
አገር ማለት ሰው ነው። አገርና ሰው፣ ሰውና አገር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ሰው የሌለው ባዶ መሬት አልያም የራሱ ሉአላዊ ክልል እና ነጻ ዜጎች የሌለው መሬት ብቻውን አገር ሊባል አይችልም። እያንዳንዱ ሰው ዴሞክራሲያዊም ሆነ ሰብአዊ መብቶቹ ተከብረው መኖር የሚችለው በቅድሚያ ነፃ እና ሉአላዊ አገር ሲኖረው ነው። ከዚህ ውጭ ግን በሌሎች ተጽዕኖ ስር ያለች እና ሉአላዊነቷን የተነጠቀች አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ነፃነት ሊኖራቸው አይችልም።
ኢትዮጵያ በየዘመኑ ለነፃነቷ ዋጋ የከፈለች አገር ናት። ቀደም ሲል በቅኝ ግዛት ዘመን ምዕራባውያን ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት በተሯሯጡበት ዘመን እንኳን፣ ሉአላዊነቷን አሳልፋ ያልሰጠች እና እምቢ ለነጻነቴ በሚል የታገለች፤ ከራሷም አልፋ ለሌሎች ጥቁር ህዝቦች የትግል ተምሳሌት የሆነች አገር ናት። በዚህ የተነሳ በአድዋ ጦርነት ወራሪውን የተደራጀ ቡድን አሳፍራ በመመለስ ታሪክ ሰርታለች። ይህ የሆነው ደግሞ ኢትጵያውያን አንድ በመሆናቸውና የአገርን ምስጢር በቅጡ በመረዳታቸው ነው።
ከዚህም አልፎ የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ በርካታ ጊዜ ሙከራ አድርገዋል። ከፖርቹጋሎች ጀምሮ አፍሪካዊቷ ግብጽም ሆነች እነዚያድባሬ የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት በመድፈር ድንበር ዘልቀው የገቡበት ጊዜ እንደነበር ታሪክ ይናገራል። ይሁን እንጂ እነዚህንም ቢሆን ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብና በአንድ መንፈስ በጋራ በመታገል የኢትዮጵያን ነጻነትና ሉአላዊነት አስከብረው ቆይተዋል።
እነሆ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከጉያዋ በበቀሉ ጠላቶች ሉአላዊነቷ ተደፍሮ በርካታ ፈተናዎችን አይታለች። በተለይ ሕወሓትና ሸኔ የሚባሉ የውስጥ ጠላቶች አንድ እግራቸውን በአገር ውስጥ ሌላ እግራቸውን ከውጭ ጠላቶች ጋር በማድረግ የኢትዮጵያን ነፃነት ለመንጠቅ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፤ ያልማሱት ጉድጓድ የለም። በዚህ የተነሳ በተለይ ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ በርካታ ችግሮች ተከስተዋል። አገር በሰላም መዋል አቅቷት በየቀኑ የጥይት ድምጽ የሚሰማበት እና ዜጎች በየጊዜው የሚረግፉበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድገዋል።
በአንጻሩ ደግሞ ይህንን የሕወሓት እና የሸኔ ሴራና ተንኮል ያልተረዱ አልያም ለግል ጥቅማቸው ብቻ የቆሙ ሆዳሞች ከነዚህ አካላት ጋር በተለያየ መንገድ ሲሰሩም ተመልክተናል። ለምሳሌ ለነዚህ ቡድኖች አንዴ ጥይት፣ ሌላ ጊዜ ገንዘብ ሊያቀብሉ ሲሞክሩ የሚያዙ ባንዳዎችን አይተናል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኮንትሮባንድ ስም ለነዚህ አካላት ልዩ ልዩ ግብይቶችን የሚፈጽሙ አካላት እንዳሉ ታዝበናል። ሆኖም እነዚህ አካላት የሚፈፅሙት ተግባር አገርን ከመሸጥ የሚተናነስ አይደለም።
ሕወሓት ዋነኛ ተልዕኮው አገርን ማፍረስ ስለመሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር አሸባሪ ብሎ የፈረጀው ቡድን እንደሆነ ሁላችንም የምንገነዘበው ነው። በዚህ የተነሳ ቡድኑ የሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ የሽብር እና አገርን የማፍረስ ተግባር ነው። ከዚህም አልፎ አገርን ለውጭ ጠላቶች አሳልፎ ለመስጠት እና ኢትዮጵያን ብዙ ቦታ በመበታተን ደካማ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ለመፍጠር የሚፈልጉ አገራትን ዓላማ የማስፈፀም ድብቅ አጀንዳው ነው።
ይህ ቡድን ዓላውን ለማስፈፀም ታዲያ በአንድ በኩል ለ27 አመታት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ያከማቸውን ሃብት እየመነዘረ ለድብቅ አጀንዳው ማስፈጸሚያ ይጠቀማል። በተለይ የቡድኑ አላማ በግልጽ ያልገባቸው አልያም ገንዘብ ካገኙ የቤታቸውንም ንብረት ከመሸጥ ወደኋላ የማይሉ “ይሁዳዎችን” በመጠቀም የተለያዩ ሴራዎችን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ቆይተዋል።
ይህ ቡድን ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ በይፋ ጦርነት እስከከፈተበት ጊዜ ድረስ ብቻ ከ113 ጊዜ በላይ የሽብር ተግባራትን ማከናወኑን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸው ነበር። ይህ ቡድን እነዚህን ሁሉ የሽብር ተግባራት ሲያከናውን ታዲያ ሙሉ ለሙሉ ራሱ እየተሳተፈ ሳይሆን ግጭቶችን ስፖንሰር እያደረገ ጭምር ነው። ለዚህ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የሚተባበሩት ደግሞ ለገንዘብ ራሳቸውን የሸጡ ጥቂት ግለሰቦች ናቸው።
ይህ ብቻ አይደለም። አንድ እግራቸውን ከዚሁ ቡድን ጋር ያቆራኙ እና ሌላ እግራቸውን በመንግስት መዋቅር ውስጥ የወሸቁ ሃይሎች እንዳሉም በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚነሳ እውነታ ነው። እነዚህ ሃይሎች ደግሞ በተለይ ህዝብን በማማረር በተዘዋዋሪ መንገድ የነሱ ደጋፊ እንዲሆን የሚያደርጉ የጭቃ ውስጥ እሾኮች ናቸው። በንግዱ ማህበረሰብ ውስጥም በመሆን ንግዱን የሚያዛቡና ህዝቡ ሰላማዊ ህይወት እንዳይኖረው የሚሰሩ ሃይሎች እንዳሉም ይታወቃል። የነዚህ አካላት ዓላማም ተመሳሳይ ነው።
አሸባሪው ሸኔም ቢሆን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የማይፈነቅለው ድንጋይ፣ የማይምሰው ጉድጓድ የለም። ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን እንዳለው ሸኔም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለዘመናት ሲያሳድደው ከኖረው ሕወሓት ጋር ግንባር በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ብዙ ጥረት አድርጓል። ይህ ቡድን እታገልለታለሁ ላለው የኦሮሞ ህዝብ ላይ ጭምር በደልና ግፍ በመፈፀም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ብዙ ጥሯል።
በአጠቃላይ እነዚህ እጆች ዓላማ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ነገር ግን እነዚህ ሃይሎች ይህንን ለማሳካት የሚጠቀሙት ዘዴ ሌሎችን በማስተባበር እና በማወናበድ እንዲሁም በገንዘብ ሃይል በማታለል ከጎናቸው በማሰለፍ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ከዚህ ውጭ ግን እርቃናቸውን የቆሙ ናቸው። እርቃን የቆመ ቡድን ደግሞ ለደቂቃም ቢሆን ህልውና አይኖረውም። እናም እነዚህን ቡድኖች እርቃናቸውን በማስቀረት ከህዝብ መነጠል፤ በቀጥታ እነዚህን የሽብር ቡድኖች ለመፋለም እድሉን ባናገኝም የነዚህ ቡድኖች መጠቀሚያ ባለመሆን ሉአላዊነታችንን መጠበቅ ከሁላችንም ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014