መላው ኢትዮጵያውያንን ያስተሳስራል የተባለለት የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ውድድር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ በሐዋሳ ከተማ መካሄድ ይጀመራል። ይህ የወጣቶች ኦሊምፒክ ከግንቦት 21-ሰኔ 4/2014 ዓ.ም ድረስ የኦሊምፒክ ስፖርት በሆኑና ባልሆኑ ስፖርቶች ሲካሄድ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከቅርብ አመታት ወዲህ የሚካሄደው ይህ ትልቅ የስፖርት መድረክ 134 ሚሊዮን ብር የተበጀተለት ሲሆን ወጪውን ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንደሚሸፍን ታውቋል። ውድድሩ በተመሳሳይ በግብጽ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞች እንደሚመረጡበት ተገልጿል።
የውድድሩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ባለፈው ሳምንት በሸራተን አዲስ በሰጡት መግለጫ 6000 ወጣቶች በውድድሩ ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ይህ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ የኦሊምፒክ ስፖርት በሆኑና ባልሆኑ ስፖርቶች እንደሚካሄድም ተጠቁሟል።
በመግለጫ ላይ እንደተጠቆመው፤ ኮሚቴው ውድድሩ በሁሉም ስፖርቶች እንዲካሄድ ፍላጎት ቢኖረውም በአዘጋጁ ክልል ውስንነት የተነሳ ክልሉ በወሰነው መሠረት ውድድር የሚካሄድባቸውን ስፖርቶች የግድ ለመገደብ ተገደዋል። ያም ሆኖ በውድድሩ ከኦሊምፒክ ስፖርቶች አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ጅምናስቲክና ወርልድ ቴኳንዶ ፉክክር የሚደረግባቸው ሲሆን የኦሊምፒከ ስፖርቶች ባልሆኑት የቼዝ፣ የኢንተርናሽናል ቴኳንዶና ውሹ ስፖርቶች በሁለቱ ሳምንት ፉክክር መካተታቸው ታውቋል።
የውድድሩ መነሻ ሀሳብ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባኤ ጥር1/2014 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በግብጽ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ቻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ታስቦ መሆኑን የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ተናግረዋል። ወጣቶች አካባቢ የኦሊምፒክን መንፈስን ለማስረጽ፣በሀገር ግንባታ ላይ ትልቅ ሚና እንዲወጡ ማስቻል፣ ወጣቶች ታይተው ተሰጥዋቸውን ተረድተው በስፖርቱ በኩል ተተኪ እንዲሆኑ በማሰብ፣ ወጣቶቹ ሀገራቸውን ወክለው እንዲወዳደሩ እንዲሁም መልካም ገጽታ እንዲያሳዩ የህዝብ ለህዝብ የባህል ልውውጥ ለማድረግም ነው” በማለትም ፕሬዚዳንቱ የውድድሩን አላማ አስረድተዋል።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ፣ በርካታ የፕሮጀክት መመዘኛዎች የታዳጊ ፕሮጀክት የዕድሜ ማጭበርበር የበዛባቸው መሆኑ በተለይ አመራሮቹ ለሜዳሊያ ለዋንጫና ለሽልማት ፍላጎታቸው እየጨመረ ሄዷል። ይህ የዕድሜ ማጭበርበር ችግር በአርጀንቲና በተካሄደው የአለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በተካፈሉ ስፖርተኞች ላይም ተስተውሏል። እነዛ ስፖርተኞች አሁን የሉም፣ ያኔ የነበሩ እነሜሲና ሮናልዶ ግን አሁንም እየተጫወቱ ነው፣ የነበረውን የዕድሜ ማጭበርበር ችግር ለማጥፋት የተቻለንን እየሰራን ነው፣ ይሄን ችግር ለማስወገድ ውድድሩን ወደ ወጣቶች አካባቢ በተለይም ወደ ትምህርት ቤቶች፣ ወላጆች ወዳሉበት መስመር ማስገባት ይገባል” በማለት ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል።
በመግለጫው ላይ ወጣት ማለት ዕድሜው እስከ ስንት ያለ ነው? የሚለው ጥያቄ ለኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮቹ ቀርቦም “በኦሊምፒክ ውድድር መርህ ወጣት ማለት ከ15-18 አመት ዕድሜ ያለው ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህ የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት የሚኖር ሲሆን መጠኑንም በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርጉ አዘጋጆቹ ጠቁመዋል። በውድድሩ የጸጥታ ችግር እንደማይኖር የተገለጸ ሲሆን የዕድሜ ማጭበርበር እንዳይከሰት የኮሚቴው የህክምና ቡድን ከፍተኛ ስራ እንደሰራም ተጠቁሟል። በአዘጋጆቹ እንደተገለጸው ለዚህ ውድድር መሳካት አቢይና ንዑስ ኮሚቴ በማዋቀር ከፍተኛ ስራ የተሰራ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዳሽን ባንክን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ለውድድሩ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል።
የውድድሩ መክፈቻ ደማቅና የኦሊምፒክ ድባብ የሚታይበት እንዲሆን የኢ.ፌ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዲሁም ፕሬዝዳንቷ ሳህለወርቅ ዘውዴ በእለቱ ተገኝተው የወጣቶቹን ኦሊምፒክ መጀመር እንዲያበስሩ ፍላጎት እንዳላቸው የጠቆሙት አዘጋጆቹ፣ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ርችት በመተኮስና ትእዒት በማሳየት መክፈቻውን ለማድመቅ መስማማቱን በመጠቆም ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በተለይም ፕሬዘዳንቱ ዶክተር አሸብር “ውድድሩ በራሱ መልካም ገጽታ ያበረክታል፣ ውድድር መኖሩ በአለም ደረጃ የሚያስተላልፈው ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗንና ችግሯን እያለፈች እንደምትገኝ ነው፣ በዚህም ደስተኛ ነን፣ ውድድሩ በሰላም ለመጠናቀቁም ካለው የጸጥታ ሃይል በላይ አይሆንም” ሲሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከዚህ የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ውድድር ጀምሮ እስከ በግብጽ እስከሚካሄደው ድረስ 134 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡም ታውቋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ በየሁለት አመት እንዲካሄድ መወሰኑንም አስታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2014