ትምህርት ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ መሰረት ነው።በትምህርት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው የሰሩ አገራትም የብልጽግና ማማ ላይ ወጥተዋል።የዜጎቻቸውን ሕይወትም በልዩ ልዩ መልኩ አሻሽለዋል።አሁንም የበለጠ ስኬት ለማምጣት ዛሬም በማያቋርጥ ኡደት ውስጥ ይተጋሉ።
ኢትዮጵያም ለትምህርት ትኩረት ሰጥታ ትገኛለች።ቀደም ሲል በነበሩት አመታትም በተለይ ትምህርትን ለዜጎች ለማዳረስ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ አድርጋ ስትሰራ ቆይታለች።አሁን ደግሞ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች።ሆኖም ይህ ገና ጅምር ነውና በቀጣይ የሚጠበቀው ለውጥ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል።
በተለያዩ ዘርፎች ከወረዳ እስከ ሚኒስቴር ደረጃ ባሉ መዋቅሮች ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ የክልልና የፌደራል መንግስት ተቋማት የ2014 ዓ.ም የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀማቸውን ገምግመዋል።በግምገማቸው ወቅትም በዘጠኝ ወር የስራ እንቅስቃሴያቸው የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለይተዋል።የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት በቀሩት ጥቂት ወራቶች ውስጥ ጠንካራ አፈፃፀማቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠል፤ የታየባቸውን ደካማ አፈፃፀም ደግሞ ለማሻሻል የቀጣይ አቅጣጫም አስቀምጠዋል።
ከነዚህ ተቋማት ውስጥ አንዱ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሲሆን የ2014 ዓ.ም የዘጠኝ ወር እቅድ አፈፃፀሙን በቅርቡ ገምግሟል።በግምገማው ወቅትም በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ አብዛኛዎቹን በእቅድ የያዛቸውን ተግባራት መፈፀም ችሏል።በአብዛኞቹም ጠንካራ አፈፃፀም አሳይቷል።ክፍተት ናቸው ያላቸውን ተግባራትን ለይቶ በቀጣይ ለማስተካከል አቅጣጫም አስቀምጧል።
ዶክተር ገላና ወልደሚካኤል የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት ቢሮው በ2014 ዓ.ም የዘጠኝ ወር አፈፃፀም በርካታ ተግባራትን በጥንካሬ ገምግሟል።ከነዚህ ውስጥ አንዱ የትምህርት እድልን ከማዳረስ አንፃር የተሰራው ስራ ሲሆን በዘጠኝ ወራት ውስጥ በክልሉ በተለይ በገጠራማው አካባቢ ወደ 3 ሺ የሚሆኑ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተሰርተውና መምህራን ሰልጥነው ስራ ጀምረዋል።በተመሳሳይ በመደበኛ ትምህርት ዘርፍም ከተማሪዎች ምዝገባ ጀምሮ በርካታ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆንም የአካባቢው ሰላም እንዲጠበቅና ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ በመቻሉ የተለያዩ የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ተደርጓል።
በዚህም ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ከአምናው በጀት አመት በእጥፍ ጨምረዋል።አምና ከ500 እና 600 በላይ ያመጡ የተማሪዎች ብዛት 152 የነበረ ሲሆን በዘንድሮው በጀት አመት ግን ቁጥሩ ወደ 226 ከፍ ብሏል።ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱም ይህ ለውጥ ሊመጣ ችሏል።እንደአገርም ያለው ተሳትፎ ጨምሯል።ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድል ካገኙ ተማሪዎች ወደ 52 ከመቶ ያህሉን ተማሪዎች አስተዋፅኦ ማድረግም ተችሏል።ይህም እንደ ትልቅ ለውጥ የሚታይና በጥንካሬ የተገመገመ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የፕሮጀክት አፈፃፀምን በሚመለከት የክልሉ ትምህርት ቢሮ በእጁ ላይ ያሉ ሁሉንም ፕሮጀክቶች በዘጠኝ ወር ውስጥ አጠናቆ ትምህርት እየተሰጠባቸው ይገኛሉ።በተለይ ደግሞ ደረጃቸው ከፍ ያሉ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግም ተችሏል።ይህም እንደክልልም ሆነ እንደአገር ፕሮጀክቶችን በሰባትና በዘጠኝ ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ትልቅ ልምድ የተወሰደበትና ውጤታማ ስራ የተሰራበት ነው።
በዚሁ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሰባት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተሰርተው ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ ይገኛሉ።ይህም በክልሉ የሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር ወደ ዘጠኝ አሳድጎታል። በዚህም በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑ ተማሪዎች በነዚህ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ገብተው የመማርና ውጤታቸውንም የማሻሻል እድል አግኝተዋል።በቀጣይም ክልሉንም ሆነ አገሪቱን በተለያየ መልኩ በሞያቸው ሊገለግሉ የሚችሉና የሚመሩ ተማሪዎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ መገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
እንደ ምክትል ኃላፊው ገለፃ ቀደም ሲል በነበሩት አመታት በክልሉ ትምህርት ቤቶች የብጥብጥና የረብሻ ማእከላት ነበሩ።ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ትምህርት ቤቶች የሰላም ማእከላት እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።መምህራኖችና ተማሪዎችም ትምህርት ቤቶቹ ሰላማዊ የመማርና የማስተማር ሂደት እንዲከናወንባቸው የተደረገው አሰራር ትልቅ ውጤት አምጥቷል።የተማሪዎች ውጤት ተሻሽሏል፤ መምህራንና የትምህርት አስተዳደሮችም በዚህ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።የክልሉ መንግስት መዋቅሮችም ትምህርት ቤቶች የሰላም ማእከል እንዲሆኑ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል።
እነዚህ ውጤቶች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሊከናወኑ የቻሉትና ሰላማዊ የትምህርት አካባቢ መፍጠር የተቻለው በመምህራን፣ አስተዳደር ሰራተኞችና በክልሉ መንግስት በኩል ጠንካራ ቁርጠኝነት በመኖሩ ነው።ለአብነትም የአዳሪ ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች መደበኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመስራት ተነሳሽነቱ የመንግስት ነው።ጥሩ በጀት መድቦ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉና በትምህርት ላይ ለውጥ ካልመጣ በአገር ላይ ለውጥ አይመጣም የሚል ትልቅ ቁርጠኝነት በመንግስት በኩል አለ።በተመሳሳይ በትምህርት ቢሮው በኩልም ተመሳሳይ ቁርጠኝነት በመኖሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ጠንካራ አፈፃፀም ማሳየት ተችሏል።
ትምህርት የሁሉም ዘርፎች ትኩረትና የሁሉም ማህበረሰብ አጀንዳ እንዲሆን ቢሮው ከፍተኛ ስራዎችን ሰርቷል።3 ሺ የሚሆኑ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች የተገነቡትም በማህበረሰቡ የነቃ እንቅስቃሴ ነው።በዚህ ረገድ የክልሉ መንግስት የትምህርት ቢሮን መዋቅር በማስተባበር ትልቅ ስራ አከናውኗል።ማህረሰቡ ትምህርት የራሱ ስራና አጀንዳ እንደሆነ እንዲረዳም አድርጓል።
ምክትል ኃላፊው እንደሚሉት በጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት አፈፃፀም በድክመት ሁለት ነገሮች ተለይተዋል።አንደኛው የጎልማሶች ትምህርት ሲሆን በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ጎልማሶችን ለማስተማር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ለማስተማር የተቻለው 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ያህሉን ብቻ ነው።እንደአገር ይህን ያህል ቁጥር ያለው ጎልማሳ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ተምሮ አያውቅም።ሆኖም ከተቀመጠው እቅድ አንፃር አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ነው።ከባለፉት አመታት ጋር ሲነፃፀር ግን አፈፃፀሙ የሚናቅ አይደለም።
ሁለተኛው ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች መጠነ ማቋረጦች አጋጥሟል።ለምሳሌ በቆላማዎቹ የኦሮሚያ ዞኖች አካባቢ የተከሰተው ድርቅ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ አስገድዷል።በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች አልፎ አልፎ የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮችም ለመጠነ ማቋረጡ መጨመር የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።ነገር ግን በእነዚህ ምክንያቶች ትምህርት ካቋረጡ ተማሪዎች ውስጥ 80 ከመቶ ያህሉ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል።
ይህ ቋሚ ስላልሆነና ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋረጡ ተብሎ አመቱን ሙሉ ተግቶ የሚሰራበት ሳይሆን ሁኔታዎች ሲሻሻሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው እየተመለሱ መምህራንም የማካካሻ ትምህርት እየሠጧቸው ይገኛሉ፡፡
ከነዚህ ድክመቶች በመነሳት በቀጣይ አምና 3 ሚሊዮን ጎልማሶችን ለማስተማር በቀጣዩ በጀት አመት ወደ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጎልማሶችን ለማስተማርና በዚህ ረገድ የታየውን ክፍተት ለመሙላት እቅድ ተይዟል።በክልሉ የተለያዩ ሴክተሮችን በማቀናጀትና በማሳተፍ የጎልማሶችን ትምህርት ለማጠናከረም ታስቧል።
በተለይ ደግሞ ይህን ችግር ከስሩ ለመፍታት ትምህርቱ ራሱን ችሎ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሊሰሩት በሚችሉበት መልኩ አዲስ ስርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶለት ታትሟል።አዳዲስ የማስተማሪያና የስልጠና ማንዋሎችም ተዘጋጅተዋል።
በጎ ፍቃደኞችን በመጠቀም ትምህርቱን በዘመቻ መልክ እንዲያስተምሩና ትምህርት ቤቶች ደግሞ ራቅ ስለሚሉ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ጣቢያዎችን በማስፋትና ለሁሉም እንዲዳረስ በማድረግ ለጎልማሶች ቅርብ በሆነ ቦታ ላይ ትምህርት እንዲሰጥ በማድረግ ቀደም ሲል የነበረውን ችግር ለማቃለል ዕቅድ ተይዟል።
ቅድመ ማቋረጥን በሚመለከት የፀጥታ ችግር ከዚህ አመት ይዘላል ተብሎ የማይታሰብ በመሆኑና የድርቁ ሁኔታም እየቀነሰ በመምጣቱ ትምህርት አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመላሳሉ ተብሎ ይበቃል።
በሌላ በኩል ደግሞ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎችን ለማቆየት የምገባ ፕሮግራም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።ከዚህ ቀደምም በተለይ በቆላማ አካባቢዎች ከ700 ሺ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በምገባ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል።ይህንኑ የምገባ ፕሮግራም በማስፋት በቅድመ መደበኛ የሚማሩ ተማሪዎች ሁሉ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች እንዲመጡና የመጡትም በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲቆዩ ለማድረግ እቅድ ተይዟል።
ምክትል ኃላፊው እንደሚገልፁት በትምህርት ዘርፉ በተቻለ መጠን በክልልም ሆነ በአገር ደረጃ ለውጥ እየመጣ ነው።በተለይ ትምህርትን በማዳረስ በኩል ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል።ይህም የክልሉን ትምህርት አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ነው።ጥራትን በማስጠበቅ በኩልም እየተደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍ እያለ መጥቷል።
በተለይ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአይ ሲ ቲ እንዲደገፉ ተደርገዋል።በአብዛኛው ከተለመደው ወጣ ያለ ዝግጅትም ተደርጓል።በአዳሪ ትምህርት ቤቶችም ተጨማሪ ካሪኩለሞች ገብተዋል።ለአብነትም በሁሉም አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከእንግሊዝኛና ኦሮሚኛ ቋንቋዎች በተጨማሪ የአረብኛ፣ ፈረንሳይኛና ቻይንኛ ቋንቋም ይሰጣል።ይህም የተማሪዎችን የትምህርት ፍላጎት ጨምሯል።ወደፊትም ተማሪዎች በአገር ውስጥ ያላቸውን ተወዳዳሪነትም ያሰፋል።
የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የጋራ ቋንቋዎችን ይናገራሉ።ከዚህ አንፃር ለኦሮሚያ ተማሪዎች የሱማሌ ቋንቋ፤ ለሶማሌ ተማሪዎች ደግሞ የኦሮሞ ቋንቋ ይሰጣል።በተመሳሳይ በሲዳማና አፋር የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይም የጋራ ቋንቋዎች ለተማሪዎች ይሰጣሉ።አማርኛ ቋንቋም እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ ክልሉ በበጀት አመቱ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ በመነሳት በጠንካራ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2014