ከስር መሠረታቸው ጀምረው በሥራ ላይ ብቻ አተኩረው አድገዋል። ገና የሦሥተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ በንግድ ሥራ ተጠምደው ነበርና አፍላ የልጅነት ጊዜያቸውን ጭምር ለንግድ ሥራ የሰጡ በመሆናቸው በቂ የልጅነት ጨዋታ ተጫውተው አድገዋል ለማለት አያስደፍርም።
የሦሥተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ የጀመሩትን የናፍጣ ንግድ አክብረውና አጥብቀው መያዝ በመቻላቸው ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንደሚባለው የንግድ ሥራቸው አድጎና ተመንድጎ የበዛ ፍሬ በማፍራቱ ዛሬ ላይ አንቱ የተባሉ ባለሃብት መሆን ችለዋል። በብዙ ልፋትና ጥረት ባገኙት ሀብትም ስመጥር የአገር ኩራት በመሆን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
በሥራቸው ስኬታማ ሆነው በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉት የዛሬው የስኬት እንግዳችን የሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ አወል ናቸው። አቶ ሙስጠፋ፤ ትህትናን ገንዘባቸው ያደረጉ፣ ሰው አክባሪና ታታሪ ናቸው። ገና ከድሮ ጀምሮ ለተራበ አጉራሽ ለታረዘ አልባሽ በመሆን ቤተሰብ፣ ዘመድና ጓደኛን በማገዝ ከእኔ ይልቅ እኛ በሚል ሕዝባዊ ስሜት መምጣታቸው ለዛሬ ስኬት ያበቃቸው ባህሪያቸው እንደሆነ በቅርብ የሚያውቋቸው ሁሉ ምስክርነት ይሰጣሉ።
አቶ ሙስጠፋ የተወለዱት በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ነው። የልጅነት ዕድሜያቸውን ጨምሮ ሰፊውን የሥራ ዘመናቸውን ያሳለፉት ግን በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን አረካ ነው። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ያቀኑ ቢሆንም የሶስተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ግን ዛሬ ላይ ለደረሱበት የስኬት ማማ ያበቃቸውን ለኩራዝ የሚውል የናፍጣ ንግድ ‹‹ሀ›› ብለው በመጀመር መሠረት ጥለዋል።
በወቅቱ ስምንት ብር ይዘው ለኩራዝ የሚውል ናፍጣ በታኒካ ወይም በባልዲ እያመጡ መነገድ የጀመሩት አቶ ሙስጠፋ፤ ጠበቅ አድርገው የያዙት የስምንት ብር የናፍጣ ንግድ 80 ብር፣ 80 ብሩ ደግሞ 160 ብር በመሆኑ ሥራቸው አድጎ ሱቅ መክፈት አስቻላቸው። ሱቅ ከፍተው ይህንኑ የናፍጣ ንግድ ሲያስቀጥሉ ታዲያ በታኒካ አልያም በባልዲ ያቀርቡት የነበረውን ወደ በርሜል በማሳደግ በአረካ ከተማ ቀዳሚ የኩራዝ ናፍጣ ነጋዴ ሆነዋል።
በወቅቱ በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ አፍላ የወጣትነት ጊዜ ላይ የነበሩ መሆናቸውን የሚያስታውሱት አቶ ሙስጠፋ፤ ከፍተኛና ውስጣዊ የሆነ የመሥራት፣ የማደግና የመለወጥ ጉጉትና ፍላጎት እንደነበራቸውም አጫውተውናል። ይሁንና ማንኛውም ወላጅ ልጁ ትምህርት ቤት እንዲውል የሚፈልግ እንደመሆኑ የአቶ ሙስጠፋ ወላጆችም ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ፍላጎታቸው ነበር።
በመካከለኛ ንግድ የተሰማሩት የአቶ ሙስጠፋ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ቢልኩም አቶ ሙስጠፋ ግን ከትምህርታቸው ጎን ለጎን አንዳንዴም ትምህርቱን ያዝ ለቀቅ እያደረጉ የናፍጣ ንግዳቸውን አሳለጡ። አቶ ሙስጠፋ የጦፈ ንግድ ውስጥ መሆናቸውን ያወቁት ወላጆቻቸው ብዙ ሳይቃወሟቸው ሥራቸውን አድንቀው አልፈዋል። በፍጹም ነጻነት ያሳደጓቸው ወላጆቻቸው በወቅቱ የስኬታማነት ጫፍ ላይ የሚያደርሳቸውን መሠረት እየጣሉ እንደሆነ በመረዳታቸው እጅጉን ደስተኞች ነበሩ።
በነበራቸው የሥራ ትጋት፣ ፍጥነትና ወኔ በተጨማሪም ፈጣሪም አግዞና ደግፏቸው ዛሬ ላይ እንደደረሱ የሚናገሩት አቶ ሙስጠፋ፤ በሂደት ከፍ ከፍ እያሉ በ16 ዓመታቸው ጥሩ የሚባል ገንዘብ መሥራት እንደቻሉና በዚሁ ዕድሜያቸው መኪና እንደገዙ ያስታውሳሉ። ታዲያ ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ጠንካራ ሴት አለች እንደሚባለው ባለቤታቸው ወይዘሮ ዘሀራም የንግድ ሥራቸውን በመደገፍ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው አቶ ሙስጠፋ ይናገራሉ።
የንግድ ሥራቸውን በማስፋፋት ወላይታ ውስጥ ከገዙት መኖሪያ ቤታቸውና መኪኖች በተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለማስፋፋትና ሃብት ለማፍራት ከ500 ሺ ብር በላይ ሀብት ማፍራት አይቻልም የሚለው የደርግ ሥርዓት ማነቆ ሆኖባቸው እንደነበር አስታውሰው፤ እንደልብ አላላውስ ብሎ አንቆ የያዛቸው የደርግ ሥርዓት ተወግዶ ኢሕአዴግ ሲገባ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በከፍተኛ ፍጥነት ተንቀሳቅሰው ኢንቨስትመንታቸውን በማስፋፋት ውጤታማ መሆን ችለዋል።
በወላይታና በአካባቢዋ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን ያቋቋሙት አቶ ሙስጠፋ፤ በዋናነት ቡና እንዲሁም ዝንጅብል አቅራቢ ሆነው በስፋት ተንቀሳቅሰዋል። ከቡና ምርታቸው ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውን አራት የቡና መፈልፈያ ፋብሪካም በአካባቢው አቋቁመው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ከቡናው ልማትና ግብይቱ ጎን ለጎንም ነዳጅ ማደያዎችን ከፍተዋል። በአካባቢው የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ቀዳሚ አልነበራቸውም።
‹‹ስልጤ ልወለድ እንጂ በፍቅር ተንከባክቦ ያሳደገኝ የወላይታ ሕዝብ ነው›› የሚሉት አቶ ሙስጠፋ፤ በበርካታ የንግድ ሥራቸው በሚታወቁበት ወላይታ አካባቢ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን ለኅብረተሰቡ በመሥራት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ለአካባቢ በሚሠሩት የልማት ሥራም ታዋቂነትን ከማትረፍ ባለፈ ተቀባይነትና ተደማጭነት አላቸው።
ፋብሪካዎቻቸው ባሉበት በወላይታ፣ በዲላና በአካባቢው ያገኙትን ከማኅበረሰቡ ጋር አብረው የሚቋደሱ እንደመሆናቸውም ትምህርት ቤቶችን በመገንባት፣ የገጠር መንገዶችና ድልድዮችን በማሠራት፣ አርሶ አደሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና ንጹህ የመጠጥ ውሃ በአቅራቢያው እንዲያገኝ አበክረው ሠርተዋል።
የጸና መሠረት የያዘውን የንግድ ሥራ ይበልጥ ለማስፋፋት ወደ አዲስ አበባ ባቀኑበት ወቅት በተለይም በቡና ምርት ቀዳሚ ሆነው ሠርተዋል። ያመረቱትን ቡናም በቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ አገሪቱ ከዓመት ዓመት እየተፈተነችበት ያለውን የውጭ ምንዛሪ ችግር በማቃለል ኢኮኖሚውን መደገፍ ችለዋል።
በአገር ኢኮኖሚ ላይ በሚያሳድሩት በጎ ተጽዕኖ ምክንያትም ከ20 ጊዜያት በላይ ተሸልመዋል። ሽልማቶቹን ያገኙት ከአገር ውስጥና ከውጭ አገራት ሲሆን ከሽልማቶቹ መካከል በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥራት ያለው የቡና ምርት በማቅረብ የወርቅ ስኒ መሸለማቸውና ከታች በመነሳት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ በመቻላቸው ከአስር ዓመታት በፊት የቡድን ስምንት (Group 8) አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ ተጋባዥ ሆነው ያገኙት ሽልማት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በግብርናው ዘርፍ ቡናን ከማምረት በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በቡና ልማታቸው እንዲሁም ብቸኛ በሆነው የጆንያ ፋብሪካቸው እና በተለያየ የሥራ ዘርፍ ከሁለት ሺ ለሚልቁ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉት አቶ ሙስጠፋ፤ በተጨማሪም ምርት በሚበዛበት ወቅት ከ2500 እስከ 3000 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር አጫውተውናል።
በአሁኑ ወቅት ስላለው የቡና ምርትና ግብይት በተመለከተም ብራዚል ላይ በተፈጠረው የአየር ጸባይ ምክንያት ዘንድሮ የኢትዮጵያ ቡና ዋጋ ከእጥፍ በላይ በመጨመሩ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደተቻለም ገልፀዋል። ‹‹በቀጣይም የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንዲቻልም ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን ጥራት ላይ አተኩሮ መሥራት የግድ ነው›› ይላሉ።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚያለሙትን የቡና ምርት በቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት አቶ ሙስጠፋ፤ በዋናነት የገበያ መዳረሻዎቻቸው የሆኑት አገራት ጃፓን፣ የአውሮፓ እንዲሁም የእስያ ሀገራት ሲሆኑ ቻይናም የቡና ገበያውን ተቀላቅላለች። ይህም ለቡና ገበያው የተፈጠረ መልካም ዕድል በመሆኑ በርትቶ መሥራት እንደሚገባና በተለይም አርሶ አደሩን መደገፍ ተገቢ እንደሆነ ይገልፃሉ። በተለይም የኢትዮጵያ ቡናን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ እንዲቻል አርሶ አደሩ ላይ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ።
አቶ ሙስጠፋ ‹‹ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች፣ ተስማሚ የአየር ንብረትና ለም መሬት ያላት በመሆኗ ብዙ ልንሠራ ይገባል። ዝናብ ብቻ ከመጠበቅ ባለፈም በመስኖም ማምረትና ገበሬው ዓመቱን ሙሉ ቡናውን ብቻ ከሚጠብቅ በቡና እርሻ ውስጥ የተለያዩ አትክልቶችን በማልማት በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ማሳካት ያስፈልጋል›› ብለዋል። ለዚህም ይርጋጨፌ በሚገኘው የቡና እርሻ አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ከኮሎምቢያ ባስመጧቸው ባለሙያዎች አማካኝነት በቡና ውስጥ የተለያዩ አትክልቶችን አምርተው እንዲጠቀሙ አድርገዋል።
ይርጋጨፌን ጨምሮ ሲዳማና ቦንጋ ላይ ቡናን በስፋት አምርቶ ለውጭ ገበያ በመላክ አራት አስርተ ዓመታትን ያስቆጠረው ሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ዘንድሮ ብቻ ስምንት ሺ ቶን ቡና ለመላክ ዕቅድ የነበረው ሲሆን በአስር ወራት ውስጥ ስድስት ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ አቅርቧል። ቀሪ ሁለት ሺ ቶን ቡና ደግሞ በቀጣይ ሁለት ወራት በመላክ ሙሉ ዕቅዱን ለማሳካት እየሠራ ነው።
የሶስት ሴትና የሶስት ወንድ ልጆች አባት የሆኑት አቶ ሙስጠፋ፤ ልጆቻቸውን እርሳቸው ባደጉበት ኢትዮጵያዊ በሆነ ስነምግባር አገር ወዳድ፣ ሰው አክባሪና ታታሪ ሠራተኞች እንዲሆኑ አድርገው ማሳደጋቸውን ይናገራሉ። ልጆቻቸው ትምህርታቸውንም በአገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የተማሩ ሲሆን፣ ሀገራቸውን የሚወዱና ባላቸው እውቀትና አቅም ተጠቅመው በሀገራቸው ሠርተው መለወጥና ማደግን የሚመኙ፤ አገራቸውን ለማሳደግ የሚጥሩ ስለመሆናቸውም ምስክርነት ሰጥተዋል።
የአባታቸውን ሥራ እየተመለከቱ ያደጉትና የቡናን ሥራ ጠንቅቀው የሚያውቁት ሁሉም ልጆቻቸው ታዲያ የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል በቡና ልማትና ግብይት ውስጥ ተቀላቅለው በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ። ሥራውን ጠንቅቀው በማወቃቸውና የከፍተኛ ትምህርት የተማሩ በመሆናቸውም ድርጅቱን በተሻለ መንገድ በዕውቀትና ቴክኖሎጂ እየመሩት እንደሆነ የገለጹት አቶ ሙስጠፋ፤ ካላቸው ነገር ሁሉ አብልጠው የሚወዱትና እጅጉን የሚኮሩት በእነዚሁ ልጆቻቸው እንደሆነ አጫውተውናል።
አቶ ሙስጠፋ አብዛኛው የሕይወት ዘመናቸውን በሥራ አሳልፈዋል። በተለይም ለ48 ተከታታይ ዓመታት በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተው በብዙ ልፋትና ጥረት ዛሬ ላይ ቢደርሱም ቅሉ ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ›› እንዲሉ ዛሬ ደግሞ ከአብራካቸው ክፋይ ከሆኑ ልጆቻቸው ጋር በመሆን ቤተሰባዊ አንድነትን ፈጥረው በጋራ በመሆን ተግባብተው፣ ተናበውና ተደጋግፈው ውጤታማ ሥራ በመሥራት ሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን እየመሩ ይገኛሉ።
ንግድ ሁልጊዜም ቢሆን ፈታኝ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሙስጠፋ፤ በየጊዜው የተለያዩ ፈተናዎችን በማለፍ እዚህ ቢደርሱም በንግድ ባሳለፉዋቸው 48 ዓመታት ውስጥ በአንድ ወቅት ምክንያቱ በማይታወቅ ጉዳይ ድርጅታቸው መዘጋቱንና ለሁለት ዓመት ተኩል ከሥራ ውጭ ሆነው እንደነበር ያስታውሳሉ። ምንም እንኳን ያ ጊዜ በሕይወታቸው ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ቢኖርም ንግድ ፈታኝ ነውና ፈተናውን ተቋቁመው በማለፍ የሕይወታቸው አንድ ክፍል የሆነውን የንግድ ሥራ አስቀጥለዋል።
በአሁኑ ወቅት ያሉ ወጣቶች ቴክኖሎጂው በሚያሳድረው ተጽዕኖ ጭምር በጣም ፈጣን እንደሆኑ የገለጹት አቶ ሙስጠፋ፤ በአቋራጭ መክበር እንደማይቻልና ሁሉም ነገር በትዕግስትና ቀስ በቀስ መሳካት እንደሚችል፤ እንዲሁም በጥድፊያና በችኮላ ከላብ ውጭ የሆነን ገንዘብ ለማግኘት የሚደረገው ሩጫና ጥድፊያ ሁሉ ፍጹም የማይጠቅም እንደሆነም መክረዋል።
ኢትዮጵያ ታላቅና ሀገር ስለመሆኗ የሚናገሩት አቶ ሙስጠፋ፤ በቀጣይም ይህችን ታላቅ ሀገር ወደ ከፍታ ለማድረስ ባላቸው አቅም ሁሉ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። በተለይም የውጪው ዓለም የማያጓጓቸው ልጆቻቸው ሥራውን በማስፋፋት የተለያዩ ፋብሪካዎችን በማቋቋም ሰፋፊ የሥራ ዕድል ፈጥረው አገራቸውን የማሳደግ ትልቅ ራዕይ ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም አጫውተውናል። እኛም ምኞታቸው ሰምሮ የሀገር ኩራት እንዲሆኑ በመመኘት አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2014