አዲስ አበባ፡- አራተኛው አገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ ጊዜ መራዘም በቀጣይ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ምርጫ ወሳኝ ቢሆንም ስጋትም ያለው መሆኑን አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው ፓርቲዎች ገለፁ።
የፓርቲዎቹ አመራሮች እንደገለፁት፤ መጋቢት መጨረሻ ላይ ለማካሄድ ታስቦ የነበረውና ብዙ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ጊዜ መራዘም በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመስርቶ እንዲከናወንና ተዓማኒነት እንዲኖረው ወሳኝ ሚና አለው። በሌላ በኩል ግን በቆጠራው ምክንያት ምርጫው ከተራዘመ አገሪቱን በህዝብ ያልተወከለ መንግሥት እንዲመራ በማድረግ ለተጨማሪ ቀውስ ምክንያት ይሆናል።
የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት እንደተናገሩት፤ አገሪቱ አሁን ካለችበት የፖለቲካ ቀውስ አኳያ በተለይም በርካታ ህዝብ ከመኖሪያ ቀየው በተፈናቀለበትና ለረሃብ በተዳረገበት ሁኔታ ትልቅና አገራዊ ትርጓሜ ያለውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ማካሄዱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። በዋናነትም መንግስት የህዝቡን ደህንነት በአግባቡ ማስጠበቅ ባልቻለበት ወቅት ቆጠራውን በአግባቡ ለማድረግ አዳጋች ስለሚሆን ለተጨማሪ አገራዊ ብጥብጥ ምክንያት ይሆናል።
«በተረጋጋና በተደራጀ ሁኔታ ቆጠራውን ማካሄዱ ተጨባጭና ተዓማኒ አገራዊ መረጃ ለማግኘት ያስችላል፤ ይህም ህዝቡን ማዕከል ያደረገ አማራጭ ፖሊሲ ይዘን በምርጫው እንድንወዳደር ያስችለናል» የሚሉት ኢንጅነር ይልቃል፣ ከዚህም በላይ ግን እያንዳንዱ ፓርቲ የህዝብ ውክልናው መጠን በእውነታ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
በተጨማሪም የምርጫውን ጊዜ ወደ ፊት መግፋቱ የማይቀር በመሆኑ ፓርቲዎች በቂ ዝግጅት አድርገው ወደ ውድድር ሜዳው እንዲገቡ ብሎም መንግሥት ሰላምንና ፀጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያስከብር ጊዜ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱን ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታ በመገንዘብ የህዝብና ቤት ቆጠራው እንዲራዘም የቀረበውን ሃሳብ ሊያፀድቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ የአመራር አባል አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፤ የህዝብና ቤቶች ቆጠራውም ሆነ የምርጫው ጊዜ መራዘም ህገመንግስታዊ ጥሰት የሚያስከትል ከመሆኑም ባሻገር አገሪቱን ለተጨማሪ ፖለቲካዊ ቀውስ ሊዳርጋት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አመልክተዋል።«በአሁኑ ወቅት በአገራችን በርካታ ጉዳዮች ህገመንግሥቱን በጣሰ መልኩ እንዲተገበሩ እየተደረጉ ነው። ለአብነት የአካበቢ ምርጫን ብናነሳ በየአምስት ዓመቱ ሊካሄድ ሲገባው እስካሁን አልተካሄደም፤ በተመሳሳይ የህዝብና ቤቶች ቆጠራም በ2009 ዓ.ም መካሄድ ሲገባው ለሁለት ዓመት ተራዝሞ ቆይቷል» ብለዋል። አሁንም ተጨማሪ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ ህገመንግሥታዊ ጥሰት ከመሆኑም ባሻገር ይህንን የማድረግ መብትም ማንም አካል እንዳልተሰጠው አስረድተዋል።
አንዳንድ አካላት እንደምክንያት የሚያቀ ርቡት የህዝቦች መፈናቀልና አለመረጋጋት መቼ እንደሚፈታ እርግጠኛ መሆን ባልተቻለበት ሁኔታ ቆጠራውንም ሆነ ምርጫውን ማራዘም ተገቢ አይደለም ሲሉ የሚከራከሩት አቶ ገብሩ፤ ይህን ሃሳብ የሚያነሱ አካላት የራሳቸውን ዝግጅት ባለማድረጋቸው ለመወዳደር ስጋት ስለተፈጠረባቸው ነው የሚል እምነት እንዳ ላቸውም ተናግረዋል። በመሆኑም መንግሥት የጥቂቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ ጊዜውን በማራዘም ተጨማሪ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት እንደሚሆን አፅዕኖት ሰጥተዋል። በሌላ በኩልም ያለፈው ምርጫም ፍትሃዊነት አጠራጣሪ እንደነበር እየታወቀ መንግሥትም ሥልጣን የያዘው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ባለመሆኑ ምርጫውንም የሚያራዝም ከሆነ ቅሬታዎች ተባብሰው ወደ አገራዊ ነውጥ እንዳይሸጋገሩ ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፣ የህዝብና ቤቶች ቆጠራውም ሆነ የምርጫው ጊዜ መራዘም የለበትም የሚል እምነት አላቸው። እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ መንግሥት እንደምክንያት የሚጠቀሱ ችግሮችን ከልብ ለመፍታት መጣር እንጂ ማራዘሙ ብቻውን መፍትሄ አያመጣም። ይልቁንም ጊዜው በተራዘመ ቁጥር ችግሮቹ ሊባባሱ የሚችሉበት እድሎች ሊሰፉ ይችላሉ።
«በአሁኑ ወቅት ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ችግሮችን በእቅድና በጊዜ ለክቶ ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ አይታይም» ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ ይህም ቀውሱን የተሻለ መልክ ለማስያዝ ለሚፈልጉ ኃይሎች በር እየከፈተ መሆኑን አስረድተዋል።
መንግሥት ጊዜ በማራዘም ፖለቲካዊ ቀውሱን ሊወጣው እንደማይችለው ተገንዝቦ ለውጡ ወደታች ወርዶ ህዝቡን የሰላሙ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ሊያስቀምጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። በዋናነትም በየአካባቢው ቁጥራቸው እየተበራከቱ የመጡትን የጎበዝ አለቆችና ታጣቂዎችን በህግ አግባብ ሊያስታግሳቸው እንደሚገባ ፕሮፌሰር መረራ አስገንዝበዋል። ይህንን በአፋጣኝ ማድረግ ካልተቻለ አሁን አለ የሚባለውም መፍትሄ ከእጅ ሊያመልጡበት የሚችሉበት እድል መኖሩን ጠቁመዋል። ለቆጠራውም ሆነ ለምርጫው ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥ ከተወሰነ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታየው ፖለቲካዊ ትርምስ ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ሊዛመት ይችላል የሚል ብርቱ ስጋት እንዳላቸውንም አመልክተዋል።
የህግ ባለሙያውና አማካሪው አቶ ዝናቡ ይርጋ ደግሞ እንደተናገሩት፤ የህዝብና የቤቶች ቆጠራው መካሄድ ለምርጫውም ሆነ ለአጠቃላይ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሥራዎችን ለማካሄድ የማይተካ ሚና አለው። በዚህ መሰረት በየአስር ዓመቱ ቆጠራው ሊካሄድ እንደሚገባው የተቀመጠውን ህገመንግሥታዊ ድንጋጌ ማክበር የመንግሥት ኃላፊነት ነው። የህጉ መርህ ይህም ቢሆን ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር እንዲሁም ችግሩ ከአቅም በላይ ከሆነ ግን መንግሥት ጊዜውን እንዳያራዝም በህግ ሊታገድ እንደማይችል አስረድተዋል።
«ምክንያቱም ህግ ሁልጊዜም ቢሆን የሚ ወጣው ለህዝብ ጥቅም በመሆኑ አገሪቱን የሚመራው መንግሥት ለህዝቤ የሚበጀው ማራዘሙ ነው ካለ መቀበል ይገባል፤ ይህም ህገ መንግሥት ተጣሰ ሊባል የሚችልበት ሁኔታ የለም» ሲሉ አብራርተዋል። ከዚያ ይልቅ እንደምክንያት የተጠቀሰው ጉዳይ ምንያህል አሳማኝ ነው የሚለው ጉዳይ ሊፈተሽ እንደሚገባ ተናግረዋል። በተመሳሳይ የሚደረገው ቆጠራ ፍትሃዊና በእውነታ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር እንደሆነም ጠቅሰዋል። በሌላ በኩልም የቆጠራው መካሄድ የተራቡ ዜጎችን መጠን ለማወቅ የሚረዳ በመሆኑ እንደ አንድ መፍትሄ ሊታሰብ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ከመጋቢት 29 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ሊያካሂደው የነበረው ቆጠራ ላልተወሰነ ሂዜ እንዲራዘም ለህዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
ማህሌት አብዱል