ውስጥ ያለውን ሊመርጥ ይችላል።
መነሻዬ ከአንድ አነስተኛ ሆቴል ውስጥ ያየሁት የዋጋ መጋነን ነው። ምንም እንኳን የዋጋ መጋነን በአገር አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ቢሆንም፤ ዳሩ ግን እኛም ቀብራራነቱን እናበዛዋለን። የተወደደ ነገር ነው ትልቅ የሚያደርገን የሚመስለን። መለኪያችን የምንመገበው ምግብ ወይም የምንገለገልበት ዕቃ ጥራት እንጂ የዋጋው ውድነት መሆን የለበትም!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2014