በሳምንታዊው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1960ዎቹ የታተሙ ጋዜጦችን ለዚህ ሳምንት ተመልክተናል። የጅብ መንጋ በሰዎችና በቤት እንስሳት ስላደረሰው ጉዳት፤ በሐረርጌ አሁን ሶማሌ ክልል በምንለው በደገሀቡር አካባቢ አንድ ነጋዴ በ20ሺህ ብር የውሃ ገንዳ ማሠራታቸውና ይህም በአካባቢው የሚከሰተውን የውሃ እጥረትና ድርቅ ለመከላከል እንደሚረዳ በወቅቱ መናገራቸውን፤ ከጎረቤቱ በግ ሰርቆ ያረደ ግለሰብ ተከሶ ስለመቀጣቱ የሚያትቱ በወቅቱ የተሰሩ ዘገባዎችን ከሃምሳ ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ተመልሰን እንደሚከተለው ልናስታውስ ወደናል።
የጅብ መንጋ በረት ወርሮ ሰው ገደለ
ፍቼ፤(ኢ.ዜ.አ.) በሰላሌ አውራጃ በኩዩ ወረዳ በዳሮ ምክትል ወረዳ ውስጥ ኩዩ ከተባለው ቀበሌ ግንቦት ፰ ቀን የአቶ ሞቱማ ገሙን በበረት ውስጥ እንዳለ የወረረው የጅብ መንጋ አንድ ሰው ገድሎ ሲበላ በአምስት ሰዎች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው መሆኑን የኩዩ ወረዳ ግዛት ፖሊስ ጣቢያ ገለጠ።
በጅብ መንጋ ተወርረው የነበሩት አቶ ሞቱማ ገሙን ለመርዳት ከጎረቤት በቅድሚያ ለርዳታ የደረሱትን አቶ ጀንቢ ሂርጴ የተባሉትን የ፶ ዓመት አዛውንት የጅብ መንጋ ወዲያውኑ አደጋ አድርሶባቸው ከገደላቸው በኋላ ከጭንቅላታቸውና ከእጃቸው በስተቀር የቀረውን ሰውነታቸውን በሙሉ ከስክሶ የበላቸው መሆኑን ሁኔታውን የተከታተሉት የ፲ አለቃ ገብረ ማርያም ፎራ አስረድተዋል።
ከዚህም በቀር ብዛቱ ከ፳ በላይ የሆነ የጅብ መንጋ ፈለቀች ሲሳይና ኃይሉ ቱሉ፤ ፈዬ ራፎ፤ ቱሉ ብሩና አቶ ሞቱማ ገሙን ነክሶአቸው በከባድ ሁኔታ ስላቆሰላቸው በገብረ ጉራቻ ክሊኒክ ተኝተው በሕክምና በመረዳት ላይ ይገኛሉ።
የአካባቢው ሕዝብ በማግስቱ ግንቦት ፱ ቀን ከጅብ መንጋ የተረፈውን የአቶ ጀንቢ ሂርጴን አስከሬን በቀበሌው ቤተ ክርስቲያን ቀብረው ሲመለሱ አንድ ጅብ ቀን ፯ ሰዓት ላይ በመንገድ ላይ አድፍጦ ከቀብር በሚመለሰው ሰው ላይ በድጋሚ አደጋ ለማድረስ ሲሞክር በጥይት ተመትቶ ሞቷል።
በዚሁ ጊዜ የጅቡ ሆድ ተቀድዶ ቢታይ ልዩ ምልክት ያለበት የሟቹ አስከሬን ከጅቡ ሆድ ውስጥ ተገኝቶ እንደነበር የክፍሉ ፖሊስ ጣቢያ በተጨማሪ አረጋግጧል።
የአገሬው ሕዝብ ይህን ከባድ አደጋ ያደረሰውን የጅብ መንጋ ለማጥፋት በማደን ላይ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል።ከኩዩ ፖሊስ ጣቢያ የደረሰን ሪፖርት እንደሚያመለክተው ግንቦት ፰ ቀን ለዘጠኝ አጥቢያ እኩለ ሌሊት ላይ ብዛታቸው ከአምስት የማይበልጡ ጅቦች የአቶ ሞቱማ ጋሙን የከብት በረት ሰብረው ከብቶቹን መብላት ጀመሩ።ከዚያም የከብቶቹ ባለቤት አቶ ሞቱማ ከብቶቻቸውን ለማስጣል የመከላከል ሙከራ ሲያደርጉ ጅቦቹ በመተባበር የአሁኑ ሰው ሁለት እጆቻቸውንና ታፋቸውን በመንከስ አቆሰሉዋቸው። ከዚያም ጅቦቹ በበረት ውስጥ የሚገኙትን ከብቶች በየተራ እየቦጨቁ በመጣል መብላት ቀጠሉ።በዚህም ሰዓት ሟቹ አቶ ጀንቢ ሄርጶና ሌሎችም ጐረቤቶች ሁኔታውን ሰምተው ለርዳታ ሲደርሱ እንደገና ፲፭ ጅቦች ከመጀመሪያዎቹ አምስት ጅቦች ጋር ሁነው ሰዎቹን ያለፍርሃት በመብላት በአንድ ሰው ላይ የሞት አደጋ ሲያደርሱ የቀሩት አምስት ሰዎች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ ማድረሳቸውን ኩዩ ፖሊስ ጣቢያ አረጋግጧል። (ግንቦት 13 ቀን 1960 ዓ.ም አዲስ ዘመን)
ነጋዴው በ፳ ሺህ ብር የውሃ ገንዳ ሠሩ
ጅጅጋ፤(ኢ.ዜ.አ.) በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በደገሀቡር አውራጃ በአዋሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ወልደዮሐንስ የተባሉ ነጋዴ በ፳ ሺ ብር ፳፫ ጫማ ስፋት ያለው አንድ የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ አሠሩ።
አቶ ተስፋዬ ይህንን የማጠራቀሚያ ገንዳ ለማሠራት ያቀዱበት ምክንያት ሲያስረዱ፤በአዋሬ ከተማና በአካባቢው የውሃ እጥረት በመኖሩ አንዳንድ ጊዜ ድርቅ በሚሆንበት ወቅት አንድ በርሜል ውሃ ከ፲ ብር በላይ ስለሚሸጥ ይህንን የመሰለውን ችግር በኗሪዎቹ ላይ በመድረሱ ችግሩን ለመቋቋም ይረዳል ብዬ ነው ብለዋል።
ይህ አዲስ የተሠራው የማጠራቀሚያ ገንዳ ፩፻፫ ጫማ ርዝመት ፳፫ ጫማ ስፋት ፲፪ ተኩል ጫማ ጥልቀት ያለው ሲሆን ፤የማጠራቀሚያ ክፍል ደግሞ ፳ ጫማ ርዝመት ፳ ጫማ ስፋትና ፰ ጫማ ጥልቀት አለው። በዚሁ መሠረት ፲፯ ሺ ኪዩቢክ በርሜል ውሃ ለማጠራቀም የሚችል መሆኑ ታውቋል። (ግንቦት 13 ቀን 1960 አዲስ ዘመን)
በ፩ በግ ስርቆት ዓመት ከስድስት ወር እስራት
ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ፡- ገብሬ አሻሜ የተባለው ሰው አንድ ዳለቻ ወጠጤ በግ ሰርቆ በማረዱ በመናገሻ አውራጃ ፍርድ ቤት ዓመት ከስድስት ወር እንዲታሰር ተፈርዶበታል።
ገብሬ ይህን ተግባር የፈጸመው በመናገሻ አውራጃ በአዲስ ዓለም በገነት ከተማ ሲሆን ፤በጉም አቶ ነጋሽ ማሞ የተባሉት ሰው ነው። ገብሬ ከአቶ ነጋሽ የሰረቀውን በግ ከቤቱ ወስዶ ሲያርድ የበጉ ድምጽ በመሰማቱ የበጉ ባለቤት ጎረቤት በመሆናቸው ሰምተው ከሌሎች ሰዎች ጋር ደርሰውበት ሊይዙት ችለዋል ሲሉ የ፲ አለቃ በቀለ ማሞ መናገሻ አውራጃ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ባልደረባ ገልጸዋል። (ግንቦት 29 ቀን 1960 አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2014