ኢትዮጵያ የበርካታ ወንዞች መፍለቂያና የሐይቆች መገኛ ብትሆንም፣ ዛሬም ድረስ ይህን የውሃ ሀብቷን ለመስኖ ልማት በሚፈለገው ልክ ተጠቅማ ግብርናዋን ማዘመን አልቻለችም። በመስኖ ልማት በአንዳንድ አካባቢዎች በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች ቢኖሩም፣ መስኖን ለሰብል ልማት በማዋል በኩል ሳይሠራበት ቆይቷል።
በመሆኑም ዛሬም ዝናብ ጠብቀው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች የሚገኙባት ሀገር ነች። በዚህም ምክንያት ዜጎች ለድርቅ፣ ለረሃብና ድህነት ተጋልጠው ይገኛሉ። ሀገሪቱ በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የማይችሉ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለማስገባት መጠቀም ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ለምግብ ሸቀጦችና ለግብርና ምርቶች ግዥ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ እና ለውጭ ገበያ መላክ የሚጠበቅባትን ምርቶች ጭምር ከውጭ ሀገራት ለማስገባት እየተጠቀመችበት ትገኛለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የመስኖ ልማትን በማስፋፋት ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር ጥረት ማድረግ ተጀምሯል፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተካሂደዋል፤ እየተካሄዱም ይገኛሉ። ሀገሪቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በበጋ መስኖ ልማት ስንዴ ማምረትም ጀምራለች። ዘንድሮም ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ወደ 17 ሚሊየን የሚጠጋ ኩንታል አምርታለች።
በሀገሪቱ የመስኖ ልማትን ማካሄድ የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተገነቡም ይገኛሉ። ግንባታቸው እየተካሄደ ከሚገኝ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል የታችኛው ርብ የመስኖ ልማት አንዱ ነው። የታችኛው የርብ የመስኖና ድሬኔጅ ፕሮጀክት በርብ ወንዝ ላይ ከተገነባው የርብ ግድብ ውሃ ከሚጠቀሙ የመስኖ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። የርብ የመስኖ ግድብ ግንባታን በአራት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ አስር ዓመታት ቆይቶ በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመረቀ ፕሮጀክት ነው።
የመስኖ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ቢመረቅም የአካባቢው አርሶ አደሮች መስኖን ለመጠቀም ሳይችሉ ቆይተዋል። ፕሮጀክቱ የመስኖ አውታር /ቦይ/ ስላልተሠራለት እስከ አሁን አርሶ አደሮቹ ከመስኖ ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አልሆኑም።
አርሶ አደሮቹ ከመስኖ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ በርብ ግድብ ላይ እየተገነቡ ካሉ የመስኖና ድሬኔጅ ፕሮጀክቶች አንዱ የታችኛው ርብ የመስኖና ድሬኔጅ ፕሮጀክት ነው። በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በደቡብ ጎንደር ዞን የሊቦ ከምከም እና ፎገራ ወረዳን የሚያዋስነው የታችኛው ርብ መስኖና ድሬኔጅ ፕሮጀክት ግንባታ ጥቅምት 2008 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። በአምስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞለት እንደነበር የመስኖና እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
በፕሮጀክቱ 3400 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከስድስት ሺህ በላይ የሚሆን የአካባቢውን አርሶ አደር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። የአካባቢው አርሶ አደሮች ዝናብን እየጠበቁ በዓመት አንድ ጊዜ ከማምረት በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ ለማምረት የሚያስችላቸው መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ብዙነህ ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ሕይወት ለመቀየር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ታምኖበታል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አቅራቢያ የሚገኙ አርሶ አደሮች በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ እንዲያመርቱ ያስችላቸዋል። አርሶ አደሮች ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲያመርቱና የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያስችልም ነው።
ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚያሠራው የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሲሆን በሥራ ተቋራጭነት የሚሠራው ደግሞ ሀገር በቀሉ አባይ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ነው። የማማከር ሥራውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በማከናወን ላይ ይገኛል።
የፕሮጀክቱን የግንባታ ወጪ የዓለም ባንክና የኢትዮጵያ መንግሥት ናቸው የሚሸፍኑት። በቅድሚያ የዓለም ባንክ ወጪውን እየሸፈነ እንደነበርና ፕሮጀክቱ መጓተቱን ተከትሎ ባንኩ ድጋፉን ማቋረጡን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ወጪውን የኢትዮጵያ መንግሥት እየሸፈነ ግንባታው እየተካሄደ መሆኑን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ብዙነህ ቶልቻ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ፤ የፕሮጀክቱ ዋነኛው ዓላማ የተጠቃሚውን ኅብረተሰብ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ የኑሮ ደረጃቸውን ማሻሻል ቢሆንም፣ ፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደት ላይ እያለም ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል ፈጥሯል። በፕሮጀክቱ ወንድ 137 ሴት 24 በጠቅላላ 161 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። በፕሮጀክቱ ላይ በመሥራት ለኑሯቸው አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ችለዋል።
ፕሮጀክቱን በ2013 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ቢታቀድም፣ በዚህ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሊጠናቀቅ ግን አልቻለም። በ2013 ሊጠናቀቅ ቀርቶ የ2014 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራትን ጭምር ፈጅቶ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ገና 83 በመቶ ላይ ይገኛል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት እቅድ መሠረት እንዳይጠናቀቅ ያደረጉ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን አቶ ብዙነህ ያብራራሉ።
እንደ አቶ ብዙነህ ገለጻ፤ ተቋራጩ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሠራ የሚያደናቅፉ የተለያዩ እንቅፋቶች አጋጥመዋል። ከችግሮቹ መካከል የወሰን ማስከበር ችግር አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ የሚገነባበት አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ ነዋሪዎች የፕሮጀክቱ ግንባታ በሚካሄድበት ቦታ ላፈሩት ንብረት የካሳ ክፍያ የተፈጸመላቸው ቢሆንም ከአካባቢው ለመነሳት ፈቃደኛ አልነበሩም።
ለመነሳት ፈቃደኛ ያልሆኑ ነዋሪዎችን ለማሳመን ብዙ ጊዜ ወስዷል። አንዳንዶቹ ደግሞ ንብረቱን ለማንሳት ፈቃደኝነታቸውን ቢገልጹም፤ የንብረት ካሳ ክፍያ ከተፈጸመላቸው በኋላ ንብረታቸውን እንዲያነሱ ቢነገራቸውም በተፈለገው ጊዜ ያለማንሳት ሁኔታ ታይቶባቸዋል። በዚህም ምክንያት ተቋራጩ የፕሮጀክቱን ግንባታ ሥራ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳያከናውን እንቅፋት ሆኖበት ቆይቷል።
የፕሮጀክቱ መጓተት የአካባቢው ነዋሪዎች በጊዜ ባለመነሳታቸው ምክንያት ብቻ የተፈጠረ አይደለም። ከካሳ ገማች አካል ጋርም ችግሮች ይስተዋሉ ነበር። የአንዳንዶቹ የካሳ ግመታ ቶሎ አልተሠራም። የካሳ ግመታ ቶሎ ካልተሠራ ደግሞ ለአካባቢው ነዋሪዎች ካሳ ከፍሎ ከቦታው ለማስነሳት አዳጋች እንደሚሆን እሙን ነው። በዚህም ምክንያት ቦታቸውን ለቀው ለመነሳት ረጅም ጊዜ የፈጀባቸው አሉ።
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በታዳጊ ሀገራት የመስኖ ግድቦችን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ኘሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ የማይጠናቀቁበትን ምክንያት ፕሮጀክቶችን ከአዋጭነት ጥናት ጀምሮ እስከ ማጠናቀቁ ድረስ የእቅድ እና የአተገባበር መንገዳቸው በውል ተለይቶ ስለማይቀመጥ መሆኑን የዓለም ባንክ በ2016/17 ያካሄደው ጥናት ያመለክታል::
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ የመስኖ ፕሮጀክቶች የአካባቢ አዋጭነት ጥናት ሳይካሄድ ወደ ግንባታ መግባት ለመስኖ ፕሮጀክቶች መጓተት አንዱ ምክንያት ነው። ወደ መስኖ ግድቦች የሚያደርሱ መንገዶች፣ መብራትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች አለመኖር እና በዚህ ምክንያትም የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች ይዘገያሉ።
ከመሠረተ ልማት አለመሟላት ባሻገር ለመስኖ ግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገው የአካባቢ ቁሳቁስ ማለትም ቀይ አፈር፣ ጠጠር፣ ድንጋይ፣… የመሳሰሉት የት እንደሚገኙ? በምን መንገድ ወደ ግንባታ ቦታው እንደሚጓጓዙም? በጥናት አለመለየት ለፕሮጀክቶች መዘግየት የአንበሳውን ድርሻ ሲይዙ ይስተዋላል። ሌላውና ለመስኖ ግንባታ መጓተት መሰናክል እየሆነ ያለው የገንዘብ /የበጀት/ እጥረት ነው:: ለግንባታው የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪም ሆነ ከመንግሥት የተመደበው ጥሬ ገንዘብ በወቅቱ ስለማይለቀቅም ለመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች መጓተት አንዴ ምክንያት መሆኑን ያመለክታሉ።
አቶ ብዙነህ እንደሚሉት ፤ ከዚህ ቀደም የታችኛውን ርብ መስኖ ፕሮጀክትን ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ የመስኖና ድሬኔጅ ፕሮጀክት ግንባታውን በበጀት ዓመቱ 20 ነጥብ 29 በመቶ በማከናወን አጠቃላይ ግንባታው በ2013 በጀት ዓመት መጨረሻ ከነበረበት 79 ነጥብ 71 በመቶ ፕሮጀክቱን 100 በመቶ ለማጠናቀቅ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ ነው።
ፕሮጀክቱን ሲያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጎደል የተፈቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የፕሮጀክቱ ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን አቶ ብዙነህ ይናገራሉ፤ በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ሰኔ 2015 ዓ.ም ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ፕሮጀክቱን ለማፋጠን የተለያዩ እርምጃዎችም ተወስደዋል። ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል ግንባታውን ሲያከናውን የቆየው የቻይና ተቋራጭ እንዲሰናበት ተደርጓል። አዲስ ሀገር በቀል ተቋራጭ እንዲሠራ ተደርጓል። ተቋራጩም አባይ የኮንስትራክሽን ድርጅት ነው። ይህ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው እርምጃ ነው። የተወሰደው የውጭ ምንዛሪ ለማትረፍ ከማገዙም ባሻገር በቀጣይ ሀገር በቀል ተቋራጮች አቅም እንዲጎለብት የሚረዳ ነው።
ሀገሪቱ ሁል ጊዜ የውጭ ተቋራጮችን እያስገባች የግንባታ ሥራዎችን እያከናወነች መቀጠል አዳጋች ነው። በቀጣይ ጊዜያት ሀገር በቀል ተቋራጮች ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም የሚገነቡበት አቅም ማጎልበት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በዚህ ረገድ ፕሮጀክቱ እንዲጓተት አንዱ ምክንያት ሆኖ የነበረውን የውጭ ተቋራጭ በማሰናበት ሀገር በቀል ተቋራጭ ሥራውን እንዲያከናውን መፈቀዱ መልካም እርምጃ ነው።
ሌላኛው የተወሰደው እርምጃ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ የተቀመጠበት ሁኔታ ነው። የክልሉ መንግሥት የበኩሉን እንዲወጣ እና የፌዴራል መንግሥትም የበኩሉን እንዲወጣ ከክልል አመራር ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ተደርሷል። አቅጣጫም ተቀምጧል። ከዚያ ባሻገር የታችኛዎቹ የመንግሥት መዋቅሮችም ለፕሮጀክቱ መፋጠን የማይተካ ሚና ያላቸው እንደመሆናቸው ይህንን ሚናቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ ተቀምጧል። ከዚያ በመነሳት ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን የፕሮጀክቱ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ፕሮጀክቱን በ2015 አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት እና ሀገሪቱ ከፕሮጀክቱ ማግኘት ያለባትን ጠቀሜታ ማግኘት እንድትችል የመሬት አቅርቦት ችግርን በመቅረፍ ለግንባታ ሥራ ዝግጁ ማድረግ ፣ ተቋራጩ የማሽነሪና የሰው ኃይል አቅርቦትን ሥራው በሚጠይቀው ልክ እንዲያቀርብ ማድረግ ያስፈልጋል። በተጨማሪም አርሶ አደሩ ስለ ዘመናዊ መስኖ ልማት ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በተከታታይ መሥራት ይገባል። አርሶ አደሩ ስለ ዘመናዊ መስኖ ልማት ያለው ግንዛቤ ከፍ ካላለ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ብቻ አርሶ አደሮችንም ሆነ ሀገሪቱን ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልም። ስለመስኖ ልማት ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ የመንግሥት መዋቅሮች እና የምርምር ተቋማት ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2014