ዓለም በልዩነት ከሚያውቃቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አንዷ በቆጂ ናት። ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስኬት የጀርባ አጥንት የሆኑ እንቁ አትሌቶች ከዚህች ትንሽ ከተማና አካባቢዋ ፈልቀው ዘመን የማይሽረው ታሪክ ሰርተዋል። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ ከሰበሰበቻቸው 58 ሜዳሊያዎች መካከል 18 የሚሆኑት ሜዳሊያዎች(10የወርቅ፣ 3 የብር እና 5 የነሃስ) ከዚህ ስፍራ በተገኙ አትሌቶች የተሰበሰቡ ናቸው። ይህ ቁጥር በቆጂን እንደ አንድ አገር ብናስባት ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ በዘለቀው የኦሊምፒክ ታሪክና አጠቃላይ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ከዓለም 59ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል። በኦሊምፒክ መድረክ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተሳትፎ ታሪክ ያላቸው ከስልሳ በላይ አገራት አንድም ሜዳሊያ ባላገኙበት ሁኔታ በቆጂ እንደ አንድ አገር ታሳቢ ብትደረግ እንደ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኢንዶኔዢያና ሌሎች በርካታ የዓለማችን ታላላቅ አገራት ያላገኙትን ደረጃና ክብር በማግኘቷ ዓለም ‹‹የሯጮች ምድር›› ብሎ ቢጠራት አይገርምም።
በቆጂ ተፈጥሮ ያደላት ለሩጫ ምቹ የሆነ የአየር ፀባይዋ ከመልካ ምድሯ አቀማመጥና የነዋሪዎቿም አትሌቲክስ ባህል የማድረግ ዝንባሌ ለኢትዮጵያ መልካም ገጽታ ግንባታ በረከት ሆኗል። ይሁንና ይህች የሯጮች ምድር ባለፉት ዘመናት እንዳበረከተቻቸው በርካታ ወርቃማ ኦሊምፒያን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተተኪዎችን በማፍራት ረገድ መዳከም እያሳየች እንደምትገኝ መታዘብ ይቻላል። በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከምታስመዘግበው ውጤት በመነሳትም በቆጂ እንዳላት እምቅ አቅምና ባለፉት ዘመናት እንዳፈራቻቸው ብርቅየ አትሌቶች አንፃር በመጣችበት ፍጥነት እየተጓዘች ነው ለማት አያስደፍርም። ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑና የአካባቢው ነዋሪዎችም ይህንን ቁጭት ይጋሩታል።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ከሆነችው አንጋፋዋ አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ አንስቶ እንደ ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለና ስኬታማው የዲባባ የአትሌቲክስ ቤተሰብ እንዲሁም እስከ አሁን ድረስ በርካታ ውጤታማ አትሌቶችን ከትምህርት ቤቶች በመመልመል ከሚታወቁ አሰልጣኞች መካከል አንዱ ስንታየሁ እሸቱ ናቸው። እኚህ አሰልጣኝ በአሁኑ ወቅት በበቆጂ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የረጅም ርቀት አሰልጣኝ በመሆንም እየሰሩ ይገኛሉ። የውጭ አገራት ዜጎች ጭምር ስራቸውን በዘጋቢ ፊልም በመቅረጽ ለዓለም ያሳዩላቸውና ለበርካታ አትሌቶች መሰረት የጣሉት አሰልጣኝ ስንታየሁ በሯጮቹ ምድር አሁን አሁን ወደ ስፖርቱ የሚሳቡ ታዳጊዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን እንዳስተዋሉ አልሸሸጉም።
ቀደም ባለው ወቅት ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያሰለጥኑላቸው አምጥተው እስከመስጠት ይደርሱ እንደነበር የሚያነሱት አሰልጣኙ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ዓይነቱ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን ነው የሚጠቁሙት። ለዚህ ደግሞ አንድም ከወቅቱ ጋር የተያያዘው ሁኔታ ተጽእኖ በማሳደሩ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር አካባቢው ቀድሞ እንደነበረው እንጂ አበረታችና አትሌቶችን ሊያነሳሳ የሚችል ነገር አለመኖሩም ለዚህ ሚና እንዳለው ያስረዳሉ። በእርግጥ በማዕከሉ የሚሰለጥኑ ታዳጊዎች በየዓመቱ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የትጥቅ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ነገር ግን እንደ አጠቃላይ ከተማዋ ውስጥ ያለው ሁኔታ አትሌቶችን ሊያበረታታ የሚችል አለመሆኑን አሰልጣኙ ይናገራሉ።
በቅርቡ የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር የጀመረው በቆጂን የአትሌቲክስ ስፖርት ማዕከል ማድረግ እንዲሁም በየዓመቱ በከተማዋ ውድድር ማካሄዱ ታዳጊዎችን የማነቃቃትና የመሳብ አንዱ መንገድ ሊሆን እንደሚችልም አሰልጣኝ ስንታየሁ ይጠቁማሉ። ከዚህ ጎን ለጎን በስፖርቱ ላይ የሚሰሩት መንግስታዊ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ዳግም በቆጂን የኦሊምፒክ ሜዳሊያዎች መፍለቂያ ማድረግ እንደሚቻል ያስባሉ።
የበቆጂ ፍሬ የሆነችው አትሌት መሰረት ሂርጳ፤ በማሰልጠኛ ማዕከሉ አልፋ አሁን የቢሾፍቱ ከተማ አትሌቲክስ ክለብ አትሌት ለመሆን በቅታለች። አትሌቷ በቱሪዝም ሚኒስትርና ታላቁ ሩጫ በተዘጋጀው የ7ኪሎ ሜትር ሩጫ ተሳትፋ በአሸናፊነት ነበር ያጠናቀቀችው። ተወልዳ ባደገችበት በቆጂ ሌሎች አትሌቶችን በመመልከት ወደ ስፖርቱ ብትገባም አሁን ላለችበት ደረጃ ለመብቃት በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማሳለፏን ታስታውሳለች። አትሌቶች በራሳቸው ጥረት ካልወጡ በቀር የትጥቅ እና የስልጠና ሁኔታ አለመመቻቸት እንዲሁም ድጋፍ ማጣት አሁንም ድረስ በቆጂ ወርቃማ ኦሊምፒያንን በብዛት እንዳታፈራ እንቅፋት መሆናቸውን ትናገራለች። በዚህም ምክንያት ከቀድሞ አንጻር የአትሌቶች ቁጥር መቀነስ እያሳየ ነው። በመሆኑም በሌሎች አገራት አትሌቶች የሚደረግላቸው ድጋፍ በቆጂ ላይም ቢደረግ ችሎታ ያላቸው ምርጥ አትሌቶችን በብዛት ማፍራት እንደሚቻልም እምነት አላት።
ወጣት ብሩክ ከድር የበቆጂ ከተማ ነዋሪ ሲሆን፤ በቆጂ እንደ ወርቃማ አትሌቶች ምንጭነቷ ትኩረት ያላገኘችና መሰረተ ልማትም ያልተሟላላት ከተማ መሆኗን ይገልጻል። የማሰልጠኛ ማዕከላትንና አካዳሚዎችን በመገንባት ስፖርቱን ማበረታታት ባለመቻሉ ስፖርቱ የመቀዛቀዝ አዝማሚያ እያሳየ እንደሚገኝም ያስቀምጣል። ይህን ሁኔታ በተለያየ ጊዜ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ ቢሞከርም በቆጂ እንደ አትሌቲክስ ምንጭነቷ መቀጠል ሳትችል ቀርታለች። ‹‹እንደ አገር በትልልቅ ውድድሮች ውጤት ለማጣት ምክንያት ከሚሆኑት መካከል አንዱ የበቆጂ አትሌቶችን አለማፍራት ነው›› የሚለው ወጣቱ፣ በቱሪዝም ሚኒስቴር የተጀመረውን ዓይነት በአካባቢው ስፖርቱን የማነቃቃት ስራ በማስፋትና ለስፍራው ይበልጥ ትኩረት በመስጠት መፍትሄ ማምጣት እንደሚቻል አስታውቋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2014